Home › Forums › Semonegna Stories › የዓለም ቲቢ ቀን “በተጠናከረ አመራር ከቲቢ ነፃ የሆነች ሀገር” በሚል መሪ ቃል ይከበራል ― የጤና ሚኒስቴር
Tagged: World TB Day, የዓለም ቲቢ ቀን
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 10 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
March 16, 2019 at 2:18 pm #10270SemonegnaKeymaster
የዘንድሮው የዓለም ቲቢ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ “ጊዜው አሁን ነው…” (It’s Time…) በሚል መሪ ቃል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ “በተጠናከረ አመራር ከቲቢ ነፃ የሆነች ሀገር” መሪ ቃል ይከበራል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር በየዓመቱ የሚከበረውን የዓለም ቲቢ ቀን በዓል ከዓመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባዔ ጋር በማቀናጀት የክልል ጤና ቢሮዎችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችንና አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር ያከብራል።
በዚህም መሠረት ዘንድሮ በዓለም ደረጃ ለ37ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ22ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም ቲቢ ቀን በዓል እና ለ14ኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባዔ “በተጠናከረ አመራር ከቲቢ ነፃ የሆነች ሀገር” በሚል መሪ ቃል በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰመራ ከተማ መጋቢት 14-15 ቀን 2011 ዓ.ም. ይከበራል።
በኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር አገልግሎት እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ መጀመሪያ ከተጀመረ አንስቶ በሁሉም ክልሎች፣ በመንግሥታዊና በተፈቀደላቸው የግል ጤና ተቋማት በነጻ በመሰጠቱ በርካታ የቲቢ ሕሙማን ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ የብዙ ዜጎችን ሕይወት ታድጓል።
እ.ኤ.አ. በ2018 የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት በኢትዮጵያ አጠቃላይ የቲቢ በሽታ ስርጭት ምጣኔ እ.ኤ.አ. በ1990 ከ100,000 ሰዎች ውስጥ 369 የቲቢ ተጠቂዎች የነበሩ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ አሽቆልቁሎ እ.ኤ.አ. በ2017 ከ100,000 ሰዎች ውስጥ 164 የቲቢ ተጠቂዎች አንደሆኑ አሳውቋል። በቲቢ በሽታ ምክንያት የሚከሰት የሞት መጠንም እ.ኤ.አ. በ1990 ከ100,000 ሰዎች ውስጥ 89 ከነበረው ወደ 24 መቀነስ ተችሏል።
አገልግሎቱን በተመለከተ ዛሬም ቢሆን ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉ በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ህይወት ሰለሞን ገልፀዋል። ወ/ሮ ህይወት በመግለጫቸው እንደተናገሩት በአገሪቱ የቲቢ በሽታ ይገኝባቸዋል ተብለው ከሚገመቱት ሰዎች 35 ከመቶ ያህሉ ወደ ሕክምና ተቋማት አለመሄድ እና የቲቢ በሽታ ታካሚዎች መድኃኒትን በሐኪም ትዕዛዝ መሠረት አለመጠቀም፣ ማቋረጥ፣ በባለሙያዎች የሚሰጥ ትዕዛዝና ክትትል ጉድለት ለመጀመሪያው ደረጃ ቲቢ በሽታ ሕክምና በጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ መድኃኒቶች የቲቢ በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን የመግደል አቅማቸውን እያሳጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
- ቲቢ በዓለም ላይ ሰዎች ከሚሞቱባቸው መንስዔዎች ዘጠነኛው ሲሆን፥ በአንድ ተሕዋስ ብቻ ከሚተላለፉ በሽታዎ ከ ኤች አይ ቪ/ኤድስ (HIV/AIDS) ቀጥሎ ሁለተኛው ገዳይ በሽታ ነው፤
- እ.ኤ.አ. በ2016 አፍሪካ ውስጥ ብቻ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች በቲቢ በሽታ ተጠቅተዋል፤ ይህም በመላው ዓለም በበሽታው ከተጠቁ ሰዎች ሩቡን ያህል ነው፤
- እ.ኤ.አ. በ2016 አፍሪካ ውስጥ ብቻ 417,000 ሰዎች፣ በመላው ዓለም ደግሞ 1.7 ሚሊዮን ሰዎች በቲቢ በሽታ ለሞት ተዳርገዋል፤
- ሰባት አገራት፥ ማለትም ህንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቻይና፣ ፊሊፒንስ፣ ፓኪስታን፣ ናይጄርያ እና ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ከሚከሰተው ቲቢ 64 በመቶው ያህሉ ይከሰትባቸዋል፤
- በኤች አይ ቪ (HIV) ለተጠቁ ሰዎች ዋነኛ ገዳይ በሽታ ቲቢ ሲሆን፥ እ.ኤ.አ. በ2016 መሠረት 40 በመቶ የሚሆኑት በኤች አይ ቪ የተጠቁ ሰዎች የሞቱት በቲቢ በሽታ ነው፤
- በየዓመቱ የቲቢ በሽታ በሁለት በመቶ እየቀነሰ ቢሆንም፥ እ.ኤ.አ. በ2020 ቲቢን ከዓለም ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ይህ በሽታ ከአራት እሰከ አምስት በመቶ ያህል በየዓመቱ መቀነስ አለበት፤
- እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2015 ድረስ በአጠቃላይ 53 ሚሊዮን ሰዎችን በሕክምና ከቲቢ በሽታ ማዳን ተችሏል፤ ከዚህ ውስጥም አፍርካ ውስጥ ብቻ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2014 ድረስ 10 ሚሊዮን ሰዎችን በሕክምና ከቲቢ በሽታ ማዳን ተችሏል፤
- እስከ 2030 ድረስ (እ.ኤ.አ.) ከዓለም ላይ የቲቢ በሽታን ማጥፋት ከዘላቂ የዕድገት አጀንዳዎች (Sustainable Development Goals) አንዱ ነው።
ምንጮች፦ የጤና ሚኒስቴር፣ የዓለም ጤና ድርጅት / ሰምነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.