ዩኒሴፍ ባወጣው መግለጫ መሠረት በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለስደተኞች ህጻናት የሚሆኑ ሦስት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ፣ ባለ 41 ክፍሎች ስምንት ሁለተኛ ደረጃ እና ባለ 84 ክፍሎች አራት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ።
አዲስ አበባ (ኢዜአ)– በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እና ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ሊገነቡ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) አስታወቀ።
ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ኅዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ የሚከናወነው ”ትምህርት ቆሞ አይጠብቅም” በሚል መርህ ለትምህርት በተያዘው እና በመላው ዓለም በስደት ለሚገኙ እና ለአደጋ የተጋለጡ 12,000 የሚደርሱ ህጻናትን በትምህርት ለመደገፍ ከተያዘው የ15 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት ውስጥ እንደሆነ ታውቋል።
ሦስት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ፣ ባለ 41 ክፍሎች ስምንት ሁለተኛ ደረጃ እና ባለ 84 ክፍሎች አራት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ የሚከናወን መሆኑን መግለጫው አትቷል።
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ጊሊያን ሜልሶፕ ”ይህ ፕሮጀክት በስደተኞች መጠለያ ጣቢያና የስደተኞች ተቀባይ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ የምናደርገው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
ማንኛውም ታዳጊ በምንም አይነት ሁኔታ ቢገኝ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን ብሩህ ከሚያደርገው ትምህርት መራቅ የሌለበት መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 3600 ታዳጊዎችን በሁለተኛ ደረጃ፣ 8400 ታዳጊዎችን በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተቀብሎ የሚያስተናግድ ይሆናል። ትምህርት ቤቶቹ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2019 እና 2020 ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚገመት ተገልጿል። ትምህርት ቤቶቹ በቁሳቁስ፣ በላቦራቶሪ፣ በቤተመጽሐፍት፣ በመምህራን ቢሮዎችና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች የተሟላ እንደሚሆኑም ተነግሯል።
ዩኒሴፍ ያውጣውን መግለጫ ሙሉውን (በእንግሊዝኛ ቋንቋ) ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ተመሳሳይ ዜናዎች፦