አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የመጽሐፍት አውደ-ርዕይና ሲምፖዚየም ተካሄደ

Home Forums Semonegna Stories አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የመጽሐፍት አውደ-ርዕይና ሲምፖዚየም ተካሄደ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #11145
    Semonegna
    Keymaster

    ‹‹የንባብ ባህላችንን እናዳብር፤ ምክንያታዊ ትውልድ እንፍጠር›› በሚል መሪ-ቃል የመጽሐፍት ሽያጭ፣ ዓወደ-ርዕይና ሲምፖዚየም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ሠራተኞችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።

    አርባ ምንጭ (AMU) – በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት “የንባብ ባህላችንን እናዳብር፤ ምክንያታዊ ትውልድ እንፍጠር” በሚል መሪ-ቃል የመጽሐፍት ሽያጭ፣ ዓወደ-ርዕይና ሲምፖዚየም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰኔ 3 ቀን እስከ ሰኔ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ተካሂዷል።

    የዝግጅቱ ዓላማ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በንባብ ባህል ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር እውቀት እንዲስፋፋ እና ልምድ እንዲዳብር ለማድረግ እንዲሁም ማኅበረሰቡ የመጽሐፍትን ጥቅም ተረድቶ ከሌሎች ወጪዎች በመቀነስ የመግዛት ልምድ እንዲቀስም ለማስቻል መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለምሰገድ ካሣሁን ገልፀዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ ገጣሚ፣ ደራሲና መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ የንባብ ጅማሮ፣ ጥቅምና የመምህራን ሚናን አስመልክቶ ባቀረቡት አንኳር ሀሳብ ንባብ ሊለካ የሚችለው በአንባቢው ላይ በሚያመጣው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንደሆነ ገልጸዋል። ንባብ የተለያየ ነገር ግን የተዋሀደ ይዘት ያለው እንደመሆኑ ማኅበራዊ ተግባቦት እንዲጨምር፣ ተአማኒ እውቀት እንዲዳብር ብሎም ባልኖርንበት ዘመንና ቦታ በምናብ እንድንኖር የሚያደርግ ጥልቅ ምስጢር አለው ብለዋል።

    ጥሩ አንባቢ የአፃፃፍ ስልትና የቃላት አመራረጥን ከመረዳት ባለፈ በሚያነበው ጉዳይ ራሱን የሚመለከትና የሚፈትሽ እንዲሁም የሌሎችንም ስሜት መረዳት የሚችል እንደሆነ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ተናግረዋል። ለዚህም መምህራን ከመጽሐፍት ምርጫ አንስቶ መልካም ልምዶችን ለትውልዱ በማካፈል በመረጃ የዳበረና ያወቀ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ለአንድ ማኅህበረሰብ እድገት የተማረ ማኅበረሰብ መፍጠር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደመሆኑ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአገሪቱ ከመሠረተ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል።

    ማንበብና መጻፍ ከግለሰብ ባለፈ ለማኅበረሰብ ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ናቸው ያሉት ፕሬዝደንቱ፥ የንባብ ባህል እንዲዳብር አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት፣ አቅምና ጊዜ በተገቢው በመጠቀም፣ ተፈላጊውን የአዕምሮና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት እንዲሁም ምክንያታዊ ትውልድ በመፍጠር ከግለሰብና ከማኅበረሰብ ባለፈ ለአገር ዕድገት አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚቻል ገልፀዋል። በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለንባብ ባህል መዳበር አጽንዖት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

    የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ምንም እንኳ ጥንታዊ የሆኑና የተለያየ ዘውግ ያላቸው የስነ-ጽሑፍ ውጤቶች እንዲሁም ወቅታዊ አዕምሯዊ ውጤት የሆኑ የህትመት ውጤቶች ቢኖሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚታየው የንባብ ባህል መቀዛቀዝ በመረጃ የበለጸገና ምክንያታዊ የሆነ ዜጋ ከመፍጠር አኳያ እንደ አገር ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንደሆነ ተናግረዋል። በአገሪቱ ለንባብ የሚውለው ጊዜ በዓለም አንባቢ ዜጋ ካላቸው አገራት አንጻር በሣምንት ለንባብ ከሚያውሉት አማካይ ጊዜ በእጅጉ መራቁን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያስረዱም ዶ/ር የቻለ ገልፀዋል።

    በማኅበረሰቡ ዘንድ መጽሐፍትን ገዝቶ ከማንበብ ይልቅ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ምርኮኛ መሆን፣ የወረቀትና የህትመት ዋጋ መጨመርና ሌሎችም ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ይሁን እንጂ የንባብ ባህል መዳበር ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ባህሉ እንዲያንሰራራና መሻሻሎች እንዲመጡ ጠንከር ያለ ጥረትን ይጠይቃል።

    በንባብና ሚዲያ ቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚያጠነጥን የውይይት መነሻ ጽሑፍ የዶክትሬት (PhD) ተማሪ በሆኑት አቶ ተመስገን ካሣዬ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በዚህም ዘመኑ የቴክኖሎጂና የመረጃ ከመሆኑ ባሻገር የሚዲያ ተግባቦት ባህሎችን ከሌላው ጋር የመቀየጥ አቅም ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ ተገልጿል።

    ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ንባብ የአንድ ወቅት ሂደት ስላልሆነ በየደረጃው ያለው ሁሉም ማኅበረሰብ ከዋና ሥራው ጎን ለጎን መጽሐፍት ማንበብን ልምድ በማድረግ ከራሱ አልፎ ለሌሎችም መትረፍ የሚያስችል አቅም ማጎልበት እንደሚገባው ገልጸዋል። በተለይም በአገራችን ያሉ ደራሲያን መጽሐፍት ስነ-ጽሑፋዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ፣ ታሪክን ሳያዛቡ እንዲሁም በሥነ-ምግባር ረገድ የተሻለ አቀራረብ እንዲይዙ በማድረግ ንቁ ማኀበረሰብ በመፍጠር ለአገራዊ ለውጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

    በመጽሐፍት አውደ ርዕይና ሲምፖዚየሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ከተማ እና ከአዲስ አበባ የመጡ የቤተ-መጽሐፍት ባለሙያዎችና የመጽሐፍት ሽያጭ መደብሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

    ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የንባብ ባህል


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.