Home › Forums › Semonegna Stories › “የማይሰበረው” የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ሰኞ በገበያ ላይ ይውላል
Tagged: አንተነህ ይግዛው, ኤርሚያስ አመልጋ, የማይሰበረው
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 5 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
July 5, 2019 at 12:36 am #11303SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በአዳዲስ የቢዝነስና የሥራ ፈጠራ ሃሳቦች አፍላቂነታቸውና በፈር-ቀዳጅ ኢንቬስተርነታቸው (entrepreneur) በሚታወቁት ኢትዮጵያዊው ኢኮኖሚስትና ባለሃብት በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ የሕይወት ታሪክና ሥራዎች ዙሪያ የሚያጠነጥነውና በደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው የተጻፈው < የማይሰበረው – ኤርሚያስ አመልጋ > የተሰኘው የሕይወት ታሪክ (biography) መጽሐፍ ከሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በገበያ ላይ ይውላል።
አጠቃላይ ዝግጅቱ ከስድስት ዓመታት በላይ ፈጅቶ የተጠናቀቀው ይህ መጽሐፍ፥ ከወላጆቻቸው የበስተጀርባ ታሪክ አንስቶ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋን የልጅነት ሕይወትና አስተዳደግ፣ የወጣትነት ዘመንና የትምህርት ቆይታ እንዲሁም ወደ አሜሪካ አቅንተው ከዘበኝነትና የዩኒቨርሲቲ ተማሪነት እስከ ግዙፉ የዓለማችን የፋይናንስ ማዕከል ዎልስትሪት (Wall Street) የኢንቨስትመንት ባንኪንግ ስመጥር ባለሙያነት የዘለቁበትን የረጅም ዓመታት ጉዞ የሚያስቃኝ ሲሆን፥ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ከ20 ዓመታት በላይ የተጓዙበትን በስኬትና በውድቀት የታጀበ፣ ፈተናና ውዝግብ ያልተለየው ረጅም የሕይወት ጎዳናም በዝርዝር ይዳስሳል።
◌ ኤርሚያስን የትኛው “ወንጀል” ሊያሳስረው ይችላል?
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የወጠኗቸውን አዳዲስና ሰፋፊ የፋይናንስ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕቅዶቻቸውን ከዳር ለማድረስ ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ጉዞ ውስጥ ያጋጠሟቸውን እሾህ አሜካላዎች፣ የተጋፈጧቸውን ፈተናና እንቅፋቶች በዝርዝር የተረኩበት መጽሐፉ፣ ከባለታሪኩ የግልና የሥራ ሕይወት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ተሰምተው የማይታወቁ በርካታ አዳዲስና አነጋጋሪ መረጃዎችን ያካተተ ነው።
በሁለት ክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበውና 12 ዋና ዋና ምዕራፎች ያሉት < የማይሰበረው – ኤርሚያስ አመልጋ > የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ፣ “ማረፊያ አንቀጾች” እና “ድህረ-ታሪክ” የሚሉ ተጨማሪ ንዑሳን ክፍሎችን ጨምሮ አጠቃላይ የገጽ ብዛቱ 394 ነው።
< የማይሰበረው – ኤርሚያስ አመልጋ > በአዲስ አበባና በሁሉም የክልል ዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ መጽሐፍት መደብሮችና በአዟሪዎች፣ በአዲስ አበባ በሁሉም የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎችና በሸዋ ሱፐርማርኬቶች፣ በስልክ ትዕዛዝ የቤት ለቤት እደላና በአማዞን ድረ-ገጽ አማካይነት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የሚሸጥ ሲሆን፣ የመሸጫ ዋጋውም 300 ብር እንደሆነ ተነግሯል።
◌ ዘመን ባንክ እንደ ይሁዳ – (ኤርሚያስ አመልጋ – ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት)
በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የታሸገ ውሃ “ሃይላንድ” ለገበያ በማቅረብ እንዲሁም “ዘመን ባንክ” እና “አክሰስ ሪል ስቴት”ን ጨምሮ ባቋቋሟቸው የተለያዩ ኩባንያዎች የሚታወቁት አወዛጋቢው ኢኮኖሚስት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፥ ከብረታ ብረት ኮርፖሬሽን የሙስና ክስ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ከወራት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውና በአሁኑ ወቅትም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆነው የፍርድ ሂደታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ጸሃፊው ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው ከዚህ ቀደም “መልስ አዳኝ” እና “ባቡሩ ሲመጣ” የተሰኙ የአጫጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን፥ ለ54 ተከታታይ ሳምንታት በፋና ኤፍ ኤም 98.1 የተላለፈውንና “ስውር መንገደኞች” የተሰኘውን ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ በደራሲነትና በተዋናይነት ለአድማጭ ማብቃቱም ይታወሳል።
ለተጨማሪ መረጃ፦
Email: yemayseberew@gmail.com, amelgaermiyas283@gmail.com
Facebook: Ermyas Tekil Amelga
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.