Home › Forums › Semonegna Stories › ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተቀሰቀሰ ረብሻ የአንድ ተማሪ ህይወት አለፈ
- This topic has 3 replies, 2 voices, and was last updated 5 years, 7 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
May 27, 2019 at 7:46 am #10954SemonegnaKeymaster
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከዓርብ ጀምሮ እስካሁን በውል ባልታወቀ ምክንያት የተቀሰቀሰው ግጭት እስከዛሬ (ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም.) ድረስ አለመረጋጋቱን ተማሪዎቹ ገልጸዋል።
ደብረ ማርቆስ (ቢቢሲ አማርኛ)– በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተፈጠረ ግጭት አንድ ተማሪ መሞቱን ተማሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ። ሟች ሰዓረ አብርሃ እንደሚባልና የሦስተኛ ዓመት የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል (economics department) ተማሪ እንደነበረ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።
በዩኒቨርስቲው ከዓርብ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ግጭት እስከዛሬ (ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም.) ድረስ አለመረጋጋቱን ተማሪዎቹ ገልጸዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደሳለው ጌትነትም በተቋሙ ከባለፈው አርብ (ግንቦት 16 ቀን) 12 ሰዓት ጀምሮ ግጭቶች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።
በዚህም አርብ ግንቦት 16 ላይ 3 ልጆች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረው ልጆቹ አሁን ሆስፒታል ይገኛሉ ብለዋል። የተጎዱት ተማሪዎች በባህር ዳር እና አዲስ አበባ ሪፈራል ተጽፎላቸው ወደዚያው መወሰዳቸውንም ጨምረው ያስረዳሉ። በግጭቱ ሁለት ተማሪዎች በድንጋይና በስለት ጉዳት እንደደረሰባቸው የዓይን እማኞቹ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በተፈጸመበት ጥቃት ምክንያት አንደኛው ተማሪ ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉንና ሌላኛው ተማሪ ደግሞ ለሕክምና እርዳታ ወደ ባህር ዳር መወሰዱን ከተማሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።
የረብሻውን ምክንያት እስካሁን ማረጋገጥ አልቻልንም ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አርብ ዕለት ተሳትፎ የነበራቸውን የተወሰኑ ልጆች ፖሊስ ተከታትሎ ከግቢ ውጭ ይዟቸው ፖሊስ ጣቢያ ስለሚገኙ ጉዳያቸው እየተጣራ ነው በማለት የግጭቱ መንስዔ ከዚያ በኋላ ተጣርቶ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ የተጠለሉ ተማሪዎች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን ትላንት የሟችን አስክሬን ለመሸኘት የተሰበሰቡ ተማሪዎችም “ትምህርቱ ይቅርብን ወደ መጣንበት መልሱን” በማለት ለዩኒቨርሲቱው ፕሬዚዳንት ጥያቄ ማቅረባቸውን ነግረውናል።
የዚህን ዜና ተጨማሪ መረጃ ቢቢሲ አማርኛ ላይ ማንበብ ይቀጥሉ።
ከዚያው ከአማራ ክልል ሳንወጣ፥ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በምዕራብ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት (አብመድ) ዘግቧል። በቀጣይም ከ967 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ለአብመድ በጻፈው ደብዳቤ እንዳመላከተው ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ከዚህ በፊት በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በኩል የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። አሁን ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች 967ሺህ 786 ብር ከወር ደመወዛቸው አዋጥተው ድጋፍ አድርገዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም በሚደረገው አገራዊ እና ክልላዊ የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት ተማሪዎችም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
ከዚህ በፊት ሠራተኞች እና ዩኒቨርሲቲው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋሙ አንድ ሚሊዮን ብር በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በኩል ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል።
ምንጮች፦ ቢቢሲ አማርኛ እና አብመድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
May 28, 2019 at 9:43 am #10968AnonymousInactiveበደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ተማሪ ሞት ምክንያት የሆነውን ድርጊት የከተማው ነዋሪዎች እና የክልሉ መንግስት አወገዙ።
—-ባሕር ዳር (አብመድ) – በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ተማሪ ሞት ምክንያት የሆነውን ድርጊት የከተማው ነዋሪዎች እና የክልሉ መንግስት አወገዙ። የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ስለ ችግሩ እና ስለ ቀጣይ የተማሪዎች ሰላም ተወያይተዋል።
ድርጊቱን ያወገዙት ተወያዮቹ ችግር ፈጣሪዎቹን በማጋለጥ ለጸጥታ አካላት እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል። እስካሁን በድርጊቱ የተጠረጠሩ ተማሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ነው በውይይቱ የተገለፀው።
ውይይቱን የተከታተለው ጋሻዬ ጌታሁን እንዳደረሰን መረጃ ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የጸጥታ ስጋት እንዳይደርስባቸው ከጎናቸዉ እንደሚሆኑ ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እሁድ ግንቦት 18/2011 ዓ.ም የአንድ ተማሪ ህይወት ሲያልፋ ሶስት ተማሪዎች ቆስለዉ በህክምና ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል። የችግሩ መንስኤ እስካሁን እንዳልታወቀም ነው ማብራሪያ የተሰጠው።
የክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና ሕዝብ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪ ላይ በደረሰዉ የሕይወት መጥፋት ከልብ ከማዘን ባሻገር ድርጊቱን አጥብቀው እንደሚያወግዙት ገልጿል።
የክልሉ መንግሥት ከሕዝቡና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ጥቃት አድራሾችን ተከታትሎ ለሕግ እንደሚያቀርብም ነው ያስታወቀው።
ለሟች ቤተሰቦች፣ ለጓደኞቹና ለዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብም መጽናናትን ተመኝቷል።
ምንጭ፦ አብመድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
May 29, 2019 at 5:26 am #10970AnonymousInactiveየዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ ዓመት ተማሪ ሆሳዕና ከተማ ውስጥ ባልታወቁ ሰዎች ተገደለ
—–ሆሳዕና (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የ2011 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን መማር-መስተማር ተግባር በሰላም እየተገባደደ ባለበት ወቅት፥ አንድ ያልተጠበቀ አሳዛኝ ክስተት ተከስቷል፡፡ ይኸውም በዩኒቨርሲቲው የምህንድስናና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የኤሌክትሪከል ምህንድስና ትምህርት ክፍል የ5ኛ ዓመት ተማሪ በሆነው ዓለሙ ባሣ ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. የደረሰው ድንገተኛ ህልፈተ ሞት ነው፡፡
በተማሪው ላይ የሞት አደጋ የደረሰው ወጣቱ ከዩኒቨርሲቲ ውጪ በሆሳዕና ከተማ ከጓደኞቹ ጋር አምሽቶ ሲመለስ በመንገድ ላይ ባጋጠመው ግጭት መሆኑ ተዉቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሆሳዕና እና የሀዲያ ዞን ፖሊስ መምሪያ፣ ዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማኀበረሰብ ባደረጉት ብርቱ የተቀናጀ ትብብርና ክትትል ሁሉም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡ ምርመራው እንደተጠናቀቀም ለፍርድ እንደሚቀርቡ እምነታችን ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ በተማሪ ዓለሙ ባሳ በደረሰው ድንገተኛ ህልፈተ ሞት ምክንያት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ስም እየገለጽን፥ ለውድ ቤተሰቦቹ፣ ለወላጅ ዘመዱና ለሚወዱት ጓደኞቹ ከፈጣሪ ዘንድ መጽናናትን እንመኛለን፡፡ እንደዚሁም በዚህ አስቸጋሪና አስደንጋጭ በሆነው ክስተት ወቅት ተማሪዎች ላሳዩት መረጋጋትና በሳል ስሜት፥ የዞንና፣ የሆሳዕና ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቶች ተጠርጣሪዎችን በማሰስና በቁጥጥር ስር በማዋል ለፈጸሙት ፖሊሳዊ ጀብድ፣ የአካባቢውና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ስላሳዩት ትኩረትና ትብብር ከልብ የመነጨ ምስጋናን ለመቅረብ እንወዳለን፡፡
ምንጭ፦ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
June 5, 2019 at 12:03 pm #11066AnonymousInactiveአክሱም ዩኒቨርሲቲ ግጭት አንድ ተማሪ ሲሞት በርካቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል
—–አክሱም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተማሪዎች መካከል የተከሰተን ግጭት ተከትሎ አንድ ተማሪ ሲገደል አስር ተማሪዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ኪሮስ ግዑሽ ከግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው የብሄር መልክ ያለው ውጥረትና ድንጋይ መወራወር መኖሩን ተናግረዋል።
ውጥረቱ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም በተፈጠረው ግጭት አንድ ተማሪ መሞቱ መነሻ ሳይሆን እንደማይቀር ጥርጣሬያቸውን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው የፀጥታ ኃይሎችን በግቢው ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ለማረጋጋት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም “አልፎ አልፎ የብሔር መልክ ያላቸው ትንንሽ ትንኮሳዎች ነበሩ” ይላሉ ዶ/ር ኪሮስ ።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአክሱም ከፍተኛ ሆስፒታል ሰራተኛ አንድ ተማሪ እንደሞተ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ባለሙያው ጨምረውም በርካታ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.