Home › Forums › Semonegna Stories › የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያጋጠመው አደጋ (የተከሰከሰው አውሮፕላን)
Tagged: BlackBox, ET302, ሳህለወርቅ ዘውዴ, ቦይንግ 737-8, ተወልደ ገብረማርያም, የኢትዮጵያ አየር መንገድ
- This topic has 5 replies, 2 voices, and was last updated 5 years, 10 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
March 10, 2019 at 3:22 pm #10157SemonegnaKeymaster
በአደጋው የሁሉም ህይወት (157 ሰዎች) ያለፈ ሲሆን፥ ከተሳፋሪዎቹ መካከል 32ቱ ኬኒያዊያን ሲሆኑ፤ 17ቱ ኢትዮጵያዊያን ቀሪዎቹ ደግሞ የሌሎች አገራት ዜጎች መሆናቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በዛሬው ዕለት የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተሳፋሪዎች በሙሉ ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።
ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ (ኬንያ) ሲጓዝ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ ላይ የተከሰከሰው የበረራ ቁጥር ET302 የሆነው ቦይንግ 737 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የ33 አገራት 149 መንገደኞችና ስምንት የበረራ አስተናጋጆችን ይዞ ነበር።
ከተሳፋሪዎቹ መካከል 32ቱ ኬኒያዊያን ሲሆኑ፤ 17ቱ ኢትዮጵያዊያን ቀሪዎቹ ደግሞ የሌሎች አገራት ዜጎች መሆናቸውን አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታውቋል።
አውሮፕላኑ አደጋው የደረሰበት ዛሬ ማለዳ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በተነሳ በስድስት ደቂቃ ልዩነት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የአደጋው መንስዔ እስካሁን አልታወቀም።
በአደጋው የሁሉም ህይወት (157 ሰዎች) ያለፈ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በአደጋው የተሰማውን ሀዘን በመግለጽ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ተመኝቷል።
“የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 በረራ ዛሬ ጠዋት ከአዲስ አበባ ተነሥቶ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ይበር በነበረው አውሮፕላን በደረሰው የመከስከስ አደጋ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ሁሉ የጠ/ሚር ጽ/ቤት በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ስም ኀዘኑን ይገልጻል።” የኢትዮጵያ ተቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሰፈረው።
በተመሳሳይ የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በአደጋው የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ለአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦች የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ እያለ አደጋ አጋጥሞት የመከስከሱን ዜና በከፍተኛ ድንጋጤና መሪር ሀዘን እንደሰሙ ገልጸዋል።
“ፈጣሪ አምላክ በቸርነቱ ለቤተሰቦቻቸው በሙሉ፣ ከብዙ በጥቂቱ ናይሮቢ ለማውቃቸው ለካፒቴን ያሬድ ወላጆች፣ ዶ/ር ጌታቸውና ዶ/ር ራያን፣ ለሆስተስ ሣራ ባለቤትና ሕጻን ልጆቿ፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ላየኋት የጂቡቲዋ ራሻ ቤተስብ… መጽናናትን ይስጥልን። ዛሬ በ157 ሟች ቤተሰቦች ላይ የወደቀው መሪር ሐዘን እኔና ቤተሰቤ ኮሞሮስ በደረሰው አደጋ ያየነው በመሆኑ የሚያሳልፉትን ከባድ ፈተና ከማንም በላይ እረዳዋለሁ። 149 መንገደኞችና 8 የበረራ ሠራተኞችን ይዞ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲግዋዝ የነበረው [ET 302] በረራ ላይ በደረሰው የመከስከስ አደጋ በውስጡ የነበሩት ኢትዮጵያውያንና የ33 አገሮች ዜጎች ሕይወት ማለፍ ልቤን ሰንጥቆታል፤ እጅግ በጣም ነው ያዘንኩት።” ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት።
“ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ትልቅ የሀዘን ቀን ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቷ “በዜጎቻችንና ሌሎች የአየር መንገዱ ደንበኛ መንገደኞች ላይ በደረሰው አደጋ ልቤ ተሰብሯል” ብለዋል። በአደጋው ተጎጂ ለሆኑ ቤተሰቦች ፣ ወዳጅ ዘመዶችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል።
በተመሳሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 አውሮፕላን አደጋ ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገልጾ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ላጡ መፅናናትን ተመኝቷል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርም (ኢህአዴግ) እንዲሁ በአደጋው የተሰማውን ሀዘን በመግለጽ የሟች ወገኖች ነፍስ በአፀደ ገነት እንዲያርፍ ፣ ለወዳጅ ዘመድ ቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መፅናናትን ተመኝቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ በደረሰው አደጋ የሰው ሕይወት በመጥፋቱ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል። አውሮፕላኑ ምንም ዓይነት ቴክኒካዊ ችግር እንዳልነበረበትም አመልክቷል።
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በሰጡት መግለጫ፤ በአውሮፕላኑ መከስከስ የመንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ሕይወት በማለፉ ከፍተኛ ሃዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል። ህይወታቸው ያለፉት ቤተሰቦችና ወገኖች ማስተናገጃ በአዲስ አበባ እና በናይሮቢ ቢሮ መከፈቱን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ 1ሺ 200 ሰዓታትን የበረራ ሰዓት ያስመዘገበው አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ለበረራ የተነሳው 2 ሰዓት ከ38 ደቂቃ ሲሆን፤ 2 ሰዓት ከ40 ላይ ችግር እንዳጋጠመውና ከራዳር እይታ ውጪ እንደሆነም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ ከተረከበው አራት ወር የሆነው ቦይንግ 737 ወደ ኬንያ የሚያደርገወን ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ከጆሃንስበርግ ደቡብ አፍሪካ ተመልሶ ለሦስት ሰዓት ያህል አርፏል።
ይሄው በዋና አብራሪ ካፒቴን ያሬድ ሙሉጌታ ወደ ኬንያ እየተጓዘ የነበረው አውሮፕላን፤ ቀደም ብሎ በተካሄደ የቴክኒክ ፍተሻ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልነበረበት አመልክተዋል። ረዳት አብራሪው አህመድ ኑር መሃመድ ኑር የሚባል ሲሆን፤ ከ200 ሰዓታት በላይ መብረሩም ተገልጿል።
የአደጋው መንሰኤ አለማቀፍ የአቬሽን ሕግን በተከተለ መልኩ ዓለምአቀፍ ምርመራ ተካሂዶ ዝርዝር መረጃው ወደፊት እንደሚገለጽ አመልክተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
March 11, 2019 at 1:35 am #10170AnonymousInactiveምክር ቤቱ ያወጀው ብሄራዊ የሀዘን ቀን ተጀምሯል
—–የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ብሄራዊ የሃዘን ቀን እንዲሆን ማወጁን ተከትሎ ብሄራዊ የሀዘን ቀኑ ተጀምሯል።
ምክር ቤቱ ብሄራዊ የሀዘን ቀኑን ያወጀው ዛሬ ንብረትነቱ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 አውሮፕላን ተከስክሶ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተክትሎ ነው።
የምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሐገር ዜጎች ዛሬ የአንድ ቀን ብሄራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅ በሰንደቅ አላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001/ በአዋጅ ቁጥር 863/2006 እንደተሻሻለ አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ (2) መሰረት መወሰኑን አስታውቋል።
ስለሆነም የሪፐብሊኩ ሰንደቅ አላማ በዛሬው እለት በመላው የአገሪቱ ግዛቶች፣ በኢትዮጵያ መርከቦች እና በውጭ ሐገር በሚገኙ ኤምባሲዋች የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ዝቅ ብሎ የሚውለበለብ ይሆናል።
ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ
March 11, 2019 at 1:36 am #10171AnonymousInactiveየኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቹ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኑን አስታወቀ
—–የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቹን በሙሉ ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫው ነው አውሮፕላኖቹን ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ ማስወጣቱን ያስታወቀው።
አየር መንገዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰውም በትናንትናው እለት ቦይንግ 737-8 ማክስ በበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የደረሰበትን የመከስከስ አደጋ ተከትሎ መሆኑንም አስታውቋል።
በዚህም መሰረት የአደጋው መንስኤ ተጣርቶ እስኪታወቅ ድረስ ለመንገደኞች ደህንነትና ጥንቃቄ ሲባል ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቹን በሙሉ ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኑን ገልጿል።
አየር መንገዱ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አምስት አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፥ በትናንትናው እለት የተከሰከሰውም ከአራት ወራት በፊት የተረከበው 4ኛው አውሮፕላኑ ነበር።
በተመሳሳይ ዜና ቻይናም በሀገሯ የሚገኙ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቿ በሙሉ ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኗም ተነግሯል።
የቻይና የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የቻይናን አየር መንገዶች ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖችን ለበረራ መጠቀም እንዲያቆሙ አስታውቋል።
ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኘው አውሮፕላን ባለፉት አምስት ወራት የመከስከስ አደጋ ሲያጋጥመው የትናንቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ከአምስት ወራት በፊት ላዮን ኤየር የተሰኘ የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ተመሳሳይ ሞዴል አውሮፕላን ለበረራ በተነሳ በደቂቃዎች ውስጥ ተከስክሶ 189 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ
March 11, 2019 at 1:39 am #10172AnonymousInactiveአየር መንገዱ በአደጋው ማዘኑንና ለተጎጂ ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ
—–የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፕላን መከስከስ አደጋው ማዘኑንና ለተጎጂ ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ።
አደጋውን አስመልክቶ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳብራሩት አውሮፕላኑ ከጠዋት 2 ሰዓት ከ38 ደቂቃ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ቢነሳም ከስድስት ደቂቃ በኋላ ከራዳር ውጪ ሆኗል።
አውሮፕላኑ 149 ተሳፋሪዎችንና ስምንት የበረራ ሰራተኞችን ይዞ ሲጓዝ በነበረበት ወቅት በቢሾፍቱና ሞጆ መካከል በምትገኘው ኤጄሪ አካባቢ መከስከሱን ነው ያስረዱት።
አየር መንገዱ ቦይንግ 737 የተሰኘውን ይህን አውሮፕላን ከአራት ወራት በፊት መረከቡን ገልፀው ከአውሮፕላኑ አዲስነት በተጨማሪ በበረራው የተሳተፉት አብራሪውና ረዳቱ ልምድ ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ ባለፈው ወር ምርመራ እንደተደረገለትና ከደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከበረራ የተመለሰ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከጆሃንስበርግ መልስ ለሶስት ሰዓታት እረፍት ማድረጉንና በዚህም ወቅት የቴክኒክ ምርመራ ተደርጎለት እንደነበርም ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።
ይሁንና የአውሮፕላኑ አብራሪው ችግር ገጥሞት እንደነበር ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አሳውቆ እንደነበር ነው አቶ ተወልደ የተናገሩት።
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተወልደ በአደጋው 32 ኬኒያውያን፣ 18 ካናዳዊያን፣ 17 ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም የሌሎች አገራት ዜጎች ተሳፍረው እንደነበር ነው የገለፁት ።
አየር መንገዱ ለሟች ቤተሰቦች የሚችለውን እንደሚያደርግ የተናገሩት አቶ ተወልደ ለመንገደኞችና ለሰራተኞቹ ቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶች መፅናናትን ተመኝተዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ
March 16, 2019 at 2:17 am #10247AnonymousInactiveየአውሮፕላን አደጋ መንስኤውን የሚመረምር ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራ ጀመረ
—–የትራንስፖርት ሚኒስቴር እሁድ መጋቢት 1/2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመከስከስ አደጋ ያጋጠመውንና ለ157 ሰዎች ሕልፈት ምክንያት የሆነውን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የአደጋ መንስኤ የሚያጣራ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ስራ ገብቷል።
በትራንስፖርት ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ በ ICAO Anex-13 መሰረት የአውሮፕላን አደጋ መንስኤውን የሚመረምር ኮሚቴ አዋቅሮ ስራ ጀምሯል።
በዛሬው እለትም የአደጋውን መንስኤ በማጣራት ሂደቱ ከሚስሳተፉ አባላት ውስጥ የNational transport safety board of America የምርመራ ቡድን አባላት አዲስ አበባ ገብተዋል።
ምንጭ፥ የትራንስፖርት ሚኒስቴር
March 16, 2019 at 6:07 pm #10282AnonymousInactive«ጥቁሩ ሰንዱቅ» [BlackBox] ለምን ፈረንሳይ ተላከ?
—–ከእሑዱ አሳዛኝ የአየር መንገድ አደጋ ጋር በተያያዘ ጥቁሩ የመረጃ ሰንዱቅ ከሁለት ቀናት በኋላ መገኘቱ ይታወሳል። ትናንት ደግሞ ለምርመራ ወደ ፈረንሳይ መላኩ ተዘግቧል። ለመሆኑ ለምን ፈረንሳይ ተመረጠች? ለምን የጥቁር ሰንዱቁን መረጃ ለሌላ አገር አሳልፈን እንሰጣለን? ቦይንግ ለምን የመረጃ ሰንዱቁን ለመመርመር ፍላጎት አሳየ? የአብራሪዎች ሚና በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ምን ይመስላል? በነዚህ ቁልፍ ጥያቄዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ለሁለት ዐሥርታት አብራሪዎችን የማስተማር ልምድ ያላቸውን ካፒቴን አማረ ገብረሃናን አነጋግረናቸዋል። ካፒቴን አማረ በአየር ኃይል ከ26 ዓመት በላይ ሠርተዋል። በሲቪል አቪየሽን የፍላይት ሴፍቲ ዲፓርትመንትን ደግሞ በዳይሬክተርነት ለ14 ዓመት መርተዋል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ8ዓመት በበረራ ትምህርት ቤት አስተምረዋል። አሁን በአቢሲኒያ በረራ ምክትል ኃላፊ ናቸው።
ጥቁሩን የመረጃ ሰንዱቅ በተመለከተ
ጥቁሩ ሰንዱቅ ሁለት ቅንጣት አለው። አንዱ ፍላይት ዳታ ሪኮርደር ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ኮክፒት ቮይስ ሪኮደር ነው። እነዚህ ሁለቱ በአደጋ ጊዜም ሆነ በሌላ ተፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ቁልፍ መረጃዎችን ይዘው የሚቆዩና አስፈላጊ ሆነው በሚገኙበት ጊዜ ደግሞ መረጃው ተገልብጦ ጥቅም ላይ ማዋል እንዲቻል ሆነው የተሠሩ ናቸው። -
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.