Home › Forums › Semonegna Stories › የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጎበኙ
Tagged: ሳህለወርቅ ዘውዴ, አሚር አማን, የዓለም ጤና ድርጅት, ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 5 years, 11 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
February 8, 2019 at 4:37 pm #9588SemonegnaKeymaster
“በርቱ! ባየሁት ነገር ተደስቻለሁ… የሥራ ፍላጎት ተነሳሽነት ለለውጥ ወሳኝ መሆኑን ከጴጥሮስ መረዳት እንችላለን” – የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኘተው የሥራ እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በቆይታቸውም የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በጋራ ያስገነቡትን የልብ ህክምና ማዕከል፣ በሀገሪቱ ብቸኛና የመጀመሪያ የሆነውን የተመረዙ ሰዎች የሚታከሙበት የቶክሲኮሎጂ ህክምና ማዕከል እንዲሁም የእናቶችና ህጻናት የህክምና ከፍልን ዋና ዳይሬክተሩ ጎብኝተዋል።
በሆስፒታሉ ፈጣን እድገት ተደስቻለሁ ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የልብ ህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩና በሀገሪቱ ካለው የህክምና እጥረት አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸው ብዙም ትኩረት ያልተሰጠበት የመመረዝ ህክምና በሆስፒታሉ መሰጠቱም ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።
◌ ቪዲዮ፦ የኢትዮጵያዊያን-አሜሪካዊያን ዶክተሮች ቡድን እያስገነባ ያለው ግዙፉ ዓለምአቀፋዊ ሆስፒታል በአዲስ አበባ
ሆስፒታሉ የሰሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) ህክምና ብቻ ይሰጥ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ቴዎድሮስ በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ መሠረታዊ የሆስፒታል አገልግሎቶችን መስጠት መጀመሩና የተወሰኑ የህክምና አገልግሎቶች ላይም የበለጠ ስፔሻላይዝድ ለማድረግ መሥራቱ በጣም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
ከዚህ ሌላም የሆስፒታሉ ሰራተኞች የሥራ ተነሳሽነትም በጣም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። ለሆስፒታሉ ፈጣን ዕድገትም ሁሉም የሆስፒታሉ ሠራተኞች ዋና ተዋናይ መሆናቸውን እንዳዩ ገልጸው በዚህም የሥራ ፍላጎት መኖር ለለውጥ ወሳኝ መሆኑን ከጴጥሮስ መረዳት እንችላለን ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በዚሁ ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ከመጎብኘታቸው በተጨማሪም ከየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) የጤና ሚኒስትር አሚር አማን (ዶ/ር) እንዲሁም ከኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ተገናኝትው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ከሰኔ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀን ጀምሮ ዋና መቀመጫው ጄነቭ፣ ስዊዘርላንድ የሆነውን የዓለም ጤና ድርጅትን (WHO) በዋና ዳይረክተርነት የሚመሩት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከዚህ ስልጣናቸው በፊት ከ ከኅዳር 20 ቀን 2005 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከጥቅምት 2 ቀን 1998ዓ.ም. እስከ ኅዳር 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ደግሞ የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ምንጭ፦ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የካንሰር ህክምና አገልግሎት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታ 56 በመቶ ደርሷል
- ከሆዱ 120 ሚስማር የወጣለት ታካሚ መዳኑ ተገለጸ ― የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርመራ በጋራ ለማከናወን ተስማሙ
- አዳማ ከተማ ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል ተገነባ
February 10, 2019 at 4:04 am #9611AnonymousInactiveየዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በአዲስ አበባ የተለያዩ የጤና ተቋማትን ጎበኙ
—–ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻሎችን እያሳየ መምጣቱ ተገለፀ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በዛሬው እለት አዲስ አበባ የሚገኘውን የጃን ሜዳ ጤና ጣቢያ እና የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታልን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በጃን ሜዳ ጤና ጣቢያ በቤተሰብ ጤና ቡድን በጤና ጣቢያው ባለሙያዎች ቤት ለቤት እየተሰጡ ያሉ የጤና አገልግሎቶችንም በተገልጋዮቹ ቤተሰቦች ቤት በመገኘት ጎብኝተዋል፡፡
የጃንሜዳ ጤና ጣቢያ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ላላቸው ግለሰቦች ቤታቸው ድረስ በመሄድ በአይነቱ አዲስ የሆነ የህክምና ግልጋሎት የሚሰጥ ሲሆን ታካሚዎቹ ተጨማሪ ህክምና ካስፈለጋቸው ወደ ጤና ጣቢያው ሪፈር እንደሚያደርጋቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ጉብኝታቸው መደሰታቸውን የገለፁት ዶ/ር ቴዎድሮስ ሆስፒታሉ የልብ ቀዶ ህክምና መጀመሩና በመመረዝ ህክምና ዙሪያ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሆስፒታሉን እመርታ እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
“ጤና ለሁሉም” በሚለው የዓለም ጤና ድርጅት መርህ መሰረት የዓለም ጤና ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ዋናው ዳይሬክተሩ የተናገሩ ሲሆን የሀገሪቷ ከፍተኛ የጤና አመራሮች ለጤናው ዘርፍ ስርዓት መጠናከር የሰጡትን ትኩረት አድንቀዋል፡፡
ምንጭ፦ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.