Home › Forums › Semonegna Stories › 79ኛውን የአርበኞች የድል በዓል በማስመልከት ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ያስተላለፉት መልዕክት
Tagged: ሣህለወርቅ ዘውዴ, የአርበኞች የድል በዓል
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 4 years, 8 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
May 5, 2020 at 2:10 am #14372SemonegnaKeymaster
79ኛውን የአርበኞች የድል በዓል በማስመልከት ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ያስተላለፉት መልዕክት
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፥
እንኳን ለ79ኛው የድል ቀን በሰላም አደረሰን። በመላው ዓለም በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት የተነሳ እንደለመድነው በአርበኞች ሀውልት ዙሪያ አንድ ላይ ተሰባበስበን በዓሉን ማክበር አልቻልንም። ሆኖም ግን የእነዚያን የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆችን ዘመን የማይሽረው ተጋድሎ በመንፈስ አድምቀነው እንደምንውል እምነቴ ጽኑ ነው።
የዓለም የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ጮራ የሆነውን የአድዋ በዓልን የዛሬ ሁለት ወር አክብረናል። [ዛሬ] ደግሞ በተመሳሳይ የኩራትና የአይበገሬነት ከፍታ እንዲሁም መንፈስ ላይ የሚያስቀምጠንን የሚያዝያ 27 የድል በዓልን አስበን እንውላለን። ይህን ቀን ስናስታውስም ብዙ የታሪክ ሰበዞች ተከታትለው ይቀመጣሉ። አድዋ ላይ ያላሰቡትን ውርደት የተከናነቡት ፋሽስቶች ቂማቸውን ለመወጣት ቀን ሲቆጥሩ ከርመዋል። የታጠቁትን መሣሪያ ተማምነው የጠነሰሱትን ባርነት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ለማንገስ ተማምለው ድንበር ጥሰው ገቡ። መጀመሪያ ገደማ ያሰቡት የሰመረላቸው መሰላቸው። በኢትዮጵያውያን ላይ ያዘነቡት የሞት መዓት እድሜ ልካቸውን ከዚህች ምድር የሚነቅላቸው እንደሌለ ዋስትና አድርገው ወሰዱት። በከተማውና በገጠሩ የሞት ነጋሪት ጎሰሙበት።
ብዙም ሳይቆይ ግን ታሪክ ተገለበጠ። ኢትዮጵያውያንን በቅኝ ግዛት ለማንበርከክ የተመመው የፋሽቶች ሠራዊት የወጠነውን ሳይጨርስ ግማሽ መንገድ ላይ ቀረ። ኢትዮጵያውያን እናትና አባት አርበኞች የሞሶሎኒን የአደባባይ ድንፋታ እና የሠራዊቱን እብሪት የጠዋት ጤዛ አደረጉት። የአድዋውን ቂም ለመበቀል ከ40 ዓመታት በኋላ የተወጠነው ዘመቻ በድጋሚ በአድዋ መንፈስ መና ቀረ።
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፥
ይህ የኢትዮጵያውያን በጨለማ ውስጥ ብርሃን መፈለግን፣ በመከራ ውስጥ ተባብሮ ማንሰራራትን፣ በጭንቅ ጊዜ ተስፋ ማድረግን በተለይ አሁን ለምንገኝበት ሁኔታ እጅግ በጣም አስፈላጊያችን ስንቅ ነው ብየ አምናለሁ። የአድዋ እና የአርበኞችን ድል መንፈስ እየታደሰ የሚቀጥል ህያው መንፈስ ማድረግ አለብን። ለዘላቂ የሀገራችን ጥቅሞች ልናውላቸው ይገባናል። በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሳየነውን አንድነትና ታላቅ ህልም በሌሎችም ላይ እናባዛው። ዛሬ በተለያየ መልኩ የተደቀኑብንን ፈተናዎች ድል ለመንሳት እናውላቸው።
የኮሮና ወረርሽኝ የደቀነብን አደጋ ከማይታይ ጠላት ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው። የቫይረሱ ተለዋዋጭ ሁኔታ ሥራችንን ሁሉ ዱካውን ያጠፋ ጠላት ያህል ፈታኝና ውስብስብ አድርጎብናል። መመሪያ አክብረን፣ የሚጠበቅብንን ተወጥተን እስከተፋለምነው ድረስ ለመቆጣጠር ያለንን ዕድል ያሰፋዋል። ከወረርሽኙ በኋላ የሚኖረውን ሁኔታ ከአሁኑ የተሻለ ለማድረግም የቤት ሥራችንን መጀመር ይኖርብናል፤ ዛሬ ያልሠራንበትን ነገ አናገኘውምና።
የኢትዮጵያን የድህነትና የርሃብ ታሪክ ጨርሶ ለመለወጥ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ተቻችለን፣ ተደማምጠን እና ተከራክረን የሀገራችንን ተስፋ ለማለምለም ቆርጠን እንነሳ። ይህን ስናደርግ የእነዚያ አይበገሬ ኢትዮጵያውያን አሻራ ህያው ሆኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሸጋገራል። ያለንበትን ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ለዘላቂ እድገት እናውለው።የአድዋም ሆነ የአርበኞች ድል ከዚህ ውጭ የመጣ አይደለምና።
መልካም የአርበኞች የድል በዓል
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.