ባለፉት ስድስት የሽልማት መርሀግብሮች አገራችን የምትኮራባቸውን የላቀ አርአያነት ያለው ተግባር ላከናወኑ ሰዎች እውቅና የተሰጠው ከሕዝብ በቀረበ ጥቆማ መሠረት ሲሆን፥ የዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት ፕሮግራም ለአገራቸው እድገት አርአያነት ያለው አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች ዕውቅና የሚያገኙበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–ሰባተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ፕሮግራም የዕጩዎች ጥቆማ ግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደጀመረ እና እስከ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ እንደሚከናወን የሽልማት አስተባባሪ ኮሚቴው አስታወቀ።
ኮሚቴው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለአገርና ለሕዝብ አርአያነት ያለው ታላቅ ተግባርን ያከናወኑ ሰዎችን ዕውቅና የሚሰጠው የበጎ ሰው ሽልማት ሰባተኛው መርሃ ግብር ነሀሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ይካሄዳል።
ሽልማቱም በመምህርነት፣ በሳይንስ፣ በኪነ-ጥበብ፣ በበጎ አድራጎት ሥራ፣ በቢዝነስ ሥራ ፈጠራ፣ በመንግስት የሥራ ተቋማት ኃላፊነት፣ በቅርስና ባህል፣ በማኅበራዊ ጥናት፣ በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፎች እና ለኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎችን የሚያካትት እንደሆነ ኮሚቴው ገልጿል።
ለእያንዳንዱ የሽልማት ዘርፍ ሦስት ዳኞች ተመርጠው ምርጫው የሚከናወን ሲሆን ዳኞቹም የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውና በታማኝነት ምርጫውን ያከናውናሉ ተብለው የታመነባው እንደሆኑ በመግለጫው ወቅት ተጠቅሷል።
ኮሚቴው እንደገለፀው፥ ባለፉት ስድስት የሽልማት መርሀግብሮች አገራችን የምትኮራባቸውን የላቀ አርአያነት ያለው ተግባር ላከናወኑ ሰዎች እውቅና የተሰጠው ከሕዝብ በቀረበ ጥቆማ መሠረት መሆኑን ገልፆ፥ መርሀግብሩን ለዚህ ያበቃው በሂደቱ የሕዝብ ተሳትፎ በመኖሩ ስለሆነ ይህም አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
የበጎ ሰው ሽልማት ዋና ዓላማ ለአገራችን መልካም የሠሩ፣ አገራዊ ተልዕኳውን በብቃት የተወጡ፣ የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል ለውጥ አምጪ ተግባራትን ያከናወኑ፣ የአገሪቱን ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል እንዲጠበቅና የሀገራቸው ስልጣኔ ከፍ እንዲል የሠሩ ኢትዮጵያዊያንን በማበረታታት ዕውቅና በመስጠት ሌሎች በጎ ሥራዎችን ለሀገራቸው ማበርከት እንዲችሉ ማስቻል ነው።
ይህንን የበጎ ሰው ሽልማት ዓላማ ከግምት ውስጥ በማስገባት ህብተረሰቡ ጥቆማውን ከግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በስልክ፣ በቫይበር (Viber)፣ በቴሌግራም (Telegram)፣ በኋትሳፕ (WhatsApp)፣ በኢሜይል (e-mail)፣ በፖስታና በአካል በመቅረብ መጠቆም እንደሚቻል ኮሚቴው ያሳወቀ ሲሆን፥ ለዚህም አገልግሎት በስልክ ቁጥር 0940140813፣ begosewprize@gmail.com እና ፖስታ ሳጥን ቁጥር 150035 አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ መጠቀም ይቻላል ተብሏል።
የዘንድሮው የሽልማት ፕሮግራም ለአገራቸው እድገት አርአያነት ያለው አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች ዕውቅና የሚያገኙበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ