በኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ-ረቂቅ ውይይት ላይ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች መድረክ ረግጠው ወጡ

Home Forums Semonegna Stories በኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ-ረቂቅ ውይይት ላይ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች መድረክ ረግጠው ወጡ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #11501
    Semonegna
    Keymaster

    ‘በሕገ-ረቂቁ እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ማሻሻያዎች አልተካተቱም፤ ሃሳቦቻችንና አስተያየቶቻችን ያልተካተቱበትን ሰነድ ለመቀበል እንቸገራለን’ በማለት የተወሰኑ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች መድረኩን ረግጠው መውጣታቸውን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ-ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ ማኅበራት ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።

    ‘በሕገ-ረቂቁ እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ማሻሻያዎች አልተካተቱም፤ ሃሳቦቻችንና አስተያየቶቻችን ያልተካተቱበትን ሰነድ ለመቀበል እንቸገራለን’ በማለት የተወሰኑ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች መድረኩን ረግጠው መውጣታቸውን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።

    እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ማሻሻያዎች ሳይካተቱ ሕገ-ረቂቁ እንዳይጸድቅ ሲሉ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮቹ ቋሚ ኮሚቴውን አሳስበዋል።

    የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ በበኩላቸው መሠረታዊ ማሻሻያዎች የተደረገባቸው አሥራ ሦስት ነጥቦች በሕገ-ረቂቁ መካተታቸውን ገልጸው፣ የብዙሃኑን የተፎካካሪ ፓርቲ ሃሳብና አስተያየት አካተናል ብለዋል።

    ማሻሻያዎቻችን አልተካተቱም ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ለቋሚ ኮሚቴው በጽሑፍ ማቅረብ እንደሚችሉም ወይዘሮ የሺእመቤት አሳውቀዋል።

    በውይይቱ ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ለምርጫ በዕጩነት ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ የምርጫ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሥራ ገበታቸው በጊዜያዊነት እንደሚለቁና ደመወዝና ጥቅማ-ጥቅማቸውም እንደማይከር በሚዘረዝረው ረቂቅ-ሕግ አንቀጽ 33 ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበታል።

    በደመወዙ ኑሮውን መደጎም ያልቻለን የመንግሥት ሠራተኛ ለምርጫ በዕጩነት ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ደመወዙና ጥቅማ-ጥቅሙ አይከበርም ማለት ወደ ምርጫ አትግቡ ከማለት ለይተን አናየውም ብለዋል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮቹ።

    የመንግሥት ሠራተኞች በሥራ ኃላፊነት ያገኙትን ስልጣን፣ የመንግሥትንና የሕዝብን ሃብትና ንብረት ለምርጫው አገልግሎት እንዳያውሉት ለማስቻል እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ተናግረዋል።

    ረቂቅ ሕጉ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታ ጀምሮ እስከ የመሥራች ቁጥር አባላት ድረስ አዳዲስ አሠራሮችን እንዳካተተም ተገልጿል።

    አንድ ሃገር-አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ቢያንስ አስር ሺህ እንዲሁም አንድ የክልል ፓርቲ ለመመሥረት ደግሞ ቢያንስ አራት ሺህ አባላት እንደሚያስፈልጉ በረቂቅ ሕጉ ተጠቅሷል።

    ሃገር አቀፍም ሆነ የክልል ፓርቲ ለመመሥረት ሃገሪቱ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ የተጠቀሰውን የመሥራች ቁጥር አባላት ለማሟላት እንደሚቸገሩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተናግረዋል።

    መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት ሃገር የተጠቀሰውን የመሥራች ቁጥር አባል ማሟላት አስቸጋሪ እንደማይሆን ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ አብራርተዋል።

    በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. 107 የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር አሁን ላይ 137 እንደደረሰ ወይዘሪት ብርቱካን ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    [caption id="attachment_11503" align="aligncenter" width="600"]የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች[/caption]


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.