Home › Forums › Semonegna Stories › በጥናትና ምርምር በመታገዝ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን ዲላ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 3 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 12, 2018 at 4:52 am #8035SemonegnaKeymaster
አደጋ የተጋረጠበትን የቡናውን ኢንዱስትሪ በጥናትና ምርምር ታገዞ ከአደጋ መታደግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሠረታዊ ዓላማ ነው የሚሉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቃልኪዳን ነጋሽ፥ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን ሚና ለመጫወት የቡና ምርምር ማዕከል በማቋቋም በዘርፉ የአርሶ አደሩን ህይወት መቀየር የሚችል ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን ይሠራል።
ዲላ (ዲዩ) – ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ክልል ቡና አበጣሪዎች፣ አጣቢዎችና አቅራቢዎች ዘርፍ ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።
የቡና ኢንዱስትሪ በዓለም ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ዘርፍ ከመሆኑ ባሻገር ከ2.25 ቢሊዮን ሲኒ በላይ ቡና በየቀኑ እንደሚጠጣ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ ፍላጎት እየጨመረ ቢመጣም አቅርቦቱ እየቀነሰ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ለዚህም የአየር ንብረት ለውጥና ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ለምርት መቀነስ በምክንያትነት ይጠቀሳል።
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ምድር ብቻ ሳትሆን በዘርፉ የዕውቀት መሠረትም ናት። 25 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን ህዝብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ህይወቱ በቡና ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ከምታመርተው ቡና ዘጠና በመቶውን የደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ይሸፍናሉ።
የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ የነበረው ቡና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከፍተኛ የምርት መቀነስ አሳይቷል። የቡና በሽታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የእርሻ መሬት መስፋፋት፣ የደን ጭፍጨፋና ሰደድ እሳት፣ የአቅም ውስንነትና የግንዛቤ እጥረት ለቡና ምርት መቀነስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ከውሃ ቀጥሎ በብዛት የሚጠጣው ቡና በዓለም የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት በነዳጅ ብቻ ይቀደማል። በሀገራችን ደግሞ ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛል።
አደጋ የተጋረጠበትን የቡናውን ኢንዱስትሪ በጥናትና ምርምር ታገዞ ከአደጋ መታደግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሠረታዊ ዓላማ ነው የሚሉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቃልኪዳን ነጋሽ በዩኒቨርሲቲው የቡና ምርምር ማዕከል መቋቋሙ በዘርፉ የአርሶ አደሩን ህይወት መቀየር የሚችል ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን ለመሥራት ያስችለናል ብለዋል።
በጌዴኦ፣ ጉጂና ሲዳማ ዞኖች የቡና ምርታማነት መቀነስን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምሮች በመሥራት አርሶ አደሮችን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ይሠራል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በቀጣይም ዘርፉን ለማሳደግ የቡና ትምህርት ክፍል መክፈት፣ የምርምር መፅሔት ማሳተምና ለሚሰሩ ምርምሮች የበጀትና ሃሳብ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ በጌዴኦ ዞን ከ3 ሄክታር በላይ መሬት ተረክቦ የቡናን ምርት በጥራትና በመጠን ከፍለ ማድረግ የጥናትና ምርምር ሥራ መጀመሩን የተናገሩት የምርምርና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር መምህር ዳርጌ ፀጋዬ የአየር ንብረት ለውጥ፣ በሽታና ዕድሜ ለምርት መቀነስ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
የቡና ምርምር ማዕከል መቋቋሙ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያግዛል ያሉት መምህር ዳርጌ፥ በሽታን የሚቋቋሙ ምርጥ ዝርያዎችን በሳይንሳዊ መንገድ በማባዛት ያረጁና በበሽታ የተጠቃውን ቡና ለመተካት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የደቡብ ክልል ቡና አበጣሪዎች፣ አጣቢዎችና አቅራቢዎች ዘርፍ ማኅበር ፕሬዚዳንትና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባል አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ በበኩላቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው በቡና ጥራት፣ምርት መቀነስና በአባላት ተጠቃሚነት ላይ የተደቀነውን ችግር በሳይንሳዊ መንገድ መፍትሄ ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ኢንዱስትሪውን በመደገፍ የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ የጎላ ነው ያሉት አቶ ዘሪሁን በቡና ምርት ላይ ከምርት እስከ ግብይት ድረስ የሚያግጥሙ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ምርምር መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል።
የምርምር ሥራዎቹም በአዳዲስ ፈጠራ፣ በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም ከሀገሪቱ፣ ከኢንዱስትሪውና የአባላት ፍላጎት ጋር የተጣጣመ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት በተለይ በዘርፉ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ያግዛል ብለዋል አቶ ዘሪሁን።
ምንጭ፦ ዩኒቨርሲቲው
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.