ታካሚው ከቀዶ ህክምና ወጥቶ ወደ ቤቱ እንዲሄድና የአእምሮ ህክምና በአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስቶች ክትትል እንዲደረግለት እየተመቻቸ መሆኑን የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ተናግረዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጥቅምት 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ከአንድ የ33 ዓመት ወጣት ሆድ በቀዶ ህክምና 120 ሚስማሮች፣ አንድ መርፌ ቁልፍ፣ ሁለት መርፌ፣ ሁለት ስትኪኒና ሁለት ስባሪ ብርጭቆዎች ማውጣት መቻሉ ይታወሳል። ይህ ታካሚ በአሁ ሰዓት ሙሉ ለሙሉ ከህመሙና ከቁስሉ ማገገሙን የሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ዳዊት ተዓረ አስታውቀዋል።
ዶ/ር ዳዊት እንደገለጹት፥ ታካሚው ቀዶ ህክምና ከተደረገለት ሁለት ወር ሲሆነው በአሁኑ ሰዓት ከድኅረ ቀዶ ህክምና (post-surgery recovery) አገግሞ ሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ታካሚው ከቀዶ ህክምና ወጥቶ ወደ ቤቱ እንዲሄድና የአእምሮ ህክምና በአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስቶች ክትትል እንዲደረግለት እየተመቻቸ መሆኑን ዶክተር ዳዊት ተናግረዋል።
◌ Ethio-American Doctors Group (EADG): Building a regional healthcare system & medical tourism
ታካሚው ወደ ህክምናው ሲመጣ የነበረበት የጤና ችግር በጣም አጣዳፊና ከባድ ነበር ያሉት ዶ/ር ዳዊት፥ ሚሰማሮቹ ብዙ ስለነበሩ ጨጓራውን ሙሉ ይዘውት ስለነበር ምግብ መውሰድ አይችልም ነበር ብለዋል። በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ይታይበት ስለነበር በዚህ ሁኔታ ላይ ኦፕሬሽን ማድረግ በጣም አስቸጋሪ እንደነበር ዶክተሩ ተናግረዋል።
በሁለት ወር የህክምና ጊዜ ውስጥ የምግብ እጥረት ስለነበረበት ቁስሉ ቶሎ ማገገም እንዳይችል ማድረጉን የገለጹት ዶ/ር ዳዊት፥ በአሁኑ ሰዓት ታካሚው ሁሉም ነገር ድኖለት መንቀሳቀስና መመገብ መቻሉን ተናግረዋል። ዶክተሩ አክለውም በህይወታቸውና በሙያ አገልግሎታቸው ደስተኛ ካደረጉዋቸው የህክምና ሥራዎች አንዱ ይሄ መሆኑንም ተናግረዋል።
ታካሚው በበኩሉ ምግብ በአግባቡ እየተመገበ መሆኑን ገልጾ ወደ ቤቱ መግባት እንደሚፈልግ ተናግሯል።
ምንጭ፦ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል
——
ሌሎች ዜናዎች፦