Home › Forums › Semonegna Stories › በአማራ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የአተት ወረርሽኝ ምልክት መታየቱን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ
Tagged: acute watery diarrhea, AWD, አተት, የአተት ወረርሽኝ, የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 5 years, 5 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
May 13, 2019 at 1:51 am #10840SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በአማራ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የአተት ወረርሽኝ (acute watery diarrhea /AWD/) ምልክት መታየቱን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ የአተት ወረርሽኙን አስመልከቶ በሰጠው መግለጫ፥ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር እና ዋግህምራ ዞኖች በተለያዩ ወረዳዎች እየተደረጉ ባሉ የቅኝት ሥራዎች የአተት ወረርሽኝ መከሰቱ የታወቀ ሲሆን የወረርሽኙን መንስዔ ለማረጋገጥ የላብራቶሪ ምርመራ እየተካናወነ መሆኑን አስታውቋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአንድ ታማሚ ናሙና ቫይብርዮ ኮሌራባክቴሪያ (Vibrio cholera bacteria) የተገኘበት ሲሆን ወረርሽኙን ለማረጋገጥ በተጨማሪ ናሙናዎች ላይ የላብራቶሪ ምርመራ እንደሚከናወንም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
ከሚያዝያ 27 ቀን ጀምሮ በአማራ ክልል በዋግህምራ ዞን በአበርጌሌ ወረዳ 58 ሰዎች በበሽታው የተጠረጠሩ ሲሆን በሰሜን ጎንደር ዞን በጠለምት ወረዳ 90 ሰዎች፣ በበየዳ ወረዳ ደግሞ 4 ሰዎች በበሽታው ተጠርጥረዋል።
እንደ ኢንስቲትዩቱ መግለጫ፥ በአጠቃላይ በክልሉ በበሽታው 151 ሰዎች የተጠረጠሩ ሲሆን ሁሉም በበሽታው የተጠረጠሩ ህሙማን በአቅራቢያው ለዚህ አገልግሎት ብቻ ተብሎ በተቋቋሙ ጊዚያዊ የሕክምና ማዕከላት በቂ ሕክምና እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፤ በጠለምት ወረዳ ግን 3 ታካሚዎች በሕክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው አልፏል።
በፌደራል፣ በክልልና በዞን ደረጃ ፈጣን ምላሽ ሰጪ የሕክምና ቡድን ወደ አበርጌሌ፣ ጠለምትና በየዳ ወረዳዎች ተልኮ ምላሽ በመስጠት ላይ እንደሚገኝና የዓለም ጤና ድርጅትና ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድንም በቦታው በመገኘት ድጋፍ እየሰጡ መሆኑም ተገልጿል።
ከላይ ወደተጠቀሱት ወረዳዎች አስፈላጊ የሕክምና መስጫ መሣሪያዎች፣ መድኃኒቶችና መመርመሪያዎች እንዲቀርቡ መደረጉም ነው የተጠቆመው።
በአጎራባች ወረዳዎች ወረርሽኙ ቢከሰት በቂ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችሉ መድኃኒቶችና የሕክምና ግብአቶች በፍጥነት ማቅረብ እንዲቻል በጎንደር፣ በደሴና በሽሬ በሚገኙ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ መጋዘኖች እንዲከማቹ መደረጉንም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሕብረተሰቡ፡ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የመፀዳጃ ቤት በመሥራት እና በአግባቡ በመጠቀም፣ የመመገቢያ፣ የመጠጫ እና የውሃ ማስቀመጫ እቃዎችን በንጹህ ውሃ በማጠብ እና ከድኖ በማስቀመጥ ከዝንቦችና ከበካይ ነገሮች በመጠበቅ፣ ለማንኛውም አገልግሎት የሚውልን ከጉድጓድ፣ ከምንጭ፣ ከወንዝ እና ከመሳሰሉት የተቀዳ ውሃን በማከም ወይም በማፍላት በመጠቀም፣ ምግብ ከማዘጋጀት፣ ከማቅረብ፣ ከመመገብ በፊት፣ ከመፀዳጃ ቤት መልስ እና ሕፃናትን ካፀዳዱ በኋላ እጅን በመታጠብ፣ ምግብን በሚገባ አብስሎ በመመገብ፣ ከድኖ እና በንጹህ ቦታ በማስቀመጥ ከዝንቦችና ከሌሎች ነፍሳት ንክኪ በመጠበቅ ራሱንና ቤተሰቡን ከተላላፊ በሽታዎች በመከላከል የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።
የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ወረርሽኝ በተበከለ ውሃ ወይም ምግብ አማካይነት የሚከሰት ሲሆን ይህንንም ከሚያመጡ ተህዋሲያን መካከል ኮሌራን የሚያስከትለው ቪቢሮ ኮሌሬ የተሰኘው ባክቴሪያ ይገኝበታል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሌራ ወረርሽኝ በህንድ፣ በየመን፣ በኔፓል ፣ በካናዳ ቫንኮቨር ደሴት እንዲሁም በአህጉራችን አፍሪካ በዘጠኝ ሀገራት ማለትም በካሜሩን፣ በኬኒያ፣ በሶማሊያ፣ በሞዛምቢክ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮነጎ፣ በታንዛኒያ፣ በሊቢያ፣ በዙምባብዌ እና በዛምቢያ የተከሰተ ሲሆን ሀገራቱ ችግሩን ለመቅርፍ እየሰሩ ናቸው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
A WHO/UNICEF Risk Communication team member explains AWD prevention and control to health workers (PHOTO: WHO Africa)
June 5, 2019 at 11:36 am #11064AnonymousInactiveየተከሰተውን የአተት ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ግብረ ሃይል ተቋቋመ
—–በአምስት ክልሎች የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል መቋቋሙን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሰታወቀ።
በአምስት ክልልች በተከሰተው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ወረርሽኝ እስከአሁን የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ ፡፡
ወረርሽኙን በአፋጣኝ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የህክምና ግብአቶች በሁሉም ክልሎች ወደሚገኙ የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ መጋዘኖች መላካቸውንም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡
እስካሁን ድረስ በኦሮሚያ 138፣ በአማራ 198፣ በሱማሌ 33 እና በትግራይ 8፤ በድምሩ 377 ሰዎች በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ተይዘዋል ብሏል ኢንስቲትዩቱ።
ምንጭ፦ ኢቢሲ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.