ወልድያ (ኢዜአ)– የወልድያ ዩኒቨርሲቲ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ከሁለት ወር በኋላ መደበኛ ስርጭቱን እንደሚጀምር አስታወቀ።
የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ኪዳነ ማርያም ጌታሁን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው የአካባቢውን ሕዝብ የመረጃ ተደራሽነት ለማስፋፋት ያቋቋመው ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ (FM Radio) በጥር ወር መደበኛ ስርጭቱን ይጀምራል።
ጣቢያው በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርናና ሌሎች ዘርፎች ያተኮሩ ፕሮግራሞች ይኖሩታል ብለዋል አቶ ኪዳነ ማርያም። እንዲሁም ወቅታዊ መረጃና የመዝናኛ ፕሮግራሞች እንደሚኖሩትም ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።
የሙከራ ስርጭቱን በአምስት ባለሙያዎች እየተመራ ካለፈው ወር ጀምሮ በሙከራ ስርጭት እያስተናገደ ያለውን ጣቢያ ሙሉ በሙሉ ሥራ ለማስጀመር የ25 ባለሙያዎች ቅጥር እንደሚከናወን አክለው አሳውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኛነትና ኮሙኒኬሽን የትምህርት ክፍል ተጠሪ አቶ ብርሃኑ ደጀኔ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ሬዲዮ ጣቢያውን መክፈቱ ለአካባቢው ኅብረተሰብ መረጃ ለማድረስና ከማስተማር ባለፈ ወቅቱን ያገናዘበ ተግባር መሆኑን ይናገራሉ።
ጣቢያው የትምህርት ክፍሉ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበላቸውን 100 ተማሪዎቹን በተግባር የተፈተነ ሙያ ይዘው ለመውጣት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፤ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተቀራርቦ ለመሥራት እገዛ ያደርጋል በማለት አቶ ብርሃኑ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስርጭቱን የሚያደርገው በኤፍ ኤም 89 ነጥብ 2 መሆኑ ታውቋል።
ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተያያዘ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ በወልድያ ከተማና በዩኒቨርሲቲው ግቢ የሚፈጠረውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት የሚያግዝ “NE Global Chain” ከተባለ ኩባንያ ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ። ስምምነቱ ከፀሐይ ብርሀን የሚገኝ 50 ሜጋ ዋት ለማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት እንደሆነ ኅዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው ግቢ ሰነዱን በተፈራረሙበት ወቅት ተገልጿል። በስምምነቱ ቤሩትና ሊባኖስ የሚገኘውን ድርጅታቸውን በመወከል የተፈራረሙት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳቢስ ናሃስ ሲሆኑ በዩኒቨርሲቲው በኩል የተቋሙ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ጨምሮ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳዊት መለሰ ተገኝተዋል።
በሌላ ዜና የዩኒቨርሲቲው ዜና ደግሞ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት በራያ ቆቦ ወረዳ እየተከናወነ ያለውን የአገዳ ቆርቁርና የአቀንጭራ አረሞችን የክስተት መጠንን እንዲሁም የተቀናጀ የእንስሳት መኖ ምርት ያለበትን ደረጃ ለመለየት ባለሞያዎቹ በአርሶ አደሮች ማሳላይ መረጃ በመሠብሰብ ሂደት ላይ ናቸው።
ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ዜናዎች
ምንጮች፦ ኢዜአ እና ዩኒቨርሲቲው