Home › Forums › Semonegna Stories › አዲስ አበባ ከተማን የተመለከቱ ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች
Tagged: የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን
- This topic has 3 replies, 2 voices, and was last updated 4 years, 1 month ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
September 4, 2020 at 3:20 pm #15714AnonymousInactive
የአዲስ አበባ የወጪና ገቢ ንግድ ማሳለጫ ኮሪደር የሆነው የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ገፅታዎች
አዲስ አበባ (አአመባ) – የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (አአመባ) በሥራ ተቋራጮች ከሚያስገነባቸው ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት የትራፊክ ፍሰቱን ሊያሳልጡ የሚችሉ በርካታ ገፅታዎች አሉት።
የመንገድ ፕሮጀክቱ 11 ኪ.ሜ ርዝመትና 50 ሜትር የጎን ስፋት አለው። በመንገዱ ግራና ቀኝ መስመሮች ላይ በአንድ ጊዜ ብቻ 8 መኪናዎችን በቀላሉ ማሳለፍ የሚያስችል ነው። የመንገዱ ዋና ዋና መገጣጠሚያዎችና ማሳለጫዎች ላይ ደግሞ ከ70 እስከ 100 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት ይኖረዋል።
ከመኪና መስመር ባሻገር በግራና በቀኝ 6.5 ሜትር ስፋት ያለው የሳይክል መስመር፣ እግረኛ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ 9 ሜትር ድረስ ስፋት ያላቸው የእግረኛ መንገዶች፣ በመንገዱ መሀል ላይ 11 ሜትር ስፋት ያለው ለብዙሃን ትራንስፖርት ብቻ የሚያገለግል መስመር እንዲሁም በመንገዱ ግራና ቀኝ ላይ 32 የሚሆኑ የአውቶቡስ ማቆሚያዎች ይኖሩታል። እነዚህ የአውቶቡስ ማቆሚያዎች ከ40 እስከ 60 ሜትር ርዝመትና ከ3 እስከ 7 ሜትር የጎን ስፋት ይኖራቸዋል።
የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ሌላው ገፅታ ደግሞ ሦስት ዋና ዋና ማሳለጫዎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው የፕሮጀክቱ መነሻ የሆነው የቃሊቲ አደባባይ ነው። ይህ ማሳለጫ በመሀላቸው ዘጠኝ ሜትር ስፋት ያላቸው 8 ስፓን እና 240 ሜትር ርዝመት ያላቸው ሁለት ድልድዮችን የያዘ ነው።
ሁለተኛው ማሳለጫ ጥሩነሽ ቤጂንግ ማሳለጫ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፥ 100 ሜትር ርዝመት የሚጠጋ ድልድይ አለው። ይህ ማሳለጫ ወደ አቃቂ ከተማ፣ ወደ ሄኒከን ቢራ (Heineken Ethiopia)፣ ወደ ደራርቱ ት/ቤት፣ ወደ ቱሉ ድምቱ አደባባይ እና ወደ ቃሊቲ አደባባይ በድምሩ አምስት ዋና ዋና የመንገድ መጋጠሚያዎችን ለማሳለጥ የሚያገለግል ነው።
ሦስተኛውና የመጨረሻው ማሳለጫ ቀድሞ ጋሪ ድልድይ እየተባለ የሚጠራው ሲሆን፥ በ50 ሜትር ርዝመትና በ20 ሜትር የጎን ስፋት እየተሠራ ይገኛል።
አጠቃላይ የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱን የቻይናው ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ በ2 .4 ቢሊዮን ብር በጀት እያከናወነው ሲሆን፥ እስካሁን ድረስም 65 በመቶ ገደማ አፈፃፀም አስመዝግቧል። የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ በመንገዱ በግራ መስመር 800 ሚሊ ሜትር ውፍረት ያለው ግዙፍ የውሀ መስመርና የመብራት ፖሎች ባለመነሳታቸው እንቅፋት ፈጥረውበታል። ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት እነዚህን የወሰን ማስከበር ችግሮች ለመፍታት ከመብራት ኃይል፣ ከከተማዋ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን እንዲሁም ከሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቅርበት እየሠራ ችግሩን በመፍታት ላይ ይገኛል።
የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታው ሲጠናቀቅ በሀገሪቱ በምሥራቅ አቅጣጫ በኩል የሚደረገውን የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። ከዚህም በተጨማሪ የመዲናዋን ነዋሪዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማሻሻሉም ባሻገር የከተማዋን ገፅታ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀይራል ተብሎ ይጠበቃል።
ምንጭ፦ አአመባ
September 10, 2020 at 2:59 am #15805SemonegnaKeymasterሸገር ፓርክ በትልቅ ሥነ-ሥርዓት ተመርቋል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባን ከተማ የቀይራል ተብሎ የሚጠበቀው ሸገር ፓርክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በአዲስ ዓመት ዋዜማ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ባለስልጣናት እና ጥሪ የተደረገላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም በተገኙበት ተካሂዷል።
ሸገር ፓርክ የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊነት በሚያሳይ መልኩ የተገነባ ሲሆን፥ በውስጡ የተፈጥሮ እጽዋትንም ያካተተ ነው። ፓርኩ የኢትዮጵያን ቀደምት ታሪክ በማሳየት የወደፊት ብሩህ ተስፋን የሚያሳይ የወዳጅነት ፓርክ እንደሆነ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
ግንባታው ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ሸገር ፓርክ በቻይና ግዙፉ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ “China Communications Construction Company (CCCC)” የተገነባ ነው።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፓርኩ ግንባታ አስተዋጽኦ ላደረጉ የቻይና የተለያዩ ኩባንያዎች ትልቁን የወዳጅነት ሽልማት አበርክተዋል። በግንባታው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያንም እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሸገር ፓርክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰዱ ነጥቦች፡-
- አዲስ አበባ ይህን ፓርክ ማግኘቷ ስሟንና ደረጃዋን ከፍ ያደርገዋል፤
- ይህ እና ሌሎች ፓርኮች የከተማይቱንና የሀገራችንን ገፅታ ያስውቡታል፤
- ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤
- ፓርኩ ተባብሮ መሥራት የሚያስገኘውን ውጤት ማሳያ ነው፤
- ሸገር ፓርክ ከመሃል ሀገር ሳንወጣ ሩቅ ቦታ የተጓዝን የሚያስመስለን ፓርክ ነው፤
- ከተለምዶው የተለየ ነገር ማየት አድማሳችንን ያሰፋዋል፤
- [በግሌ] ይህ ፓርክ በዚህ ፍጥነት ለምረቃ ይበቃል ብዬ አላሰብኩም ነበር፤
- በፓርኩ በሚገኘው የአበባ ማፍያ ስፍራ ከዓይናችን ጠፍተው የቆዩ አበቦችን ሳይቀር ማስተዋል ችያለሁ፤
- ውበትን መሻት ካለንበት ሀኔታ ጋር አይፃረርም፤
- አገራችንን የማስዋብ ጥረታችንን ከሌሎች የልማት ጥረቶቻችን ጋር ጎን ለጎን ካስኬድነው በአጭር ጊዜ የአገራችንን ገፅታ መቀየር እንችላለን፤
- በፕሮጀክቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል።
October 19, 2020 at 3:21 am #16398AnonymousInactiveአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ተጨማሪ 560 አውቶቡሶች ተሰማሩ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውንና እጅግ ስር የሰደደውን የሕዝብ ትራንስፖርት ችግር በጥቂቱ ለመቅረፍ ተጨማሪ 560 አውቶቡሶች ለአገልግሎት መሰማራታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
“የትራንስፖርት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከአውቶብስ አቅርቦት በተጨማሪ ዘመናዊ የትራንስፖርት የመሠረተ ልማት ሥርዓት እንዲዘረጋ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው” በማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኪራይ ወደ ስምሪት የገቡትን እነዚህን 560 አውቶብሶች ሥራ አስጀምረዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፥ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የትራንስፖርት ችግር በነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።
የትራንስፖርት ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለመፍታት በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ የጋር ትብብር 560 አውቶብሶችን በኪራይ ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ መወሰኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ከአሁን ቀደም በየወሩ ለብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት 58 ሚሊዮን ብር ድጎማ በማድረግ ላይ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ለአውቶቡሶች ኪራይ 63 ሚሊየን ብር በጠቅላላው 121 ሚሊዮን ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ምክትል ከንቲባዋ አመልክተዋል።
የትራንስፖርት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ከአውቶብስ አቅርቦት በተጨማሪ ዘመናዊ የትራንስፖርት የመሠረተ ልማት ሥርዓት እንዲዘረጋ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል። በቀጣይ ሁለት ዓመታትም በ12 ቢሊዮን ብር ወጪ 3 ሺህ የሚሆኑ አውቶብሶችን በግዢ ለማስገባት የከተማ አስተዳደሩ በሂደት ላይ መሆኑንም ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል። ወደፊትም የነዋሪዎቻችንን ችግር በቅርበት አዳምጠን እና ተረድተን ተጨባጭ መፍትሄ የመስጠቱን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል – ወ/ሮ አዳነች።
በኪራይ ወደ ስምሪት የ560 አውቶብሶች ከጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ የሚጀምሩ ሲሆን ለአንድ ሳምንት ያህል ለሁሉም የከተማዋ ነዋሪ የነፃ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተገልጿል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
ምንጭ፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
December 2, 2020 at 3:40 am #16840AnonymousInactiveየሽሮ ሜዳ – ቁስቋም የአስፋልት መንገድ ግንባታ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል
የመንገድ ፕሮጀክቱ ፊዚካል አፈፃፀም ከ85 በመቶ በላይ ደርሷል
አዲስ አበባ (አአከመባ) – የሽሮ ሜዳ – ቁስቋም የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን (አአከመባ) አስታወቀ።
የሽሮ ሜዳ – ቁስቋም መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ገብረ እግዚአብሔር ሐጎስ እንደገለፁት፥ የመንገድ ፕሮጀክቱ የቀኝ መስመር ግንባታ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት መደረጉን ገልፀው፤ አሁን ላይ የፊዚካል አፈፃፀሙ (physical construction) ከ85 በመቶ በላይ በመድረሱ የግንባታ ሥራው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በመንገድ ፕሮጀክቱ የግራ መስመር ላይ 910 ሜትር የአስፋልት ንጣፍ የተከናወነ ሲሆን፤ 600 ሜትር የሚሆነው ቀሪው የግንባታ ክፍል ላይ ደግሞ የአፈር ቆረጣ፣ የቤዝ ኮርስ እና የድጋፍ ግንብ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በቀጣይ አጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንደሚሆን ኢንጂነር ገብረ እግዚአብሔር ጨምረው ተናግረዋል።
የሽሮ ሜዳ – ቁስቋም መንገድ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ክፍል 1.4 ኪ.ሜ ርዝመትና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 30 ሜትር የጐን ስፋት አለው። የመንገድ ፕሮጀክቱን በ160.9 ሚሊዮን ብር ወጪ ዮቴክ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማ እየገነባው ሲሆን፤ የማማከርና የቁጥጥር ሥራው ደግሞ ቤስት ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ኃ/የተ/የግ/ማ እያከናወነው ይገኛል።
በተመሳሳይ ከ600 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ሁለተኛው ክፍል በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የራስ ኃይል ተከናውኖ ለትራፊክ ክፍት የተደረገ ሲሆን፤ ለግንባታ ወጪውም ከ53.3 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል። አሁን ላይ ያልተጠናቀቁ የእግረኛና የማስተካከያ ሥራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ አጠቃላይ የመንገድ ግንባታ ሥራውን ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ እንዲጠናቀቅና የወሰን ማስከበር ሥራዎችን እና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሠራ ቆይቷል።
የመንገዱ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ነዋሪዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ፋይዳ ከመስጠቱም ባሻገር ወደ እንጦጦ ፖርክ እና አካባቢው ለሚንቀሳቀሱ የከተማዋ ነዋሪዎችና ቱሪስቶች ምቹና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበርክታል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ አበባ ከተማን የተመለከቱ ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች
ምንጭ፦ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.