ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

Home Forums Semonegna Stories ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

Tagged: 

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #12198
    Semonegna
    Keymaster

    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
    የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍትህ እና ነፃነት ጥያቄ በግድየለሽነት በሚንቀሳቀሱ ሰዎችና ተግባራቸው እንዳይጠለፍ ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል!

    የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲ ሥርዓት ይገባናል በሚል ሁሉንም አገዛዞች ሲታገል የቆየ ሕዝብ መሆኑ ሃቅ ነው። በዘመናዊት ኢትዮጵያ እንኳን ፍትሃዊ እና የሁሉንም ዜጎች ነፃነት የሚያከብር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል በትግል የተገኙ አራት ዕድሎች መክነውብናል። ይህ የአምባገነን ሥርዓቶች እና የዜጎች አልገዛም ባይነት እና እምቢተኝነት ትንቅንቅ የሚቋጨው ሕዝብ እውነተኛ የሥልጣን ምንጭ ሆኖ የሚመርጠው እና የሚቆጣጠረው መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው።

    የሩቁን ትተን በ2007 ዓ.ም. እንኳን ብናይ፣ በሙሉ ድምጽ ተመርጫለሁ ብሎ ፓርላማውን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረዉ ገዢ ቡድን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ስብርብሩ የወጣው በዜጎች የጋለ የዴሞክራሲ ጥያቄ እና የተባበረ ትግል ነው።

    ይህ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተባበረ ክንድ የተሰበረ አምባገነናዊ አሠራርና አስተሳሰብ መልክ እና ቅርፁን በመቀያየር የተገኘውን የለውጥ ጭላንጭል ድርግም አድርጎ በማጥፋት ጥለነዉ ወደመጣነዉ ጨለማና ወደራሱ የአገዛዝ አቅጣጫ ሊጠልፈው እንደተዘጋጀ ከበቂ በላይ ምልክቶችን አይተናል።የኢትዮጵያን ሕዝብ ትዕግስት፣ አስተዋይነት እና አርቆ አሳቢነት የመረዳት ችሎታ ያነሳቸው ጥቂት ፅንፈኞች ሀገራችን የምትጠብቀውን ተስፋ ሊነጥቋትና እነሱም አጥፍተው ሊጠፉ የተዘጋጁ ይመስላል። በእንደዚህ ዓይነት አቅላቸውን በሳቱ የአገዛዝ ቡድኖች እጅ መውደቅ ለአገራችን የመጀመሪያ ባይሆንም ይህ አሁን የገጠመን አጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት መቆምን እና መታገልን የሚያሻ መሆኑን ማሳሰብ እንወዳለን። በተደጋጋሚ እንዳልነው አሁን ያገኘነውን ዕድል በአግባቡ ተጠቅመን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ሀገራዊ መረጋጋት በእጅጉ የሚያስፈልገን ወቅት ላይ እንገኛለን። ከዚህ በተፃራሪ የአንድ ወገን አሸናፊነት ተረክ መፍጠር ያገኘነውን ዕድል አደጋ ላይ የሚጥል እና ለማንም የማይጠቅም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን መረዳት ይገባል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንሸጋገርበትን መደላድል ለመፍጠር ሰላም እና መረጋት ለማስፈንና ተቋማትን ነጻ እና ገለልተኛ ለማድረግ የበኩሉን እየተወጣ ቢሆንም በገዢው ፓርቲ ውስጥም ይሁን ከዚያ ውጪ ለውጡ የጋራ ትግል ውጤት መሆኑን የዘነጉ ቡድኖች የሚሠሩትን ነውረኛ አካሄድ በማየት በሚከተሉት 7 ነጥቦች ላይ ያለውን አቋም ይገልጻል።

    1. የአማራ እና የቅማንት ሕዝብ ብዙ መከራዎችን በጋራ ያሳለፈ ድንበር የሌለው አንድ ሕዝብ ዛሬ በአስተዳደር ወሰን እና በማንነት ጉዳዮች የሚነሱ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን የሚያስተናግደው በክፋት በተዋቀረው ፌደራላዊ አሠራር መሆኑን ተገንዝበን ለዘላቂ ሰላም እና ለሕዝብ አብሮ መኖር በትዕግስት እንድንሠራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ግጭቶች ባሉበት አካባቢ የሚኖረውም ሕዝብ፤ በመሀከሉ ያለውን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እና ሰላሙን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ እኩይ ኃይሎች ሰለባ እንዳይሆን በሕዝባችን አንድነት ስም እንማጸናለን።
    2. ኢሕአዴግ በጌታ እና ሎሌ አደረጃጀት የተዋቀረ ከዚህም ሲያልፍ መንግሥትነት የሚያስገኘውን የሥልጣን ጥቅም በመቀራመት ጎን ለጎን ሲጓተቱ የነበሩ ቡድኖች ስብስብ መሆኑን ለምናውቅ ሁሉ የዛሬው እሽኮለሌ አያስደንቀንም። ሆኖም ግን ሕዝባችንን በእነሱ ጦስ ወደእልቂት ለመክተት የሚያደርጉትን የትንኮሳ አካሄድ እንዲያቆሙ በኢሕአዴግ ውስጥ የተሰባሰቡ የብሔር ድርጅቶችን በጥብቅ እናሳስባለን።
    3. የተቋማትን መኖር እና መጠንከር አስፈላጊ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ውስጥ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክንውኖች ከፖለቲካ ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጥ ቢሆንም ከሰሞኑ በተለይም የኦዴፓ አደረጃጀት የሰላም፣ የይቅርታ እና የምስጋና ታላቅ በዓል የሆነውን ኢሬቻን መጥለፉ ሳያንስ የተለመደውን የ100/150 ዓመት የሠባሪ/ተሠባሪ ትርክት ማቀንቀኑ ሀገሪቱን ወደ አንድነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ የሚጎትት እና የሚበርዝ በመሆኑ እንዲህ ዓይነትቱ ትርክት በአስቸኳይ እንዲታረም አንጠይቃለን። የሀገር አንድነትንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማምጣት ሂደት የምንጠቀምበት ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን።

    በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ የአዲስ አበባ ሕዝብ አዲስ አበባ ለተከበረው ኢሬቻ በዓል ከየቦታው የመጡ የበዓሉ ታዳሚ ኢትዮጵያዊያንን በመንከባከብ ላሳየው አብሮነት እና ወገናዊ ፍቅር እንዲሁም በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ላሳየው ትዕግስት ያለንን አክብሮት እና ምስጋና እየገለጽን ወደፊትም ለሀገር ሰላም እና መረጋጋት እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲታገል የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡

    1. የአዲስ አበባ ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን አፈና እስካሁን በሆደሰፊነት ማለፉ ሊያስመሰግነው ቢገባም ይህን ያልተረዱ ወገኖች ትዕግስቱን እንደፍርሀት፤ ጨዋነቱን እንደ የዋህነት እየወሰዱ ማኅበረሰቡን መተንኮስ እየተለመደ መጥቷል። ይህ የሀገራችንን ሁሉንም ሕዝብ አቅፎ የያዘ፤ ከዚያም በላይ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማእከል የሆነና ለፌደራል መንግሥቱም ከፍተኛ የሆነ የግብር ገቢ የሚያስገኝ ከተማን በጥንቃቄና በአክብሮት፤ የሚገባውን መብት አክብሮ መያዝ ይገባል። የከተማው ሕዝብ ተፈጥሮአዊ የሆነና በሕገ መንግሥቱም እውቅና የተሰጠውን ራሱን የማስተዳደር መብት ለመሸርሸር የሚደረግ ምንም ዓይነት አካሄድን አይቀበልም። ይህንን መብቱን በዘላቂነት ለማስጠበቅም ራሱን ከቀበሌ ጀምሮ በሁሉም ያስተዳደር እርከን በጠንካራ ሁኔታ አደራጅቶ የራሱን መብት ለማስከበርና የራሱን መሪዎች ለመምረጥ መዘጋጀት ይጠበቅበታል። ኢዜማ ይህንን ራስን የማስተዳደር እንቅስቃሴውን እውን ለማድረግ ከከተማው ሕዝብ ጋር አብሮ ይሠራል፤ የከተማውን ሕዝብም ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ በዜግነቱና በከተማ ነዋሪነቱ ያደራጃል። ከዚህም በተጨማሪ የሚደርስበትን የመብት ጥሰት ለመቃወምና ተቃውሞውንም በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ የሚያደርጋቸውን ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች እንደግፋለን፤ በሥነ ሥርዓት እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በጠበቀና ሀገራዊ አንድነታችንን በሚያጎለብት ሁኔታ እንዲካሄድም ጥሪ እናስተላልፋለን።
    2. በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ያስተዋወቀው አዲስ የደንብ ልብስ ለከተማ የፖሊስ አገልግሎት የሚመች ባለመሆኑ ጥቅም ላይ እንዳይውል አጥብቀን እናሳስባለን። የከተማዋ ፖሊስ በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እንዲሁም በኮሚኒቲ ፖሊስ ደረጃ የተዋቀረ አደረጃጀት እያለው እና የፌደራል ፖሊስ ኃይል በቋሚነት በሚገኝበት ከተማ ውስጥ ተጨማሪ ቋሚ ተወርዋሪ ኃይል ማቋቋም ተቀባይነት የለውም። ይልቁንም የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ የከተማዋን ኅብረተሰብ ደኅንነት ማስጠበቅ እና አባላቱ የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል። በክልሎች የተደራጀው ልዩ ኃይል እና አዲስ አበባ አስተዳደር አቋቋምኩት ያለው ቋሚ ተወርዋሪ ኃይል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ለሚደረገው ትግል ትልቅ ተግዳሮቶች ናቸው። ከዚህ ቀደም እንደገለጽነው እነዚህ አደረጃጀቶች ፈርሰው ወደመደበኛ ፖሊስ እና መከላከያ ሠራዊት እንዲካተቱ በድጋሚ ጥሪ እናስተላልፋለን።
    3. በአማራ ክልል የተከሰቱ የወንድማማች ሕዝብ ግጭቶች ተከትሎ ሁኔታው እንዲረጋጋና ሰላም እንዲሰፍን ከመስበክ ይልቅ ሥራዬ ብለው ወሬ እየፈበረኩ ግጭቶችን በሚያዋልዱ ሚዲያዎች ላይ የብሮድካስት ባለሥልጣን በአስቸኳይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እናሳስባለን።
    4. ላለፉት 27 አመታት ሲሰራበት የቆየው ሀገርን እና ሕዝብን ሆን ብሎ የሚከፋፍልና የሚበትን የዘረኝነት አሠራር ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም የሚቻለው ፖለቲካችንን በማዘመንና በመግራት፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ተደራጅቶ በመታገል በመሆኑ፤ ሌሎች ያደርጉልናል ብሎ ከመጠበቅ ዜጎች በተለይም ለዘብተኛ አመለካከት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በጋራ እንድናልፍ ባላችሁ አቅም ሁሉ በሀገራችሁ ጉዳይ ሙሉ ተሳታፊ እንድትሆኑ የዘወትር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    በአጠቃላይ ሰላምን፤ ሀገራዊ አንድነትንና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚያይ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን እንዲገነባ ሕዝባችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባሉ የኢዜማ አደረጃጀቶች በመግባት የጀመረውን የሰላምና የዴሞክራሲ ጉዞ ከዳር እንዲያደርስ ጥሪያችንን እያቀረብን ሌሎች የማኅበረሰብ መሪዎች ለሀገር ሰላም እና ለሕዝብ መረጋጋት ዘብ መቆም የሚገባቸው ጊዜ ዛሬ መሆኑን በአጽንዖት እንገልጻለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሀገር አንድነትን ማስቀጠል እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። አሁን ያለንበት የሽግግር ወቅት የሀገር አንድነትን እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረትን እንዲያረጋግጥ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንደምናደርግ እና አስፈላጊውን መስዕዋትነት ለመክፈልም ወደኋላ እንደማንል በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን። የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎናችን እንደሚቆም አንጠራጠርም።

    ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
    መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.