ታላቅ ክብር ለጋሞ ሽማግሌዎች ይሁን!

Home Forums Semonegna Stories ታላቅ ክብር ለጋሞ ሽማግሌዎች ይሁን!

  • This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years ago by Anonymous.
Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #13347
    Anonymous
    Inactive

    የጋሞ ሽማግሌዎች (የጋሞ አባቶች) መንግሥት ኖረም አልኖረ በአካባቢያቸው ላይ፤ በተለይም በገዛ ልጆቻቸው የማንም ሌላ ኢትዮጵያውን ሕይወትም ሆነ ንብረት እንደማይወድም ተንበርክከው፤ ግን ደግሞ በመንፈስ ልዕልና ከፍ ብለው አሳይተውናል።

    ታላቅ ክብር ለጋሞ ሽማግሌዎች ይሁን!
    (ያሬድ ኃይለማርያም)

    ለእውነት የቆሙ ሽማግሌዎች እጦት፣ በካድሬ እና በመንጋ ፖለቲከኛ ክፉኛ ለተመታችው አገሬ የጋሞ ሽማግሌዎች (የጋሞ አባቶች) ፍቱን መድኃኒት ናቸው። እንደ ጋሞ ሽማግሌዎች ዓይነት ቅን አሳቢ፣ የፍቅር መምህር፣ የተግባር ሰው፣ ደፋር እና ዝቅ ብለው የከፍታን ውሃ ልክ የሚያሳዩ ሽማግሌዎች ከየማህበረሰቡ ቢገኙ ከገባንበት ቅርቃር በቀላሉ ለመውጣት ዕድል ይኖረን ነበረ። በሽማግሌ እና በካድሬ መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ያልቻሉ ቀሳውስት፣ ሼኾች፣ አባገዳዎች፣ ፓስተሮች፣ መንፈሳዊ አባቶች ኮሽ ባለ ቁጥር አበል እየተከፈላቸው በየሆቴሉ ሲማማሉ እና በሕዝብ ስም እነሱ ሲታረቁ ቢውሉም መሬት ላይ ጠብ ያለ ነገር የለም።

    የአገራችን ችግር ቅን አሳቢ እና ለእውነት የወገነ፣ ያመነበትን በትክክል የሚናገር፣ ክፉን የሚያወግዝን እና ጥሩውን የሚያበረታታ እውነተኛ ሽማግሌ፣ ደፋር ምሁር፣ ሃቀኛ ፖለቲከኛ፣ ሚዛናዊ ጋዜጠኛ እና መሰሪ ያልሆነ የአገር መሪ ይፈልጋል። ለጋሞ ሽማግሌዎች እና ሽማግሌዎቹንም ለሚያከብሩት የጋሞ ወጣቶች ትልቅ ክብር አለኝ። ጥሩ ምሳሌም ሊሆኑ ይችላሉ።

    የአማራ ሽማግሌዎች ከወዴት አላችሁ? የትግራይ ሽማግሌዎች ከወዴት አላችሁ? የኦሮሞ ሽማግሌዎች እና አባገዳዎች ከወዴት አላችሁ? እነዚህን ክልሎች በተለየ ሁኔታ የምጠራው ሦስቱም ክልል ውስጥ ያለው እሳት አገሪቱን ወደ ከፋ ሁኔታ እየገፋት ያለ ስለመሰለኝ ነው። በማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት ሲፈጠር፣ ዜጎች በጠራራ ፀሀይ ሲታረዱ፣ እናት ከነልጆቿ ከቅዮዋ ተፈናቅላ ዱር ስታድር፣ ሕጻናት በነፍሰ በላዎች ታፍነው ገሚሱ ሲገደሉ፣ የዩንቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች በወሮበላ ታጣቂዎች ታፍነው ሲወሰዱ የመንግስት ክርን ቢዝል እናንተ የአገር ሽማግሌዎች የት ገባችሁ?

    የጋሞ ሽማግሌዎች (የጋሞ አባቶች) መንግሥት ኖረም አልኖረ በአካባቢያቸው ላይ፤ በተለይም በገዛ ልጆቻቸው የማንም ሌላ ኢትዮጵያውን ሕይወትም ሆነ ንብረት እንደማይወድም ተንበርክከው፤ ግን ደግሞ በመንፈስ ልዕልና ከፍ ብለው አሳይተውናል። ከዛም አልፈው ይህን ትልቅ የሽምግልና እና የፍቅር መንፈስ ይዘው ከአንድ አገሪቱ ጫፍ ወድ ሌላው ጫፍ ተጉዘዋል። መንፈሳችሁ በሌሎች ሽማግሌዎች ይደር!!

    ክብር ለጋሞ ሽማግሌዎች ይሁን!
    (ያሬድ ኃይለማርያም)

    ከጋሞ ኢትዮጵያውያን ጋር በተያያዘ የጋሞ አባቶች እና ወጣቶች ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም. “የሰላም ጉዞ” በሚል መርህ ከአርባ ምንጭ በመነሳት የተለያዩ ከተሞችን በማቋረጥ መዳረሻቸውን ጎንደር ከታማ እና የጥምቀት በዓልን አድርገው መጓዛቸውንበዚህ ሳምንት ተዘግቧል።

    በጉዞው የጋሞ አባቶች የአካባቢያቸውን ሰላም እንዴት እንዳስጠበቁ ተሞክሮዎቻቸውን ለሌሎች እንዳካፈሉ እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ተምሳሌትነትም ለሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተሞክሮነት አሳይተዋል። አባቶች በጉዞው የተለያዩ ከተሞችን ያቋረጡ ሲሆን፥ በጉዟቸው መሃል ባረፉባቸው ከተሞችም ስለ ሰላም እና አንድነት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ምክክር አድርገዋል። እንዲሁም ተማሪዎችን ስለአቃፊነት፣ ስለ ሰላምና አንድነት እንደመከሩም የጋሞ ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ ሰጥቶ ነበር።

    የሰላም ዦቹ የጋሞ አባቶች እና ወጣቶች በአዲስ አበባ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ተገኝተው የአንድነት ፓርክን የጎበኙ ሲሆን፥ የጉዞው መዳረሻ በሆነችው ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማም ከከተራ በዓል ጀምረው እስከ ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ለአራት ቀናት እንደሚቆዩ ተዘግቧል።

    የአብሮነትና የሰላም ጉዞውን ኅብረ መንጎል ሚዲያና ኦሞቲክ ጀኔራል ጠቅላላ ንግድ ድርጅት በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን፥ የጉዞውን አላማ በመደገፍ የሰላም ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የደቡብ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮዎች ለአዘጋጆች የድጋፍ ደብዳቤ ሰጥተዋቸዋል።

    ምንጮች፦ ያሬድ ኃይለማርያም እና ፋና ብሮድካስቲንግ

    የጋሞ አባቶች

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.