በ65 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስገነባው ስካይላይት ሆቴል ተመረቀ

Home Forums Semonegna Stories በ65 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስገነባው ስካይላይት ሆቴል ተመረቀ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #9361
    Semonegna
    Keymaster

     

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ አየር መንገድ 65 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በሚደርስ ወጪ ያስገነባውና ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀው ስካይላይት ሆቴል እሁድ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ታላላቅ ባልስልጣናት እና የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመረቀ።

    በአጠቃላይ 40 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ስካይላይት ሆቴል (መደበኛ ስሙ፦ የኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል/ Ethiopian Skylight Hotel) ለሦስት ዓመታት ያህል የግንባታው ሥራ አቭዬሽን ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ኦፍ ቻይና (Aviation Industry Corporation of China) በተባለ ድርጅት ሲከናወን የቆየ ሲሆን፥ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የባለ 5 ኮከብ ደረጃን ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

    ሆቴሉ በመላው ዓለም የሚገኙ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡና በአዲስ አበባ የሚያልፉ ትራንዚተሮችን ከማስተናገድ ረገድ ትልቁን ድርሻ እንደሚወጣ ተገልጿል።

    Ethiopian Skylight Hotel – A new entrant to Ethiopia’s ever-growing hotel and hospitality industry

    ስካይላይት ሆቴል ከመደበኛ የመኝታ ክፍሎች እስከ ፕሬዝዳንታዊ ክፍሎች (presidential suites) የሚደርሱ በአጠቃላይ 373 የማረፊያ ክፍሎች፣ አራት ደረጃቸውን የጠበቁ ምግብ ቤቶች ሬስቶራንቶች (የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ ቤት፣ የቻይና ሬስቶራንት፣ ዓለምአቀፍ ሬስቶራንት፣ ወዘተ)፣ ደረጃውን የጠበቀየመዋኛ ገንዳ፣ 2000 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ለስብሰባ ወይም ለተመሳሳይ አገልግሎቶች የሚውል የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ሌሎች አነስተኛ የውይይት አዳራሾች እና ሌሎችም ዘርፈ-ብዙ የሆቴል አገልግሎቶችን ያሟላ ነው። ሆቴሉ ሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረት ሰጥታ እየሠራችበት ያለውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪን ይበልጥ እንደሚያግዝም ታምኖበታል።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ እኤአ በ2025 በዓለምአቀፍ ደረጃ እጅግ ተወዳዳሪ አየር መንገድ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካት መሰል የሆቴል ግንባታዎች ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን በአየር መንገዱ የመሠረተ ልማት ክፍል ኃላፊ አቶ አብርሃም ተስፋዬ ለዋልታ ሚዲያ ተናግረዋል።

    ጥር 19 ተመርቆ ወደ ሥራ የሚገባው የቱሪዝም ኮንፌረንሱን በማገዝም የጎላ አስተዋፅዖ አለው ተብሏል። ስካይላይት ሆቴልን መቀመጫነቱን ቻይና ውስጥ ሸንዘን ከተማ (Shenzhen) ያደረገው ግራንድ ስካይላይት ሆቴል ማኔጅመንት (Grand Skylight Hotel Management) የተባለ የሆቴልና ሆስፒታሊቲ ድርጅት እንደሚያስተዳድረው ተጠቁሟል።

    ከዚህ ጋር በተያያዘ በዚሁ ዕለት (ጥር 19) አየር መንገዱ የአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ላይ ሲያስገነባ የነበረው የማስፋፊያ ፕሮጀችትን እንደሚያስመረቅም አስታውቋል። እ.ኤ.አ. በ2018 መገባደጃ ላይ የዱባይ ኤርፖርትን በመብለጥ ወደ አፍሪካ ያለውን ከፍተኛ የመንገደኞች ፍሰት ያስተናገደው የአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አሁን የሚመረቀው ማስፋፊያ ሲታከልበት ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት እምነት ተጥሎበታል። አዲሱ ማስፋፊያ በ74,000 ስኩዌር ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን አሁን ኤርፖርቱ ማስተናገድ የሚችለውን የመንገደኛ ብዛት ከ8.5 ሚሊዮን ወደ 22 ሚሊዮን ከፍ ያደርገዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ስካይላይት ሆቴል


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.