Home › Forums › Semonegna Stories › የጅማ–አጋሮ–ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በተገኙበት በይፋ ተጀመረ
- This topic has 3 replies, 3 voices, and was last updated 5 years, 8 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
December 11, 2018 at 9:35 pm #8905SemonegnaKeymaster
ጅማ (ኢ.መ.ባ.)– የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በተገኙበት በይፋ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን (ኢ.መ.ባ) አስታወቀ።
የአንድን ሀገር ልማት በማፋጠን ረገድ ጉልህ ሚና ካላቸው የመሠረተ ልማት ዘርፎች አንዱ መንገድ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እና በነደፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት የዘርፉ ዋነኛ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለተግባራዊ እንቅሰቃሴው ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የመንገድ ፕሮጀክት ነባሩ መንገድ ገፅታ
- በጠባብ የአስፋልት መንገድ ደረጃ የነበረ፣
- የ50 ዓመት አገልግሎት የሰጠ፣
- በ5 ሜትር ስፋት እጅግ አስቸጋሪ የነበረው፣ እና
- ለትራፊክ እንቅስቃሴዎች ምቹ ባለመሆኑ ለአደጋ ሲያጋለጥ የነበረ መንገድ ነው።
የጅማ – አጋሮ – ዲዴሣ ወንዝ ድልድይ የመንገድ ፕሮጀክት አዲሱ መንገድ ገፅታ
- የ2ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመንገድ ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር አንድ አካል ነው፤
- የአገሪቱን ደቡብ አና ሰሜን ምዕራብ ክፍሎች ደረጃውን በጠበቀ የመንገድ መሠረተ ልማት ያስተሳስራል።
መገኛ፦ ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት – ጅማ ዞን ጅማ ከአዲስ አበባ ምዕራባዊ – ደቡብ አቅጣጫ ወሊሶን አቋርጦ በሚያልፈው አስፋልት ኮንክሪት መንገድ 360 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት።
መነሻ እና መድረሻ ፕሮጀክቱ የሚጀመረው ጅማ ከተማ ከሚገኘው “ሃኒላንድ ሆቴል” በመነሳት በዋናነት በጅማ ሰሜን – ምዕራብ አቅጣጫ አድርጐ ወደ አጋሮ እና ዴዴሣ ወንዝ ድልድይ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ከዚያም ከወንዙ እስከ መቱ ከተማ በሚዘልቀው በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኘው መንገድ ጋር ያገናኛል።
የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ኮንትራት እና ውል
የሥራ ተቋራጭ፦ ቻይና ሬል ዌይ 21ኛ ቢሮ ግሩፕ የተባለ አለም አቀፍ ድርጅት
አማካሪ ድርጅት፦ ኦሜጋ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነሪንግ እና ፕሮሜ ኮንሰልታንትስ በጋራ
የግንባታ ወጪ፦ ከ1.3 ቢሊዩን ብር በላይ
የግንባታ ጊዜ፦ 41 ወራት
የግንባታ ወጪ ሽፋን፦ የኢትዮጵያ መንግስትየጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ሁለንተናዊ ፋይዳ
ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤
የተሽከርካሪ የጉዞ ወጪና ጊዜ ይቀንሳል፤
የምርት እና የሸቀጥ ልውውጥን ያቀላጥፋል፤
የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ በማውጣት የገበያ ተደራሽነትን ያቀላጥፋል፤
የከተሞች የእርስ በርስ ትስስር ይፈጥራል፤
የጤና ፣ የትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን ተደራሽነት ያጠናክራል፤
የማኅበረሰቡን ኑሮና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል፤
ቡናን ጨምሮ በግብርና ምርቶችና በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገውን አካባቢ ተጠቃሚ ያደርጋል።ምንጭ፦ ኢ.መ.ባ. | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
February 17, 2019 at 7:42 pm #9763AnonymousInactiveበአዲስ-አዳማ የክፍያ መንገድ ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ተደረገ
—–የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በአዲስ-አዳማ የክፍያ መንገድ ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ።
በአዲስ-አዳማ የክፍያ መንገድ የተሻሻለው ታሪፍ ከየካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
ማስተካከያው በክፍያ ጣቢያና በተሽከርካሪ አይነት የተደረገ ሲሆን ከ2 እስከ 16 ኪሎ ሜትር ለተሽከርካሪ 1 እና 2 የተደረገው የዋጋ ተመን 15 ብር ነው።
የውጭ ምንዛሪ ጭማሪ መደረጉና ለጥገና የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ከውጭ የሚገቡ መሆኑ ኢንተርፕራይዙ ለታሪፍ ማሻሻያው ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡
ይሁን እንጅ የታሪፍ ማሻሻያው መንገዱ ነዳጅና ጊዜን በመቆጠብ ከሚሰጠው አገልግሎት አንፃር ተመጣጣኝና አዋጭ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድን ለማስተዳደር፣ የክፍያ መንገድ አገልግሎት ለመሥጠት፣ መንገዱን ለማስጠገንና ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎችን እንዲሰራ ኃላፊነት የተሠጠው በአዋጅ የተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው።
ምንጭ፦ ዋልታ ሚዲያ
February 28, 2019 at 1:56 am #9957AnonymousInactiveየሞጆ ሃዋሳ የፍጥነት መንገድን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው
—–በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው የተጓተተውን የሞጆ ሃዋሳ የፍጥነት መንገድን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።
ከሞጆ ተነስቶ ሀዋሳ ከተማን መዳረሻው የሚያደርገው የፈጣን መንገድ ፕሮጀክት በ2008 ዓ.ም ነበር ግንባታው የተጀመረው።
201 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን መንገድ በፍጥነት ለማጠናቀቅም በአራት ምዕራፍ በመከፋፈል ለመገንባት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።
ሆኖም የፍጥነት መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ግንባታው እየተከናወነ አለመሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በተለያየ ጊዜ ባደረገው ቅኝት መታዘብ ችሏል።
ከሞጆ መቂ፣ ከመቂ ባቱ፣ ከባቱ አርሲ ነጌሌ እና ከአርሲ ነጌሌ ሃዋሳ ለተለያዩ ተቋራጮች የተሰጠው ፕሮጀክት፥ የወሰን ማስከበር ችግር፣ በግብዓት አቅርቦትና መሰል ችግሮች ሳቢያ በፍጥነት መገንባት አለመቻሉን የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተናግረዋል።
የሞጆ መቂው የመንገዱ አንድ ምዕራፍ አሁን ላይ አፈጻጸሙ 70 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ በአንጻሩ 37 ኪሎ ሜትር ከሚረዝመው ከመቂ ባቱ መንገድ ውስጥ እስካሁን 14 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ብቻ መስራት እንደተቻለ ነው የተናገሩት።
57 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና ከባቱ አርሲ ነጌሌ ከሚደርሰው የፍጥነት መንገዱ አካልም ከ1 ነጥብ 5 በመቶ በላይ ስራውን ማከናወን አልተቻለም።
በሌሎቹ የመንገዱ አካል የተስተዋለው ችግርም በባቱ አርሲ ነጌሌ መንገድ ተደግሟል የሚሉት ዳይሬክተሩ፥ የመንገዱ ግንባታ የተደቀነበት ስጋት እንዳይቀጥል መፍትሄ ተቀምጧል ብለዋል።
ከየአካባቢው መስተዳድር ጋር ውይይት በማድረግም በቅርብ ክትትል ፈጣን መንገዱን ለማጠናቅቅ ባለስልጣኑ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
አሁን ላይም በፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም ያጋጠመውን የወሰን ማስከበርና መሰል ችግሮችን በመቅረፍ ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛልም ነው ያሉት አቶ ሳምሶን ወንድሙ።
201 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሞጆ – ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ በ14 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እየተገነባ ሲሆን በ2013 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
የመንገዱ ግንባታ የሃገሪቱን የወጪ ንግድ ከማሳለጥ ባለፈም ቀጠናዊና አህጉራዊ ትስስርን ለመፍጠር ግብ ላላት አፍሪካ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።
ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ
May 19, 2019 at 6:33 am #10915AnonymousInactiveከወሎ ሰፈር አደባባይ ጀምሮ ያለዉ መንገድ ኢትዮ ቻይና መንገድ ተብሎ ሚጠራዉ ጎዳና የሰላምና የበጎነት ጎዳና ተብሎ ሊለማ ነዉ ተባለ
ይህ የተባለዉ ዛሬ ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር ሰራተኞች፣ የአካባቢው ማህበረሰብና ተቋማት ከወሎ ሰፈር አደባባይ ጀምሮ እስከ ወንጌላዊት አደባባይ ያለዉን ጎዳና ባፀዱበት ወቅት ነዉ።
ከፅዳት ዘመቻዉ በኋላ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በፅዳቱ ለተሳተፋት ምስጋና አቅርበዉ እንደዚህ አይነት ተግባሮች ከአካባቢዉ ማህበረሰብ ጋር የጠነከረ ግንኙነት በመፍጠር አብሮነትንና ሰላምን ያጎለብታል ብለዋል።
ይህም ከወሎ ሰፈር አደባባይ ጀምሮ ያለዉ መንገድ (ኢትዮ ቻይና መንገድ) የሰላምና የበጎነት መንደር በማድረግ አበባዎችን በማልማት ፣ አረጓዴ ቦታዎችን በማልማት ፣ ማረፊያ ቦታዎችን በማዘጋጀትና ለተቸገሩ ወገኖች ከአካባቢዉ ማህበረሰብና ከበጎ አድራጊ ሰዎችና ድርጅቶች ጋር በመሆን የምግብ አቅርቦት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
ይህ የሰላምና የበጎነት መንደር ሠዎች ወደዚህ ቦታ መጥተዉ አረፍ የሚሉበትና ሠላማቸዉን አግኝተዉ የሚመለሱበት ለማድረግ የታቀደ መሆኑ ተነግሯል።
ስለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሁኔታ በቀጣይ ከማህበረሰቡ ጋር በመወያየት ወደ ተግባር ይገባል ብለዋል።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.