Home › Forums › Semonegna Stories › በዩኒቨርሲቲዎች አከባቢ ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ ችግር እየተስተካከለ መሆኑ ተገለጸ
Tagged: ሒሩት ወልደማርያም, ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ, ኦባንግ ሜቶ, የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 5 years, 10 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
January 5, 2019 at 5:49 pm #9108SemonegnaKeymaster
ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አስተማማኝ ሠላም በዘለቄታ እንዲረጋገጥ ከተለያዩ ማኅበረሰብ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን፣ የሀገሪቱ አቅም በሚፈቅደው ደረጃ የተለያዩ ግብዓቶችን ማሟላትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ ችግር በአሁኑ ሰዓት እየተስተካከለ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሒሩት ወልደማርያም ገለጹ።
ዶ/ር ሒሩት ባለፈው ሳምንት ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መደበኛው የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሪያ አከባቢ በሰላማዊ ሁኔታ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን በሂደት ግን የአገራችን ለውጥ ያልተዋጠላቸው አካላት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ማዕከል በማድረግ ግጭቶችን በማስፋፋት ሠላም እንዳይኖር ታስቦ እንደ ነበር ተደርሶበታል ብለዋል።
◌ ተመሳሳይ ዜና፦ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በቂ ዝግጅት በማድረግ አዳዲስ ተማሪዎችን መቀበሉን አስታወቀ
ግጭቶቹ በግል ደረጃ በተማሪዎች ጠብ ተጀምሮ ወደ ብሔር እንዲያድግም ታስቦ እንደነበርና፥ አሁን ግን ከተለያዩ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባላት፣ ከዩኒቨርሲቲው አመራር፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከጸጥታ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ፥ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ መደበኛ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ለዚህም በዩኒቨርሲቲ ቦርድ እንዲሳተፉ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ብቁ ምዑራን መመልመላቸውን፣ ሴቶችም በጉዳዩ እንዲሳተፉ ሀምሳ በመቶ (50%) ያህሉ ሴቶች በቦርድ እንዲመረጡ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ረዘም ላለ ጊዜ ትምህርት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፥ አሁን ግን ከተለያዩ አካላት እና ከተማሪዎች ጋር በተደረገ ውይይት ከጥር 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተማሪዎቹ በመደበኛ የትምህርት ገበታቸው እንደሚገኙ ከስምምነት መደረሱን ሚኒስትሯ አክለው ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲዎች አስተማማኝ ሠላም በዘለቄታ እንዲረጋገጥ ከተለያዩ ማኅበረሰብ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን፣ የሀገሪቱ አቅም በሚፈቅደው ደረጃ የተለያዩ ግብዓቶችን ከማሟላት በተጨማሪ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ምሁራንን በመጋበዝ የተማሪ ሥነ-ልቦና ላይ በመሥራት በተማሪዎች ዘንድ የተወዳዳሪነት ስሜት እንዲፈጠር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ክብርት ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 5ኛ ዙር የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ
- የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ካምፓስ (በንሳ ዳዬ ካምፓስ) ተማሪዎችን በመቀበል በይፋ ሥራ ጀመረ
- የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ ተማሪዎች በዚህ ወር መጨረሻ ጥሪ እንደሚያደርግ አስታወቀ
- ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 1ሺህ 500 ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ ነው
- አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገነባው የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ አይጠናቀቅም
February 4, 2019 at 5:54 am #9469AnonymousInactiveየትምህርት ተቋማት የእውቀትና የምርምር መሰረት እንጂ የግጭት ማእከላት መሆን የለባቸውም – አቶ ኦባንግ ሜቶ
—–ትምህርት ቤቶች የእውቀትና የምርምር ተቋም እንጂ የግጭት ማእከላት መሆን የለባቸውም ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ ኦባንግ ሜቶ አመለከቱ።
የትምህርት ተቋማት የግጭት ማእከላት እንዳይሆኑ ለማድረግ ተማሪዎችንና የትምህርት ማህበረሰቡን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረው ሊያወያዩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መስራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ከልኡካን ቡድናቸው ጋር በመሆን ላለፉት አምስት ወራት ግጭት በተከሰተባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
”ለመተማመን እንነጋገር” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ ለኢዜአ መግለጫ የሰጡት አቶ ኦባንግ፤ ትምህርት ቤቶች የእውቀትና የምርምር ተቋም እንጂ የግጭት ማእከላት መሆን እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል።
ልኡካን ቡድኑ በሰብአዊ መብትና ጥሰት ላይ በስፋት ከህዝብና ከመንግስት ጎን በመሆን ለአምስት ወራት እየሰራ መቆየቱን ጠቁመው ተማሪዎች ለፖለቲካ ግብአትና ብሔርን መሰረት አድርገው ለሚቀሰቅሱ አካላት መጠቀሚያ መሆናቸውን እንደታዘቡ ገልጸዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት የተማሪዎች የመማሪያ ግብአት አለመሟላትና ምቹ የመማር ማስተማር ሁኔታ አለመኖር ሌላኛው የግጭት መንስኤ እንደነበርም አብራርተዋል።
ትምህርት ቤቶች የግጭት ማእከል እንዳይሆኑ ለመከላከል በትምህርት ቤቶች በመዘዋወር ከቀጣዩ የትምህርት መንፈቅ አመት ጀምሮ የማወያየት ስራ እንደሚጀምሩ ገልጸዋል።
የየአካባቢው ማህበረሰብ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተማሪዎችና መምህራን በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ምክክር እንዲያካሂዱ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከየትምህርት ቤቶቹ አስተዳደር ጋር ውይይቶችን ተከታታይነት ባለው መልኩ የማካሄድ ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በውጭ አገር ላሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግስት ወደ አገራቸው እንዲገቡ ባደረገው ጥሪ መሰረት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መስራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶና ልኡካን ቡድናቸው ወደ አገራቸው መመለሳቸው የሚታወሰ ነው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶና የስራ ባልደረቦቻቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም በተለያየ መድረክ ላይ በመገኘት ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር እያከናወኑ እንደሚገኙ ይታወቃል።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.