የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እንዳሳወቀው፥ የተጠናቀቁ የባቡር ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ለማስገባት የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር ጉልህ ችግር መፍጠሩንና፣ እየተከናወኑ ባሉ ፕሮጀክቶችና ታላላቅ ተግባራት ላይ መስተጓጎልን አስከትሏል።
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የተጠናቀቁ የባቡር ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ለማስገባት የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር እክል መፍጠሩን የኢትዮዽ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ ችግሩ ኮርፖሬሽኑ ለመሠረተ ልማት የሚያስፈልገውን ክፍያ ባለመፈጸሙ የተፈጠረ መሆኑን ገልጿል።
በቱርኩ ሥራ ተቋራጭ ያፒ መርኬዚ እየተሠራ ያለውና ግንባታው ከ97 በመቶ በላይ የደረሰው የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት እየተጠናቀቀ ቢሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ የሙከራ ጉዞ ለማድረግ አለመቻሉን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ደረጃ ገለጻ ያለቁት ፕሮጀክቶች ወደሥራ ቢገቡ ወደ ጅቡቲ ወደብ በሚደረገው ጉዞ የሚወስደውን ጊዜ ከ50 በመቶ በላይ በመቀነስ የወጪ ገቢ ንግድን ያቀላጥፋሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን የባቡር መስመሩ የሚያልፍበት አካባቢ ኅብረተሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከፍ ይላል። ስለዚህም የኤሌክትሪክ ችግር ቶሎ እልባት ቢያገኝ መልካም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው እንዳሉት፥ ድርጅታቸው መሠረተ ልማቱን ዘርግቶ ኃይል የማቅረብ ሥራ ይሠራል። ለመሠረተ ልማት ዝርጋታው የሚያስፈልገው ወጪ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይሉን በሚፈልገው ድርጅት የሚሸፈን ይሆናል። የኢትዮጵያ ምድር ባቡርም ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚሆነውን ክፍያ ባለመፈጸሙ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊያገኝ አለመቻሉን አቶ ሞገስ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ግን ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የበጀት እጥረት ሲገጥመው በመጨረሻ ያመጣው ሃሳብ እንጂ የቀድሞ አሠራሩ እንዲህ አልነበረም ብለዋል።
እንደ አቶ ደረጀ ገለጻ፥ ‘በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ውሃ ስትፈልግ ከለገዳዲ ጀምረህ መስመር አትዘረጋም፤ ራሱ ድርጅቱ መሠረተ ልማቱን ይሰራልሃል። የኤሌክትሪክ ኃይልም ከዚህ የተለየ አይደለም፤ የመሠረተ ልማት ዝርጋታውንም ሆነ የኃይል አቅርቦቱን የሚያከናውነው ራሱ ነው’ ብለዋል።
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን / ኢቢሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦