በነቀምቴ ከተማ የተገነባው የወለጋ ስታድየም ተመረቀ

Home Forums Semonegna Stories በነቀምቴ ከተማ የተገነባው የወለጋ ስታድየም ተመረቀ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #10579
    Semonegna
    Keymaster

    ነቀምቴ (ሰሞነኛ) – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በኦሮሚያ ክልል፣ ምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር፣ ነቀምቴ ከተማ ውስጥ የተገነባውን የወለጋ ስታድየም መርቀው ከፈቱ። ስታዲየሙ በግንባታዉ በዓይነቱ ልዩ እና የገዳ ስርዓትን 8 ዙር ቅርፅ ይዞ የተገነባ መሆኑ ተጠቁሟል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ስታድየሙ በምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል ስፖርት መነቃቃት ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

    ”ወለጋ አገሪቱ በድርቅ በተጠቃችበት ጊዜ ሌላውን ማህበረሰብ ያስጠለለ አካባቢ ነው” ያሉት ዶ/ር አብይ፥ ”ምሥራቅ ወለጋን ማልማት ምዕራቡን የአገሪቱ ክፍል በልማትና በንግድ ማስተሳሰር ነው” ብለዋል።

    የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው አንድነትና ሕዝባዊ ትብብር ካለ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል የወለጋ ስታድየም ማሳያ ነው ብለዋል። ከእኛ አልፎ ለሌላው የምትተርፍ ኦሮሚያን ለመፍጠር ከአካባቢው ልማት መነሳት እንደሚገባ ገልጸዋል።

    የስታድየሙ ግንባታ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተሾመ ገመዳ በ1999 ዓ.ም. የተጀመረው የወለጋ ስታድየም የመንግስትን እጅ ሳይጠብቁ ሕዝብ በራሱ ተሳትፎ ፕሮጀክት ቀርፆ ሰርቶ ማስመረቅ እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። የወለጋ ስታድየም በዝቅተኛ ዋጋ በስርዓት በመገንባቱ ልዩ የሚያደርገዉ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል።

    ለስታድየሙ ግንባታ እስካሁን 196 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን በቀጣይ የወንበርና ሌሎች የማጠናቀቂያ ወጪዎችን ሲጨምር 226 ሚሊዮን ብር ወጪ ይሆንበታል ተብሎ ይገመታል። እስካሁን የህብረተሰቡ ተሳትፎ 48 ሚሊዮን ብር ለስታድየሙ ግንባታ ውሏል።

    የወለጋ ስታድየም 30 ሺህ የተመልካች ወንበሮች ያሉት ስቴድየሙ 17 የስፖርት አይነቶችን ያስተናግዳል ተብሏል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ከወለጋ ስታድየም ምርቃት መልስ ነቀምቴ ከተማ በነበሩበት ጊዜ ከከተማው እና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

    በውይይቱም ወቅት ትምህርት አጠናቀው ለሚገኙ ወጣቶች መንግስት የሥራ ዕድል እንዲፈጥርላቸው የነቀምቴ ከተማና አከባቢዋ ነዋሪዎች ጠየቁ። በውይይቱ ነዋሪዎች እንዳነሱት፤ የምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል ትልቁ ችግር የሥራ አጥነት ነው።

    የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በፌዴራል ደረጃ የመጣው ለውጥ ወደታች መውረድ እንዳለበት ገልጸዋል።

    የወለጋ ህዝብ ከለውጥ አመራሩ ጎን እንደተሰለፈ የገለጹት ተሳታፊዎቹ ለውጡን የመቀልበስ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች በመካከል በመግባት ሕዝቡን ከአመራሩ ጋር ለማጣላት እንደሚሞክሩ ጠቁመዋል።

    በፌደራል ደረጃ የታየው የሴቶች የአመራርነት መዋቅር በተለይ በነቀምቴ ከተማ እንዲሠራበት እና ሙስና እንዲቀንስ መንግስት ጠንክሮ እንዲሠራ ጠይቀዋል።

    የነቀምቴ ከተማና አከባቢዋ የሥራ አጥነት ችግር ያነሱት ነዋሪዎቹ በተለይም የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ዝግጅት እያላቸው በከተማ ጎዳና ላይ የፈሰሱት ወጣቶች መንግስት በአፋጣኝ የሥራ ዕድል እንዲፈጥርላቸው ጠይቀዋል።

    በነዋሪዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች የክልሉ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የወለጋ ስታዲየም


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.