በተሽከርካሪ ላይ የሚገጠመው የተቀናጀ የተሸከርካሪ ፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያ ከዓለም አቀፍ ስርዓት አቅጣጫ (GPS) ጋር የተጣመረ ሆኖ ወደ ተሸከርካሪው ሞተሩ የሚገባውን ነዳጅ አሊያም አየር በመቀነስ የተሸከርካሪውን ፍጥነት የሚቆጣጠር መሣሪያ ነው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የመንገድ ትራፊክ አደጋ እያደረሰ ያለውን የሰው ልጅ ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ለመቀነስ እየተሠራ ቢሆንም አደጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። ለመንገድ ትራፊክ አደጋ መከሰት በርካታ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆን ከተወሰነው የፍጥነት ገደብ በላይ ማሽከርከር በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ውስጥ በቀዳሚነት ይገኛል።
የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን ቀንሰው በጥንቃቄ በማሽከርከር አደጋውን መቀነስ እንዲችሉ የግንዛቤ ሥራዎችን ከመሥራት ጎን ለጎን የተሸከርካሪዎችን ፍጥነት መገደብ እንደሚገባ በማመን በተሸከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ስለመግጠም እና ስለማስተዳደር የሚገልጽ መመርያ አዉጥቷል።
በተሽከርካሪ ላይ የሚገጠመው የተቀናጀ የተሸከርካሪ ፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያ ከዓለም አቀፍ ስርዓት አቅጣጫ (GPS) ጋር የተጣመረ ሆኖ እንደተሸከርካሪው ሁኔታ ወደ ሞተሩ የሚገባውን ነዳጅ ወይም አየር በመቀነስ የተሸከርካሪ ፍጥነት በህግ ከተደነገገ በላይ እንዳይፈጥን የሚቆጣጠር መሣሪያ ነው።
የሚገጠመው የፍጥነት መቆጣጠሪያ ጣሪያም የፍጥነት ወሰን ህጉ በሚደነግገው ከፍተኛ የፍጥነት ወሰን ጣሪያ መሠረት ይሆናል። አሽከርካሪው በትራፊክ መቆጣጣሪያ ደንብ መሠረት ፍጥነቱን ከተፈቀደለት የፍጥነት ወሰን በታች ማሽከርከር የሚገባው ሁኔታ ሲኖር ፍጥነቱን ቀንሶ ማሽከርከር እንደሚገባ ይገልፃል።
የፍጥነት መገደቢያው የሚገጠምላቸው ተሸከርካሪዎች የምርት ዘመናቸው እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከ2000 እና በኋላ ያሉ ተሽከርካሪዎች ናቸው። ከተካተቱት ውጪ ያሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያው ስለሚገጠምበት ሁኔታ ባለስልጣኑ ወደፊት የሚወስን ሲሆን ይህ መመሪያ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡና በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ተሸከርካሪዎች ባለስልጣኑ ፍቃድ ከሰጠው አካል የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ የተገጠመላቸዉ ብቻ ይሆናሉ።
ምንጭ፦ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦