Home › Forums › Semonegna Stories › የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽኖች ምርምር ምን ላይ ደረሰ?
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 9 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
March 5, 2019 at 3:12 am #10050SemonegnaKeymaster
ለመሆኑ እንቦጭን ለማስወገድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራዎች የሚሠሩ የአረም ማስወገጃ ማሽነሪዎች ምን አገልግሎት እየሰጡ ነው? አሁን ሥራ ላይ ያሉት የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽኖች ቁጥርስ ምን ያክል ነው?
ባሕር ዳር – በጣና ኃይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ አራት ማስወገጃ መንገዶች በአማራጭነት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ምክረ-ሐሳብ ይቀርባል። ከእነዚህ ማስወገጃ መንገዶች እስካሁን ሁለቱ (የሕዝብ ጉልበት እና ማሽነሪዎች) ጣና ሐይቅ ዙሪያ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ነው።
ለመሆኑ እንቦጭን ለማስወገድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራዎች የሚሠሩ የአረም ማስወገጃ ማሽነሪዎች ምን አገልግሎት እየሰጡ ነው? አሁን ሥራ ላይ ያሉት የማሽኖች ቁጥርስ ምን ያክል ነው? ስንል የአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣንን ጠየቅን።
በዚህ ወቅት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ሁለት ማሽኖች ብቻ እንደሆኑ የነገሩን በአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የጣና ሐይቅ ሥርዓተ ምኅዳር ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ዳኘው ሁለቱ ማሽኖች ካናዳና እሥራኤል ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና በአማጋ ኃላፊነቱ ተወሰነ የግል ማኅበር ድጋፍ የተገዙ ናቸው ብለዋል።
“በባሕር ዳር እና ጎንደር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) እየተዘጋጁ ያሉ የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽኖች መኖራቸውን አውቃለሁ” ያሉት አቶ መዝገቡ፥ እስካሁን ድረስ ግን ከተቋማቸው ጋር ርክክብ ፈፅመው ወደ ሥራ አለመግባታቸውን ገልጸዋል።
አብመድ የተሰሩት ማሽኖች ለምን ርክክብ ተፈፅሞ አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም ሲል ሁለቱን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አነጋግሯል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ከሙላት ኢንድስትሪያል ኢንጂነሪንግ ጋር በመተባበር የሠራው የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተገኙበት ቢመረቅም ይህ ዜና እስከሚጠናቀርበት ጊዜ ድረስ አገልግሎት አይሰጥም።
“ማሽኑ አገልግሎት ለመስጠት ምንም ዓይነት ችግር የለበትም፤ በቅርቡም ለሦስት ወራት ያክል የሙከራ ትግበራ ከተደረገ በኋላ ከሚመለከተው አካል ጋር ርክክብ ይደረጋል” ያሉት የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ የዘገየው ማሽኑን ለማንቀሳቀስ የሚሠራ ራሱን የቻለ የሰው ኃይል አደረጃጀት ባለመኖሩ ቅጥርና ምልመላ ለመፈፀም ጊዜ በመውሰዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሙላት ኢንዳስትሪያል ኢንጅነሪንግ ጋር በመተባበር ለባለሙያዎቹ ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ያስታወቁት ዶ/ር ሰይፉ ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ተግባር እንደሚገቡም ገልፀውልናል። ማሽኑን በዘላቂነት ለማስተዳደርና ሥራውን ለማስተባበር ራሱን የቻለ ተቋማዊ አደረጃጀት እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል።
በጎርጎራ ወደብ አካባቢ የሚገኘው ሌላው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአረም ማስወገጃ ማሽንም ከአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ጋር ርክክብ ያልተፈፀመበት ማሽን ነው። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ኢንጅነር ሰለሞን መስፍን “ለአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ርክክብ እንዲፈፀሙ ደብዳቤ ልከናል” ብለዋል። የተዘጋጀው ማሽን አገልግሎት ለመስጠት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ማሽኑን የሚያንቀሳቅስ የሰው ኃይል (ኦፕሬተር) ማዘጋጀት የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ድርሻ እንደሆነም አስታውቀዋል።
የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን በበኩሉ ማሽኖቹን ለመረከብና የሰው ኃይል ለመቅጠር በተግር ሲሠሩ ማየት እፈልጋለሁ ብሏል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና በሙላት ኢንድስትሪያል ኢንጅነሪንግ የተዘጋጀው ማሽን ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበትም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በዚህ ሳምንት ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ የተገዛ ሌላ የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን ጣና ሐይቅ ላይ ደርሶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ምንጭ፦ አብመድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.