በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ

Home Forums Semonegna Stories በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • Author
    Posts
  • #13752
    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአሜሪካ የግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ሴክሬታሪ በየካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ28 February 2020) የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን ስብሰባ ተከትሎ የወጣውን ጋዜጣዊ መግለጫ በከፍተኛ ቅሬታ ተመልክተውታል።

    ስብሰባው የተካሄደው ኢትዮጵያ አስቀድማ ለግብጽ፣ ለሱዳን እና ለአሜሪካ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አሳውቃ እያለ ነው።

    የግድቡ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነቱ መሰረት የግድቡን ሙሌት ከግንባታው ትይዩ በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች መሠረት የምታከናውን ይሆናል።

    ኢትዮጵያ የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ ለማዘጋጀት የሚደረገው ድርድር ተጠናቋል በሚል የተሰጠውን መግለጫ አትቀበልም።

    በዋሽንግተን ዲሲ የግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ ፈርሞበታል የተባለው “ረቂቅ” የሦስቱ ሀገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አይደለም። የቴክኒክ ጉዳዮች ድርድሩም ሆነ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ ላይ የሚደረገው ድርድር አልተጠናቀቀም።

    ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ የሚዘጋጀው በሶስቱ ሀገራት ብቻ እንደሆነ አቋሟን ቀድማ አሳውቃለች።

    ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን በሚያውቁት እና በተስማሙበት እንዲሁም በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መርህ አንቀጽ ስምንት አድናቆታቸውን በሰጡት ሂደት መሠረት ሁሉንም የግድብ ደህንነት የሚመለከቱ ጉዳዮች በዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ምክረ ሃሳብ መሰረት የተሰጡትን ምክረ-ሃሳቦች መፈጸሟን ትቀጥላለች።

    የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብን ለማዘጋጀት ቀሪ መሰረታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ኢትዮጵያ ከግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ እና ከሱዳን ሪፐብሊክ ጋር የጀመረችውን ሂደት ለመቀጠል ቁርጠኛ ናት።

    ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ፥ የኢትዮጵያ መንግስት ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ብሔራዊ ጥቅምን የሚነካ ድርድር እንደማያደርግ የሚስትሮች ም/ቤት አስታወቀ።

    ታላቁ የሕዳሴ ግድብን የሚመለከት ማንኛውም ነገር የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ ብቻ እንደሚከናወን የሚስትሮች ምክር ቤት ገልጿል።

    ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ብሔራዊ ጥቅምን የሚነካ ድርድር የኢትዮጵያ መንግስት እንደማያደርግ አስታውቋል።

    በዛሬው ዕለት ባካሄደው 80ኛ መደበኛ ስብሰባው ምክር ቤቱ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ስራዎችን የሚከታተል ስድስት አባላት ያሉት ብሔራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ማቋቋምን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

    የብሔራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴው ስድስቱ አባላትም የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊ ሞገስ እና የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ናቸው።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Ethiopian government's statement regarding the negotiations on GERD የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

    #15343
    Semonegna
    Keymaster

    ዓባይ ወንዝ የእኔም፣ የአንተም፣ የአንቺም፣ የእኛም የሁላችም ነው!!

    ኢትዮጵያ በተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች የተቸረች ውብ ሀገር ብትሆንም ለበርካታ ዘመናት በራሷ የተፈጥሮ ሀብት ከመልማትና ከመጠቀም ይልቅ የበይ ተመልካች ሆና በድህነት አረንቋ ውስጥ እንድትኖር የተፈረደባት መሆኑን በድፍረት መጥቀስ ይቻላል።

    የቅኝ ገዥ ሀገራት ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ላይ ዋነኛ ተጠቃሚ ለመሆን ከፍተኛ ጉጉት ያሳደሩ በመሆኑ ከጉያዋ ፈልቆ በሚፈሰው ሃብት ላይ አንዲት ብርጭቆ ውሃ እንዳትጠቀምና እንዳትለማ የሚያደርግ፣ የተጠቃሚነት መብቷን የጣሰና የከለከለ፣ በቅኝ ግዢ አስገዳጅ ውሎች አማካኝነት ባላመነችበትና ባልተሳተፈችበት ጉዳይ በወንዙ ላይ ተጠቃሚ እንዳትሆን ሲደረግ እንደነበር በማስረጃነት ማንሳት ይቻላል።

    በተለይ በወንዙ ላይ የተደረጉ ስምምነቶችን ስንመለከት የግብጽና የሱዳንን ስም ይያዝ እንጂ በዋናነት የቅኝ ገዢዎች የእጅ አዙር ተጠቃሚነትን ታላሚ ያደረገ መሆኑ ግልፅ ነው። ይህም ሲባል የቅኝ ገዥ ሀገራት በዓባይ ወንዝ (Nile River) ዙሪያ ሲያከናውኗው የነበሩት ስምምነቶች የራሳቸውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ከማጎልበት የመነጨ እንጂ ለቅኝ ተገዥ ሀገራት ጥቅም ሲባል የተደረገ አይደለም።

    ግብፅና ሱዳን የእንግሊዝ ቅኝ ተገዢ ሀገራት ቢሆኑም በወንዙ ላይ ያላቸውን ተጠቃሚነት ስንመለከት ከፍተኛውን ድርሻ እንግሊዝ ከቅኝ ግዛት በኋላ ደግሞ ግብፅ ቀጥሎ ሱዳን ብቻ እንደነበሩ ስንመለከት፥ ተካሄዱ የተባሉት ስምምነቶች ሁሉ ምን ያህል አግላይና ከልካይ እንደነበሩ ከመጠቆሙም በላይ ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ሀብት እንዳትጠቀምና እንዳትለማ ይደረግ የነበረውን ሴራ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።

    ለዚህም እንደማሳያ በዓባይ ወንዝና ገባሮቹ ላይ እ.ኤ.አ ከ1891 እስከ 1959 ድረስ የተከናወኑ የተለያዩ ስምምነቶችን ማንሳት ይቻላል። እ.ኤ.አ በ1891 በጣልያንና በእንግሊዝ የተደረገው ስምምነት ይዘትም ጣልያን ኤርትራን በያዘችበት ወቅት በአትባራ ወይም ተከዜ ወንዝ ላይ የግብፅን ጥቅም ላለመንካት ሲባል ግድብ እንደማትሠራ ከእንግሊዝ ጋር የተዋዋለችበት መሆኑ የሚታወቅ ነው።

    ሌላው እ.ኤ.አ በ1901 ከደቡባዊ አስመራ ተነስቶ አትባራ ወንዝን የሚገብርና በመጨረሻም ወደ ዓባይ ወንዝ የሚቀላቀል ጋሽ/መረብ ወንዝን በማስመልከት በእንግሊዝና በጣልያን መካከል የተከናወነ ሲሆን፥ ይዘቱም ኤርትራ በመልካም የጉርብትና መርህ ላይ ተመሥርታ በወንዙ ላይ የመጠቀም መብት እንዳላት እውቅና የሚሰጥ በመሆኑ ከሌሎች የቅኝ ገዢዎች ስምምነቶች በተሻለ ሁኔታ ፍትሀዊና የአሁኗ ኤርትራን መብት የማይጎዳ ነው ተብሎ ይታሰባል።

    እ.ኤ.አ በ1902 የሱዳን ቅኝ ገዥ በነበረችው በእንግሊዝ እና በኢትዮጵያ መካከል የተከናወነ ስምምነት እንደነበር ይጠቀሳል። በዚህ ስምምነት ላይ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ውሃውን የሚያስቀር ግድብ መሥራት እንደማትችል ይጥቀስ እንጂ፥ ውሃውን ገድባ መጠቀም እንደማትችል የሚገልፅ አይደለም። በዚህ ስምምነት ላይ ግብፆች እንደሚያነሱት እርባና-ቢስ ክርክር ሳይሆን የስምምነቱ ይዘት የሚለው ውሃውን ይዞ ማስቀረት (‘arrest’ ወይም ‘block’ ማድረግ) ወይም ሙሉ በሙሉ ማስቆም እንደማይቻል እንጂ ከማንኛውም የተጠቃሚነት ዓይነት የሚከለክል ስምምነት አለመሆኑ እሙን ነው። ይህም አሁን ሃገሪቱ እየተከተለችው ላለው ፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን የሚያጎላ ስምምነት ነው ማለት ይቻላል።

    በተጨማሪም እ.ኤ.አ የ1906 የቤልጂየም እና የእንግሊዝ ስምምነት ማንሳት ይቻላል። በዚህ ስምነት ላይ ቤልጂየም (ኮንጎን በመወከል) እና በእንግሊዝ መካከል የተከናወነ ሲሆን የኮንጎ መንግሥት ከሰምሊኪ (Semliki River) ወይም ከልሳንጎ ወንዝ (lsango River)ወደ አልበርት ሀይቅ (Lake Albert) የሚወርደውን ውሃ ከሱዳን መንግሥት ጋር ሳይስማማ ውሃውን የሚቀንስ ሥራ ለመሥራት ለማንም ፈቃድ እንዳይሰጥ የሚል ነበር።

    ሌላው እ.ኤ.አ በ1929 በእንግሊዝ እና በግብፅ መካካል የተከናወነውን ስምምነት ስንመለከት ደግሞ፥ ሱዳንን የተወሰነ ድርሻ ብቻ እንዲሰጣት በማድረግ ግብጽ እና እንግሊዝ ብቻቸውን የናይል ወንዝ (ዓባይ ወንዝ) ተጠቃሚ እንደሆኑ በተለይም ግብፅ ዓባይ ወንዝ ላይ በብቸኝነት የመወሰንና ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን (veto power) እንዳላትና ካለምንም ጣልቃ ገብነት የሚቀጥል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

    እ.ኤ.አ በ1959 የተደረገው የግብጽ እና  የሱዳን ስምምነትን ስንመለከትም በዋናነት የዓባይ ወንዝ ውሃ የግብጽ እንደሆነ እውቅና የሚሰጥ ስምምነት ነበር ማለት ይቻላል። ይህም ሲባል 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለግብጽ፣ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለሱዳን በመስጠት ቀሪው 10 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር ደግሞ የአከባቢው የኢኮሎጂካዊ ሚዛን ለመጠበቅ እንዲተን በመስማማት ኢትዮጵያ አንዲት ብርጭቆ ውኃ እንኳን የምትጠቀምበት መብት ያላገኘችበት አስገራሚና አሳዛኝ ውል ነበር። ይህ ስምምነት ሌሎች ተፋሰስ ሀገራትን ያገለለና ፍፁም የሁለትዮሽ ውል ስለነበር በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደሌለው ተደጋግሞ ተገልጿል።

    እንግዲህ በዚህ የፍርደ ገምድል ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ሀብት መልማት እንዳትችልና እንዳትጠቀም የተለያዩ ጫናዎችና እገዳዎች ቢደረግም ይህን የዘመናት ቁጭት በራስ አቅም ገንብቶ እውን ለማድረግ ቆርጦ የተነሳው የአሁኑ ትውልድ ቀደም ሲል ይደረጉ የነበሩ ክልከላዎችና እገዳዎች ሳይበግሩት በራስ የገንዘብ አቅምና ጉልበት እንዲሁም እውቀት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራውን ከጀመረ እነሆ ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥሯል።

    እስካሁን በነበረው ሂደት ምንም አንኳን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ያጋጠሙት ቢሆንም፥ ያሰበውንና የጀመረውን ነገር ከዳር ሳያደርስ መተኛት የማይወደው ይህ ትውልድ ፈተናዎቹን ተቋቁሞ የዘመናት ቁጭቱን በደስታ ቀይሮ ድሃ እያሉ ለተሳለቁበትና የልማት ጥሙን ለመወጣት የድል ብሥራት ዜናውን “ሀ” ብሎ ማሰማት ጀምሯል።

    ታሪክን መሥራት ከአባቱ የወረሰው ይህ ትውልድ የአደራ ቃሉን በብርቱ ለመወጣትና ታሪክ ሠሪነቱን ዳግም በዓለም አደባባይ ለማስመስከር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕያው ምስክር እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም። በተለይም ቀጣዩ ትውልድ የዓባይ ወንዝን የዘመናት ቁጭት እንዳይወርስ “ቁጭት በእኔ ይብቃ!” በሚል ከፍተኛ ወኔ ዓባይ ወንዝን በሀገሩ ዋል አደር ብሎ ለሚሰነብትበት ማረፊያ ጎጆ ቀልሶ ዓባይ ወንዝን እንደሰው “ቤት ለእንግዳ” ብሎ “እንቦሳ እሰር” ሊባል ከጫፍ መድረሱ ዛሬም እንደጥንቱ ታሪክ ሠሪ ትውልድ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው።

    በመጨረሻም ለባዕዳን ሀገር የዘመናት ሲሳይ የነበረው የአባይ ውሃን ከ”ዓባይ ዓባይ፥ ያ’ገር ሲሳይ” የቁጭት እንጉርጉሮ ወደ “ዓባይ ዓባይ፥ የእኛም ሲሳይ” የድል ዜማነት ለመቀየር የተተባበረ ክንዳችን ዓባይ ወንዝ ላይ ለማሳረፍ የሚከለክለን አንዳችም ነገር የለምና ዛሬም እንደትናንቱ በምንችለው ነገር ሁሉ ድጋፋችን አጠናክረን በመቀጠል አዲስ ታሪክ ለመፃፍ እንነሳ በማለት ጽሁፌን በዚሁ እቋጫለሁ።

    አዎ ዓባይ ወንዝ የእኔም፣ የአንተም፣ የአንቺም፣ የእኛም በአጠቃላይ የሁላችንም ነው!!
    እንደጀምርነው እንጨርሰዋለን!!

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

    ዓባይ ወንዝ

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.