Home › Forums › Semonegna Stories › የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ የማስፈጸሚያ ሰነድ እንደሚያስፈልገው ተጠቆመ
Tagged: ቢንያም አለማየሁ, ታከለ ኡማ, የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር, የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ, ዮናስ ብርሃነ መዋ, ደሳለኝ ኃይሉ
- This topic has 2 replies, 3 voices, and was last updated 5 years, 8 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
October 14, 2018 at 7:30 am #8085SemonegnaKeymaster
በጥቅምት ወር ዓም የጸደቀው የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ የፊልም ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በአግባቡ እንዲያሳድገው ከተፈለገ የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅለት ይገባል – በሀገሪቱ ውስጥ በፊልም ሥራ ላየ እንደተሰማሩ ባለሙያዎች ማብራሪያ።
በጌትነት ተስፋማርያም (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ ዘርፉን በአግባቡ እንዲያሳድገው ከተፈለገ የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅለት እንደሚገባ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪያዎች ማህበር የቀድሞ ፕሬዚዳንት አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ እንደገለጸው፤ የዘርፉን ችግሮች ለማቃለል የሚያስችል አ ሠራር ይኖረዋል የተባለው ፖሊሲ ባለፈው ዓመት ጸድቋል። ነገር ግን ፖሊሲው ዝርዝር ጉዳዮችን የማይዝ በመሆኑ እያንዳንዱን የዘርፉን ችግሮች ሊቀርፍ የሚችል የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅ ይገባል።
እንደ አርቲስት ደሳለኝ ገለጻ፤ የፊልም ኢንዱስትሪው ለአምስት መቶ ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል መሆኑን በጥናት ተረጋግጧል። ነገር ግን እስካሁን በአግባቡ ስላልተሠራበት ውጤቱ እምብዛም ነው። ከአጠቃላይ የአገሪቷ ገቢ ውስጥ ያለው ድርሻም ዝቅተኛ ነው። የፊልም ፖሊሲው አስፈጻሚ አካል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ካለው የሰው ኃይል፣ የፊልም ጥበብ ዕውቀት ችግር እና አደረጃጀት አኳያ ዘርፉን በሚገባው ልክ እያገዘ አይደለም። በመሆኑም የፊልም ባለሙያዎች ዋነኛውን ድርሻ በመውሰድ ለፖሊሲው ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ለማውጣት ሌት ከቀን መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
የፊልም ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ መዋ በበኩሉ፤ እንደ አንድ የፊልም ባለሙያ ፖሊሲው ሲጸድቅ በኢንዱስትሪው ያሉት ችግሮች ይቀረፋሉ ብሎ እንደጠበቀ ገልጿል። ዝርዝር ጉዳዮችን ለማስተካከል እና ወጥ አሠራር ለማምጣት የማስፈጸሚያ ሰነዱ የግድ መዘጋጀት እንዳለበት ባለሙያዎች ሊገነዘቡ እንደሚገባ ተናግሯል። የማስፈጸሚያ ሰነዱንም ለማዘጋጀት የሚያስችል ቡድን ከባለድርሻ አካላት ተውጣጥቶ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን በር በየጊዜው በማንኳኳት ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ የፊልም ሠሪዎች የዘርፍ ማኀበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢንያም አለማየሁ እንደገለጸው፤ የማስፈጸሚያ ሰነዱ ቢዘጋጅ በመጀመሪያ ኢንዱስትሪው በማደጉ ተጠቃሚ የሚሆነው ባለሙያው ነው። በመሆኑም አርቲስቶች፣ ዳይሬክተሮች እና በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦች ሳይሰለቹ ለፖሊሲው የማስፈጸሚያ ሰነዱ ዝግጅት መሥራት አለባቸው። በዘርፉ ያለውን የዕውቀት፣ የገቢ እና የአሠራር እድገት ለማስመዝገብ ማስፈጸሚያ ሰነዱ ቁልፍ ሥራ መሆኑን በመረዳት ማንኛውም ባለሙያ በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባ ገልጿል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ሰላም ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ የፊልም ሠሪዎች የዘርፍ ማኅበር በጋራ ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ፊልም ፖሊሲ ትግበራ ላይ ያተኮረ ውይይት ሰሞኑን በብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አዳራሽ ማካሄዱ ይታወሳል። በውይይቱ መጨረሻ ከ20 ያላነሱ በኪነጥበቡ ላይ ተሳትፎ ያላቸው በጎፈቃደኛ ባለሙያዎች የፊልም ፖሊሲው ማስፈጸሚያ ሰነድ ለማዘጋጀት በሚደረገው ጥረት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተመርጠዋል።
እንደ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ፥ የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ በኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. መጽደቁ ይታወሳል።
በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን የፊልም ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ሙሉ ዶሴ (ፋይል) በፒ.ዲ.ኤፍ (PDF) እዚህ ጋር ያገኙታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
November 22, 2018 at 12:31 am #8634AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበርን ላለፉት ስድስት አመታት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲመራ የቆየውና በአሁኑ ሰዓት የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ሆኖ በማገልገል ላይ እሚገኘው አርቲስት ደሳለኝ ሃሉ የአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር የቦርድ አባል ሆኖ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የሹመት ደብዳቤ ተሰጥቶታል።
ደሳለኝ ሃይሉ ከዘጠኝ ወራት በፊት የፀደቀው የኢትዮጵያ ፊልም ፖሊሲ እውን እንዲሆን ከታገሉ ፊልም ባለሞያዎች መሃል አንዱ ነው።
የአርቲስቱ ሹመት በተለይም በሲኒማ ቤቶች አካባቢ በስፋት ሚታየውን ግልፅ ሌብነት ና የተጋነነ የአዳራሽ ኪራይ ያስቀረዋል ተብሎ ይታሰባል።
April 21, 2019 at 12:28 am #10707AnonymousInactiveለፊልምና ለባህል ፖሊሲዎቻችን ተፈጻሚነት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና አጋርነት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ
—–የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በባህል ቱሪዝምና ስፖርት ዘርፎች ለተሰማሩ ወጣቶች ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር በባህልና ፊልም ፖሊሲዎቻችን ዙሪያ ለወጣቶች በተደረገ ገለጻ፣ ማኅበራዊና ስነ-ምግባራዊ እሴቶቻችንን የሚያበረታቱ ባህሎቻችን በተመለከተና ወጣቶች ለስፖርታዊ ጨዋነት በሚኖራቸው አበርክቶ ዙሪያ በቀረበ የመነሻ ጽሁፍ በተደረገ ውይይት ተጠናቋል።
በውይይቱም በተለይ ለፊልምና ለባህል ፖሊሲዎቻችን ውጤታማነትና ተፈጻሚነት በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የዘርፉ ባለሞያዎች፣ ባለሀብቶች፣ ግለሰቦችና እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በጋራና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገልጿል።
ምንጭ፦ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.