Home › Forums › Semonegna Stories › አድዋ – የጥቁሮች ሕዝቦች የነጻነት እርሾ
Tagged: Global alliance for Justice the Ethiopian Case, በርሊን, አድዋ, አጼ ምኒልክ, የአድዋ ድል, የአድዋ ጦርነት, የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ
- This topic has 3 replies, 2 voices, and was last updated 5 years, 9 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
February 27, 2019 at 8:39 pm #9941SemonegnaKeymaster
የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ነጻነትና ኩራትን፣ በዓለም ዙሪያ በተለይ በአሜሪካዎቹ ሰፋፊ እርሻዎች ለ500 አመታት በባርነት ለተጋዙ ጥቁር ሕዝቦች ደግሞ፥ የማንነት ማረጋገጫ፣ የዘመናት ጭቆናና የስነ-ልቦና ቁስልን አውልቆ የመጣያ የተስፋ ትንሳኤ ሆኖ ነበር።
ሰለሞን ተሰራ (ኢዜአ)
በርሊን ከተማ ውስጥ የጀርመን ግዛት አስተዳዳሪ (ቻንስለር)በነበረው ኦቶ ቫን ቢስማርክ (Otto von Bismarck) መኖርያ ሳሎን ፌሽታ በፌሽታ ሆኗል። እለቱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር (እ.አ.አ) የካቲት 16 ቀን 1885 ሶስት ወር ሙሉ አሰልቺ ውይይት የተደረገበትና ዋና ዋናዎቹ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ተሰብስበው ”አንተ ይሄን ያዝ አንተ ያንን ያዝ” ተባብለው ከወታደራዊ ዘመቻ በፊት አፍሪካን የተቃረጡት።
በስብሰባው ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የአፍሪካ መሬት የሃሳብ መስመር እያሰመሩ ያለከልካይ ተከፋፈሉት። ከሦስት ወራት በላይ (እ.አ.አ ከኅዳር 15 ቀን 1884 እስከ የካቲት 26 ቀን 1885) ሲካሄድ የነበረው የበርሊን ጉባዔ (Berlin Conference) መደምደሚያ የነበረው ‘የበርሊን ጉባዔ ጠቅላላ ግብአተ ሰንድ’ (በእንግሊዝኛው፥ General Act of Berlin conference) በታሪክ አጥኚዎችና ፖለቲካ ተመራማሪዎች ዘንድ በ አብዛኛው “አፍሪካን የመቀራመት ጉባዔ” (“The Division of Africa” ወይም “Scramble of Africa”) ተብሎ ይታወቃል። በጉባዔው ላይ የጀርመን፣ ኦስትሮ-ሀንጋሪ፣ ቤልጅየም፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ጣልያን፣ ኔዘርላንድስና ፖርቱጋል ተወካዮች ተገኝተዋል።
አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት በበርሊን ስምምነት ሲያደርጉ፤ አፍሪካዊያን ደግሞ የውጭ ወራሪዎችን ለመከላከል ከዚህ አለፍ ሲልም እርስ-በርሳቸው መተነኳኮስ የጀመሩበት ጊዜ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ወቅቱ በአራቱም የአህጉሪቷ አቅጣጫዎች የሚገኙ ነገስታት እና የጭፍራ አለቆች በተናጠል ከአውሮፓውያኑ ጋር በገጠሟቸው ውጊያዎች ትርጉም ያለው ስኬት ሳያገኙ፤ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት መውደቅ የጀመሩበት ነው።
ይህን ተከትሎ ጣልያንም ኢትዮጵያን በቁጥጥሯ ስር ለማድረግ ብትነሳም እምቢተኛው ጥቁር ሕዝብ ማንነቱንና ክብሩን አሳልፎ ላለመስጠት በመወሰኑ ያልተመጣጠነ ውጊያ ቢገጥሙም አሳፍሮ መልሷታል። ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀው የጣልያን ጦር የቅኝ ግዛት ተልእኮውን እውን ለማድረግ የተመመው በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ በአግባቡ የሰለጠኑ ወታደሮችን ይዞ ነው። ነገሩ እንደታቀደው ሳይሆን ቀርቶ የጣልያን ጦር በአድዋ ድል ተነሳ። ታሪክም ይህን ጦርነት <የአድዋ ጦርነት> (The Battle of Adwa) በማለት፣ ለጥቁር ሕዝቦች ታላቅ መነቃቃትና ተስፋ የሰጠውን የጦርነቱን ድል ደግሞ <የአድዋ ድል> (The Victory of Adwa) ብሎ ሲገዝበው ይኖራል።
የታሪክ ሊቃውንት እንደሚያስቀምጡት የአድዋ ጦርነት በአፍሪካ ምድርና ታሪክ ከተከናወኑት ጦርነቶች ከፍተኛውን የዋጋና የክብር ስፍራ ይዟል። የሰሜን አፍሪካን በስፋት ይገዛ የነበረው አኒባል የአልፕን ተራሮች ዞሮ የአውሮፓን ኃያል መንግሥት ካሸነፈ ወዲህ (Hannibal’s crossing of the Alps)፣ አንድ አውሮፓዊ ጦር በአፍሪካውያን ጦር ሲሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። ስለሆነም፣ ጦርነቱ ብዙ መልክና ብዙ ቅጽል ተሰጥቶታል።
የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ነጻነትና ኩራትን፣ በዓለም ዙሪያ በተለይ በአሜሪካዎቹ ሰፋፊ እርሻዎች ለ500 አመታት በባርነት ለተጋዙ ጥቁር ሕዝቦች ደግሞ፥ የማንነት ማረጋገጫ፣ የዘመናት ጭቆናና የስነ-ልቦና ቁስልን አውልቆ የመጣያ የተስፋ ትንሳኤ ሆኖም ነበር።
የታሪክ ተመራማሪና ደራሲውፖል ሄንዝ በጻፉት ንብረ ጊዜ፥ የኢትዮጵያ ታሪክ (Layers of Time: A History of Ethiopia, by Paul B. Henze) በተሰኘው የታሪክ ድርሳናቸው “አውሮፓውያን የፈለጉትን ገድለዋል፣ ባሪያ ፈንግለዋል፣ አካባቢን፣ ሀብትን፣ ጉልበትን መዝብረዋል፤ ምክንያቱ በግልጽ ባይታወቅም ‘ኢትዮጵያን በጦር ከማስገበር ይልቅ እንቃረጣት ብለው’ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይና ጣልያን የሦስትዮሽ ስምምነት (Tripartite Agreement) ተፈራርመው አጼ ምኒልክን ‘እወቁልን’ ብለው ጦማር ሰደዋል። አጼ ምኒልክም ‘ስለነገራችሁኝ አመሰግናለሁ፣ ነገር ግን እኔ በሌለሁበት የተወሰነውን አላውቅም’ በማለታቸው ጣልያን ኢትዮጵያን በወረራ ያዘች።
ወረራውን ለመቀልበስ በአጼ ምኒልክ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ ትግል ቢያደርግም የወራሪዎቹ ብልጣብልጥነት ጦርነቱን አይቀሬ አደረገው። ወደ ጦርነት ተገዶ የገባው የኢትዮጵያ የጦር ኃይል በአምባላጌ፣ በመቀሌና በአድዋ በተከታታይ ባደረገው ጦርነት የበላይነት ወስዶ የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. ላይ በአድዋ የድል ባለቤት መሆኑ ተበሰረ። የድሉ ዜና እንደናኘ በአፍሪካ ተስፋ፣ በአውሮፓ ድንጋጤ ፈጠረ። የኢትዮጵያ ድል አውሮፓውያን በዓለም የነበራቸውን ልዕለ ኃያልነት ለመጀመሪያው ጊዜ ጥያቄ ውስጥ ከቷል። ፖል ሄንዝ ”ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው” የኢትዮጵያ ድል የአውሮፓ ተሰሚነት የቁልቁለት ጉዞ መነሻ ነበር” ሲሉ በጽሁፍ አስፍረዋል።
ድሉ ታላቋ ብሪታንያን ኢትዮጵያን በእኩል ዓይን ዓይታ ”የምስራቁን የደቡቡን የምእራቡን ድንበራችንን እንካለል” ብላ በፊርማ እንድታጸድቅ አስገድዷታል። ከዚህ በተጨማሪ በአውሮፓ ቅኝ ግዛት መዳፍ ስር ሲማቅቁ የነበሩትን አፍሪካውያን እና ካሪቢያን ጥቁሮች ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ብርታት እና ምሳሌ ሆኗቸዋል። ለጥቁር አሜሪካውያን ምሁራን ከፍተኛ የመንፈስ መነቃቃት እንዲያገኙ አድርጓል።
የአድዋ ድል (ማለትም፥ በአውሮፓውያን ዘንድ የአድዋ ጦርነት ሽንፈት) በተሸናፊ የአውሮፓ ገዢዎች ዘንድ ቁጭት ፈጥሮ ከ30 ዓመት በኋላ ፋሺዝም በጣልያን ውስጥ ስር እንዲሰድ እና መሪ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም (አይዲዮሎጂ) እንዲሆን ምክንያት ሆኗል። ለኢትዮጵያ ደግሞ የተረጋጋ መንግስታዊ አስተዳደር አስገኝቷል። በዚህ የከሸፈ የቅኝ-ግዛት ዕቅድና የአውሮፓውያን ተስፋፊነት የተደሰቱ ሶሻሊስት አመለካከት ያላቸው ወገኖች በጣልያን፣ በብሪታንያና በፈረንሣይም ነበሩ።
ዕውቁ የታሪክ ተመራማሪና የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰር የነበሩት ሪቻርድ ፓንክረስት እና ሌላው ኢትዮጵያዊ የታሪክ ተማራማሪ ዶ/ር አብዱልሳማድ አህመድ በጋራ በጻፉት ስለ አድዋ ድል በጻፉት መጽሐፍ (Adwa Victory Centenary Conference, 26 February – 2 March 1996) ውስጥ እንዳሰፈሩት የኢጣሊያኑ ክሪቲካ ሶሻሌ (Critica Sociale) ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፊሊፖ ቱራቲ (Filippo Turati) በወኔና በምልዓት ለእውነት ስለእውነት ጻፈ። “ጣልያን ወደ አድዋና ወደ ሌሎችም ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ተደረጉት ጦርነቶች የገባችው፣ ለእንግሊዛውያን አገልጋይና አሽከር ሆና ነው። በዚህም የተነሳ የጣሊያናውያን ሀብትና ደም ያላግባብ ፈሰሰ” ሲል ወረራውን በማውገዝ ድፍረት የተሞላበት ጽሁፉን ማስነበቡን ይገልጻሉ።
ጋዜጠኛው በጽሁፉ “የጣልያንና የእንግሊዝ መንግሥታት በአፍሪካ ስለተቀዳጁት የቅኝ-ግዛትና የተስፋፊነት ድል እንደጽጌረዳ የፈካ ውሸት እየፈበረኩ ይመጻደቁ እንጂ፣ በእርግጥ ኢትዮጵያ ድል አድርጋለች… ቪቫ ምኒልክ! ቪቫ ኢትዮጵያ!” ሲል አወድሷል።
በአጼ ምኒልክ መሪነት የኢትዮጵያ ኃይል በጣልያን ወራሪ ኃይል ላይ በአድዋ የተቀዳጀው ድል ድልድይ ሆኖ የጥንታዊቷን ኢትዮጵያ የታላቅነት ክብር ከዘመናዊ ዓለም ጋር ያገናኘ ድልድይ ሆኗል። ታዲያ ይህ ድልድይ በ1890ዎቹ ግንባታው የተጀመረው የተቀረው የአፍሪካ ክፍል በውጭ ኃይሎች አገዛዝ ቀንበር ስር ሲወድቅ ኢትዮጵያውያን ብቻ በተከታታይ የተሰነዘረባቸውን ወረራ በድል ሲመልሱ ነበር።
በዚያው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያውያን ለውጭ ወራሪዎች የማይንበረከኩ መሆናቸውን ማሳየታቸውን ማስታወስ ይቻላል። በ1870ዎቹ የግብፃውያንን፣ በ1880ዎቹ የመሃዲስቶችን ተደጋጋሚ ጥቃቶች መክተው መልሰዋል። የአድዋ ድል ደግሞ ይህን የነፃነት ቀናዒነት ይበልጥ ከማድመቅ አልፎ የዓለምን ትኩረት ስቧል።
የአውሮፓ መንግሥታት ዲፕሎማቶቻቸውን ወደአዲስ አበባ እንዲልኩ፣ ከኢትዮጵያ ጋር 19 ድንበርን የሚመለከቱ ስምምነቶችን እንዲፈራረሙ አደረጋቸው ። በአርነት ትግሉ መስክ በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩት እህት የአፍሪካ አገሮች ታጋዮችም ኢትዮጵያ ፋና ወጊ መብራታቸውና የራዕይ ምንጫቸው ነበረች።
የአድዋ ድል የፓን አፍሪካን ንቅናቄ መሠረት መሆኑን የኢትዮጵያውያንን የአድዋ ውሎ ከዘከሩ የታሪክ ጠበብት መካከል የዋሽንግተኑ የታሪክ ሊቅ ፕሮፌሰር ራየሞንድ ጆናስ፥ “የአድዋ ጦርነት – የአፍሪካውያን ድል በዘመነ ግዛት” (The Battle of Adwa: African Victory in the Age of Empire, by Raymond Jonas” በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡ በዚህ ጽሁፋቸው “የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን ቅኝ አገዛዝን ታግሎ መጣል እንደሚቻል ያሳየ፣ የኢትዮጵያንም ታላቅነት ያስመሰከረ” ስለመሆኑ ደጋግመው አውስተዋል።
ለዚህም ነው የናይጄሪያ ድኀረ ነፃነት የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር ናምዲ አዚኪዊ (Nnamdi Azikiwe) “ኢትዮጵያ ጥቁር ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርባት አገር ነች። በዚህ ክፍለ አህጉር ላይ የአፍሪካ ቀደምት አባቶች የመሠረቱት መንግሥት የታሪክ ዋቢ ነች። ኢትዮጵያ ከዘመን ወደ ዘመን እየተሸጋገረች ህልውናዋን ጠብቃ መኖሯ የሚደነቅና መደነቅም ያለበት ነው” በማለት የተናገሩት።
ከአድዋው ድል አርባ ዓመት በኋላ ጣልያን ቂሟን ልትወጣ ወረራ ስታካሂድ በግልጽም ይሁን በተዘዋዋሪ የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታት ከእሷ ጎን ቆመዋል። በተቃራኒው ድሉ በአፍሪካም ይሁን በተቀረው ዓለም የተቀጣጠለውን የአፍሪካዊነት የትግል ስሜት አነሳስቷል፤ እልህ አጭሯል። በአጠቃላይ መላው ጥቁር ሕዝብ፣ በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም ለፍትህ የታመኑ አውሮፓዊያን ነጮችም ለኢትዮጵያ ያላቸውን ወገናዊነት እንዲያጠናክሩ ጥርጊያውን አመቻችቷል። የነኝህም ጥረት በውጭ የነበረውን ሕዝባዊ ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ ያደላ እንዲሆን አድርጎታል። ባህላዊ እሴቶቻቸውን ያልጣሉ የአፍሪካ ምሁራን ከነበሩባቸው የአህጉሩ ከተሞች፣ ከካርቢያን ደሴቶች፣ ከጥቁር አሜሪካዊያን በኩል ተሰባስበው ወረራው ያጫረባቸውን የመጠቃት ስሜት በይፋ አንጸባርቀዋል።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለነበሩት የአፍቃሪ ኢትዮጵያዊነት እንቅስቃሴ መሪዎችም የአድዋው ድል የሞራል እርሾ ሆኗቸዋል። ከእንቅስቃሴው ግንባር ቀደም መሪዎች አንዱ ጀምስ ድዋኔ (James Mata Dwane) ግብጽና ሱዳን ውስጥ ያሉትን ክርስቲያን አፍሪካዊያን ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው መፍትሄ ይፈልጉለት ዘንድ ለአጼ ምኒልክ ደብዳቤ የፃፉት የአድዋውን ድል ተከትሎ ነበር።
ስለአድዋ ድል የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊንስተን ቸርችል “የካቲት 23 ቀን 1888 የአድዋ ጦርነት ተካሂዶ፥ ጣልያን በኢትዮጵያውያን የደረሰባት ሽንፈት ደረሰባት። (ይህም) ሌሎች ሕዝቦችን የሚነካ ሁለት ውጤቶች አስከተለ፤ አንደኛ፥ ሰሜን አፍሪካ ላይ አውሮፓዊ ክብርን ትልቅ ምች መታው። ሁለተኛ፥ በአውሮፓ ፖለቲካ ማንነት ረገድ የኢጣልያ ዋጋ ወደታች ወረደ” ብለው ጽፈዋል።
ዊንስተን ቸርችል ስለ ኢጣልያ ሽንፈትና ውጤቱ ከመጻፍ ይልቅ ስለ ኢትዮጵያ ድልና በአፍሪካና በሌሎቹ ጭቁን አገሮች ዘንድ የኢትዮጵያን ማንነት ሽቅብ መናሩን መግለጽ አልፈለጉም። ይህ ሊሆን የቻለው ምናልባትም አድዋ ላይ የተገኘው ድል ለጥቁር ሕዝቦች ከነጻነት ለመውጣት የተስፋ እርሹ በመሆኑ፣ ለአውሮፓውያኑ የቅኝ ግዛቶቻቸውን ሊያጡ የሚችሉበት ጅምር በመሆኑ ሊሆን ይችላል።
የሆነ ሆኖ አድዋ ላይ የተለኮሰው የድል ችቦ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩት የአፍሪካ አገሮች ቀንዲል ሆኗል። ለዚህም ክብር ለመስጠት 17 የአፍሪካ አገሮች የሰንደቅ ዓላማ ቀለማቸውን ከኢትዮጵያ ወስደዋል። አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የሆነው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለም ማሊ፣ ጋና፣ ካሜሩን … አገሮች በተለያየ ቅርጽ የአገራቸው መለያ ሰንደቅ አላማ እንዲሆን አድርገዋል።
Pankhurst, Richard. “”Viva Menelik!”: The Reactions of Critica Sociale to the Battle and to Italian Colonialism” In Adwa Victory Centenary Conference, 26 February – 2 March 1996, edited by Abdussamad Ahmad and Richard Pankhurst, 517-548. Addis Ababa: Institute of Ethiopian Studies, Addis Ababa University, 1998.
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
February 28, 2019 at 1:23 am #9952AnonymousInactiveተማሪዎች እና መምህራን 123ኛውን የአድዋን ድል እየዘከሩ ነው
—–‹‹3ቱ የካቲቶች›› የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ እስከ የካቲት 30 ይቆያል
የ‹መለከት አፀደ ሕጻናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት› ተማሪዎች በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር በሚገኘው በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል በመገኘት 123ኛውን የአድዋን ድል እየዘከሩ ነው፡፡
የአድዋን ድል በማስመልከትም ያዘጋጁትን ቴአትር አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ክፍል አዘጋጆች በቦታው ተገኝተው የተማሪዎቹን ጉብኝትና ቴአትር ቀረጻ አድርገዋል፡፡
ሕጻናቱ ባቀረቡት ቴአትር ላይ አገር ስለመውደድ፣ ስለፍቅር እና የፆታ እኩልነትን አስመልክተው አስተማሪ ጭብጦችን አንስተዋል፡፡
‹‹3ቱ የካቲቶች›› የተሰኘው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ እስከ የካቲት 30 ስለሚቆይ ሁላችሁም እንድትጎበኙት ተጋብዛችኋል፡፡
—————————-
አድራሻች፡- የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ ከፒያሳ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ፣ ሆስፒታሉ አካባቢ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጉለሌ ቅርንጫፍን አልፎ በሚገኘው ቅያስ 500 ሜትር ገባ ብሎ፡፡ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ
February 28, 2019 at 1:50 am #9955AnonymousInactiveኢትዮጵያ በጣሊያን ወራሪ መንግስት ለተፈፀመባት ዘግናኝ እልቂት ተገቢ ካሳ እንድትጠይቅ ጥሪ ቀረበ
—–ከ82 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ በወራሪው የኢጣሊያን መንግስት በተፈፀመባት ወረራ በግፍ ለተሰውት ንፁሃን ዜጐችና ለወደመባት ንብረት ተገቢ ካሳ ሊከፈላት እንደሚገባ የሚጠይቅ አለም አቀፍ ንቅናቄ መጀመሩ ይፋ ሆነ፡፡
አለምአቀፍ ህብረት ለፍትህ የኢትዮጵያ ጉዳይ (Global alliance for Justice the Ethiopian Case) የተባለው አለም አቀፍ ድርጅት ይፋ ያደረገው ይኸው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የየካቲት 12/1929 ዘግናኝ እልቂትን ጨምሮ ጣሊያን በአምስት ዓመቱ የወረራ ዘመን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን በግፍ የጨፈጨፈች ሲሆን ለዚህ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቷ ለኢትዮጵያ መንግስት ተገቢ ካሳ ልትከፍልና ህዝቡን በይፋ ይቅርታ ልትጠይቅ ይገባል ተብሏል፡፡
በድርጅቱ ይፋ የተደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ አገራት በተለያዩ ጊዜያት ወረራ በመፈፀም በግፍ ለጨፈጨፏቸው ንፁሀን ዜጐችና ላወደሙት ንብረት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ካሳ እየከፈሉና ህዝቡን በይፋ ይቅርታ እየጠየቁ ይገኛሉ። በደል የተፈፀመባቸው አገራትም ሊከፈላቸው የሚገባውን የካሳ መጠን በመግለጽ፣ ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ግን እስከአሁን ምንም አይነት ጥያቄ ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡
February 28, 2019 at 1:54 am #9956AnonymousInactiveለ123ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የሚደረገው ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ አስተዳደር አስታወቀ
—–123ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ምክንያት በማድረግ ለበዓሉ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ የኪነ ጥበብ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በዓሉ የአድዋ ድልን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚያስችሉ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ታስቦ ይውላል ብለዋል።
የቢሮው ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በሰጡት መግለጫ የአድዋ ድል የአባቶች ተጋድሎ መስዋዕትነት የሚዘከርበት በዓል ነው ብለዋል።
በዋዜማው በጣይቱ ሆቴል የኪነጥበብ ድግስ መዘጋጀቱም በመግለጫው ተገልጿል።
በተመሳሳይ በዋዜማው በሚኒሊክ አደባባይ የተለያዩ ትያትር ቤቶች የባህል ትሪዒቶችን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶችን ያቀርባሉ።
በዕለቱም በሚኒሊክ አደባባይ ድሉን በማስመልከት የተለያዩ መርሃግብሮች ይከናወናሉ።
በምኒሊክ አደባባይ የሚኖረው መርሃግብር ከተጠናቀቀ በኋላም ከሚኒሊክ አደባባይ እስከአድዋ ድልድይድረስ የእግር ጉዞ ይካሄዳል።
ድሉን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ በማሰብ በተጨማሪም በዕለቱ በእንጦጦ ቤተመንግስት ግብር የማብላት ስነስርዓት ይከናወናል።
ከ8 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ በመስቀል አደባባይ አንጋፋና ወጣት አርቲስቶች የተለያዩ ዝግጅቶችን እንደሚያቀርቡም ይጠበቃል።
በተያያዘም 123 የአድዋ ድል ለማሰብ የደራሼ ባህል ቡድን አባላት አዲስ አበባ ገብተዋል።
የአድዋ ድል ከ123 ዓመታት በፊት በአድዋ ተራሮች ላይ የተደረገ ኢትዮጵያውን አባቶች አውሮፓዊውን ቅኝ ገዢ ጣሊያንን መክተው የመለሱበት መሆኑ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.