የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጨምሮ የተለያዩ የክልል፣ የፌደራል እና የውጭ ሀገር ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ መርቀው ከፈቱ።
በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ንብረትነት በተገነባው በዚሁ ፋብሪካ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ የኤርትራው ፕሬዝዳንት አማካሪ የማነህ ገብረአብ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የቻይና ልማት ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ቡ ዪ እንዲሁም የደቡብ ክልል ርዕስ መስተዳደር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናትም ተገኝተዋል።
ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘው 8 ቢሊዮን ብር ብድር የተገነባው ይህ ፋብሪካ በቻይናው ቻይና ኮምፕላንት ግሩፕ ተቋራጭነት የተገነባ ሲሆን የሙከራ ምርቱን ዛሬ ይጀምራል። ፋብሪካው የሙከራ ሥራውን የሚጀምረው ከ2ሺህ እስከ 3ሺህ ቶን ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት ነው።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ መሥራት ሲጀምር በቀን ከ8 ሺህ እስከ 10 ሺህ ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም የሚኖረው ሲሆን የዓለም ገበያን ፍላጎት መሠረት በማድረግም ጥሬ ስኳር (raw sugar)፣ ነጭ ስኳር (plantation white sugar) እና የተጣራ ስኳር (refined sugar) ማምረት ይችላል። ከሁለት ወር በፊት በተደረገው ፍተሻ የፋብሪካው ማምረቻ ማሽኖች ወደ ምርት ለመሸጋገር ዝግጁ መሆናቸው ተረጋግጠዋል።
በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር በሚገኙ አራቱም ፋብሪካዎች በ100 ሺህ ሄክታር በላይ የሸንኮራ አገዳ ለማልማት የመስኖ መሠረተ ልማት ተከናውኗል፤ እስካሁንም ባለው ሂደት 30ሺህ ሄክታር መሬት የመስኖ ውሃ እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል። የመስኖ ውሃ ካገኘው መሬት ውስጥም 16ሺህ ሄክታር በሚሆነው መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ መተከሉም ተገልጿል።
ዜና፦ ቬሎሲቲ አፓረልዝ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመርያ የሆነውን የግል የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነባ ነው።
የአሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ ወደ ምርት በተሸጋገረበት በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ፋብሪካ ግንባታ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል። ግንባታውም የተከናወነው ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ነው።
ፕሮጀክቱ ወደ አገልግሎት መግባቱ በአገሪቱ ስኳር ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ፋብሪካዎችን ቁጥር ወደ ስምንት (ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፊንጫአ፣ ከሰም፣ ተንዳሆ፣ አርጆ ዲዴሳ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 እና 3) ያደርሰዋል።
በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር ከሚገነቡት አራት የስኳር ፋብሪካዎች አንዱ የሆነው ይህ ፋብሪካ፤ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የኦሞ ወንዝን በሚያዋስኑት በከፋና ቤንች ማጂ ዞኖች መሃል ይገኛል።
ኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ከተቋቋመ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ከ110 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)