Home › Forums › Semonegna Stories › የስኳር ህመም ስርጭት በኢትዮጵያ ― ችላ መባል የማይገባው ትልቅ የጤና ስጋት
Tagged: Diabetes in Ethiopia, ብሔራዊ ትያትር, የስኳር ህመም, ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
November 13, 2018 at 9:00 pm #8502SemonegnaKeymaster
የዘንድሮው የዓለም የስኳር ህመም ቀን ቤተሰብ የስኳር ህመምን ለመከላከል ባለው ሚና ላይ ተመሥርቶና “የስኳር ህመም ይመለከተኛል” በሚል መሪ ሀሳብ ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በብሔራዊ ትያትር ይከበራል።
አዲስ አበባ (ኢ.ዜ.አ) – የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በዓለም አቀፍና በኢትዮጵያ ለ28ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የስኳር ህመም ቀን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከዓለም አቀፉ ስኳር ህመም ፋውንዴሽን እና “Doctors with Africa CUAMM” ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር ቀኑ ቤተሰብ የስኳር ህመምን ለመከላከል ባለው ሚና ላይ ተመሥርቶና “የስኳር ህመም ይመለከተኛል” በሚል መሪ ሀሳብ በብሔራዊ ትያትር ይከበራል።
የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር (EDA) ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብዱራዛቅ አህመድ በኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ከስኳር ህመም ጋር እንደሚኖሩ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የስኳር ህመም ስሜትና ምልክት ሳይታይ የጤና ምርመራ የማድረግ ባህል አነስተኛ በመሆኑ ከስኳር ህመም ጋር እየተኖረ እንኳን ማወቅ ባለመቻሉ የችግሩን አሳሳቢነት እንደሚያጎላው ዶ/ር አብዱራዛቅ ተናግረዋል።
በህመሙ ከተያዙት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች በተጨማሪ ሌሎች 9 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች በተለያየ አጋጣሚ የስኳር መጠን መዛባት እየጋጠማቸው መሆኑንና ይህም ችግር ካልተፈታ የታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምር እንደሚችል አመልክተዋል። በአብዛኛው በኢትዮጵያ በስኳር ህመም የሚኖሩ ሰዎች በምርመራ የጤና ሁኔታቸውን ያላወቁ መሆናቸውን ነው ዶ/ር አብዱራዛቅ ያስረዱት።
አሁን ባለው ሁኔታ የስኳር ህመም ስርጭት በቁጥጥር ስር ካልዋለ ህመሙ ልብን፣ ዓይንን፣ ኩላሊቶችን፣ ነርቮችንና የደም ቱቦዎችን ተግባር በመጉዳትና ተግባራቸውን በማስተጓጎል ከባድ የጤና ቀውስ እንደሚያስከትልም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማኅበር የህመም ስርጭቱን አሳሳቢነት በመገንዘብ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ፣ የመድኃኒት አቅርቦትና የህክምና ተደራሽነቱን ለማስፋትና ለጤና ባለሙያዎች ሙያዊ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ጤናማ ያልሆነ የአኗኗርና የአመጋገብ ዘይቤ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መቀነስ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረትና የደም ግፊት ለስኳር ህመም አጋላጭ ሁኔታዎች እንደሆኑም ነው ዶ/ር አብዱራዛቅ ያስረዱት። በአጠቃላይ የስኳር ህመምን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ መከተል በተለይ ሁለተኛውን የስኳር ዓይነት (Type 2 Diabetes) በ80 በመቶ ለመከላከል እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡ በተቻለው አቅም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር እንደሚገባውና አትክልትና ፍራፍሬዎችን መመገብ እንዲሁም ህመም ቢሰማም ባይሰማም በዓመት አንድ ጊዜ የስኳር ህመም ምርመራ ማድረግ እንደሚገባውም ምክራቸውን አቅርበዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ባለሙያ አቶ አፈንዲ ኡስማን በበኩላቸው ሚኒስቴሩ አሁን ያለውን የስኳር ህመም ችግር አሳሳቢነት ለመከላከል የሚያስችሉ ጅምር ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
የስኳር ህመም መርሃ ግብር ከፌደራል እስከ ክልል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች (non-communicable diseases) ላይ ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል እንደ ዋና መርሃ ግብር በማካተት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ የአምስት ዓመት አገር አቀፍ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ አቅድ የስኳር ህመምን በዋናነት ባከተተ መልኩ አዘጋጅቶ የመተግበር ሥራንም እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያዎችን፣ የጤና ማኅበራትንና የባለድርሻ አካላትን ያካተተ ብሔራዊ የስኳር ህመምን መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ ግብረ ኃይልም ተቋቁሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው አቶ አፈንዲ ያስረዱት።
በተጨማሪም የስኳር ህመምና ተጓዳኝ የጤና ችግሮች መድኃኒቶችን ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ እንዲገኝ ለማድረግም ሁኔታዎችን የማመቻቸት፣ በተቀናጀ መልኩ የስኳር ህመምን ለመከላከል በጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች የበሽታውን የመቆጣጠር መርሃ ግብር ሥራዎችና ሌሎችም ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል። የስኳር ህመምን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካል አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ዓለም አቀፉ የስኳር ህሙማን ቀን ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በብሔራዊ ትያትር ሲከበር የፓናል ውይይት እንደሚካሄድና የህክምና ባለሙያዎችም ስለ በሽታው ገለጻ እንደሚያደርጉ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተጠቅሷል።
የስኳር ህመም የሚከሰተው ሰውነታችን ለኑሮም ሆነ ለእድገት የሚያስፈልገውን ስኳር በትክክል ለመጠቀም ሳይችል ሲቀር ሲሆን አንድ ሰው የስኳር ህመም አለው የምንለው በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሎ ሲገኝ እንደሆነም የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
እንደ ዓለም አቀፉ ስኳር ህመም ፌዴሬሽን እ.ኤ.አ በ2017 ባወጣው መረጃ መሠረት በዓለም ደረጃ ከ425 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከህመሙ ጋር የሚኖሩ ሲሆን አስፈላጊው የበሽታው መከላከልና መቆጣጠር ካልተሰራ እ.አ.አ በ2045 የህሙማኑ ቁጥር 629 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ቅድመ ትንበያውን አስቀምጧል።
ዓለም አቀፉ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን (IDF) እ.ኤ.አ ከ1991 ጀምሮ የያዝነው ኅዳር ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የስኳር ህመምና ተጓዳኝ ችግሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር በሚል ተሰይሟል።
በኢትዮጵያ በበሽታው ከተያዙ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ 90 በመቶው በሁለተኛው የስኳር ዓይነት (Type 2 Diabetes) የተያዙ ሲሆን የተቀሩት በአንደኛው የስኳር ዓይነት (Type 2 Diabetes) የተያዙ ናቸው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) | Semonegna Health
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.