Home › Forums › Semonegna Stories › የወሎ ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ ቋንቋን በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ሊያስተምር ነው
Tagged: የወሎ ዩኒቨርሲቲ, ግዕዝ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 10, 2018 at 5:26 am #7994SemonegnaKeymaster
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሚጀምረው የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት በቋንቋው የተጻፉ ሥራዎችን ወደ ሌሎች አገርኛ ቋንቋዎች በመተርጎም ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችል በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊና ሥነ ሰብእ ኮሌጅ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ተጠሪ ተናግረዋል።
ደሴ (ኢዜአ) – የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከያዝነው የትምህርት ዘመን ጀምሮ የግዕዝ ቋንቋን በመጀመሪያ ዲግሪ ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው ትምህርቱን ለመጀመር በቀረጸው ሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ዙሪያ ከምሁራንና ባለድርሻ አካላት ጋር መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ.ም ተወያይቷል።
በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊና ሥነ ሰብእ ኮሌጅ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ተጠሪ ዶክተር እንድሪስ አብይ እንዳስረዱት ግዕዝ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የላቀ ሥፍራ አለው።
ትምህርቱን ለማስጀመር አራት መምህራን የተቀጠሩ ሲሆን፣ እስከ 18 ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
ሥርዓተ ትምህርቱ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ አገር በቀል ህክምናና መድኃኒት፣ የሥነ ከዋክብት ቀመርና የቀን አቆጣጠር፣ የባህልና የህግ ሥርዓቶች ተካተውበታል።
ትምህርቱ በቋንቋው የተጻፉ ሥራዎችን ወደ ሌሎች አገርኛ ቋንቋዎች በመተርጎም ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችል ዶክተር እንድሪስ ተናግረዋል።
በቋንቋው በፍልስፍና፣ በህክምና፣ በሥነ ከዋክብትና በመሳሰሉት የዕውቀት ዘርፎች በርካታ ጽሁፎች ቢጻፉም፤ ህዝቡንም ሆነ አገሪቱን መጠቀም የሚገባቸውን ያህል አልተጠቀሙበትም። ዕውቀቱም ለሌሎች ሳይተላለፍ ለረጅም ዓመታት መቆየቱን ተጠሪው ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ትምህርት ክፍል አስተባባሪና መምህር አቶ ዘላለም ጌትነት በበኩላቸው የመጥፋት አደጋ ላይ የሚገኘውንና የዕውቀት ምንጭ የሆነውን ቋንቋ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ መስጠቱ ታሪክን ከማቆየትና እውቀትን ከማጋራት አንጻር ጠቀሜታው ጉልህ ነው ብለዋል።
ሥርዓተ ትምህርቱ በተለይ ቋንቋው ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ያለውን ቁርኝት በሚያሳይ መልኩ ቢቀረጽ የተሻለ እንደሚሆን አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህርና የሥነ ጥበባት ኮሌጅ የድህረ ምረቃ ተባባሪ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ወርቁ ”ዩኒቨርሲቲው የአገር ሃብት የሆነውን የግዕዝ ቋንቋ ለማስተማር መወሰኑ የሚያስመሰግነውና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ኃላፊነት እንዲወስዱ መነቃቃትን የሚፈጥርላቸው ነው” ብለዋል።
ግዕዝ ኢትዮጵያን የምናውቅበት የዕውቀት ምንጭ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህንን መገናኛ ብዙኃን አገራዊ ፋይዳ ያለውን የዕውቀት ዘርፍ በማስተዋወቅ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የወሎ ዩንቨርሲቲም ተማሪዎችን ካስመረቀ በኋላ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር መምከር እንዳለበትም አቶ አሰፋ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ወሎ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ መአምራን ብርሃነሕይወት እውነቱ ቋንቋው በዩኒቨርሲቲው መሰጠቱ በርካታ አገራዊ ታሪኮች፣ ቅርሶች፣ መንፈሳዊና ዓለማዊ ሥራዎች፣ ምርምርን የሚጋብዙ ሥራዎች ለማወቅና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በአዲስ መንፈስ ለማስቀጠል ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
የአብነት ተማሪዎች እንቅስቃሴ መዳከም ቋንቋውን እንዳዳከመው አውስተው፣ የወሎ ዩንቨርሲቲ የጀመረው ጥረት እንዲሳካ ቤተክርስቲያኗ ድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።ከዚህ ጋር በተያያዘ በ1999 ዓ.ም. የተመሠረተው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ የቅበላ አቅም ዘንድሮ ከ20 ሺህ በላይ ደርሷል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.