Home › Forums › Semonegna Stories › ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የኮምፒዩተር ድጋፍ አደረገ
Tagged: ኬሪያ ኢብራሂም, ጂንካ, ጂንካ ዩኒቨርሲቲ, ገብሬ ይንቲሶ
- This topic has 2 replies, 2 voices, and was last updated 5 years, 11 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
December 18, 2018 at 10:17 pm #8973SemonegnaKeymaster
ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪም በሌሎች የማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው አቅዶ እየሠራ መሆኑን ተገልጿል።
ጂንካ ከተማ፣ ደቡብ ኦሞ ዞን (ሰሞነኛ) – ጂንካ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ተገንብተው በ2010 ዓ.ም. ወደ ሥራ ከገቡት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ምንም እንኳን ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎት (community-based service) በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ ለሚገኙ 18 ሁለተኛ ደረጃ እና አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በጥቅሉ ለ19 ትምህርት ቤቶች 510 ኮምፒዩተሮችን ከአንድ ደርጅት እንዲሁም በውጭ ሀገር ከሚኖር አንድ የአካባቢው ተወላጅ ጋር በመተባበር ለእያንዳንዳቸው ሃያ አምስት፣ ሃያ አምስት ኮምቲዩተሮችን ለትምህርት ቤቶቹ የሰጠ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕ/ር ገብሬ ይንቲሶ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም እነዚህ ኮምፒዩተሮች ተማሪዎቹ ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በሁሉም ኮምፒዩተሮች ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር የሚያዘጋጃቸው የመማሪያ መጽሐፍት እና ሌሎች አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ ሶፍትዌሮች የተጫኑባቸው በመሆኑ ተማሪዎቹ በቀላሉ የሚፈልጉትን ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ለICT (information, communication and technology) እና ሂሳብ መምህራን በICT አጠቃቀም ዙሪያ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ ።
ድጋፍ የተደረገላቸው ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው አዲስ የተከፈተ ቢሆንም ለየትምህርት ቤቶቹ የተደረገው ድጋፍ የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማሳለጥ አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ያሉ ሲሆን፥ በቀጣይ ትምህርት ቤቶችን በመደገፍ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ ዩኒቨርሲቲው የራሱን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት ቤቶች ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪም በሌሎች የማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው አቅዶ እየሠራ መሆኑን የገለፁት የዩኒቨርሲቲው ቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ነፃነት ይርጉ ሲሆኑ ከብት በማደለብ፣ በከብቶች ህክምና፣ በዶሮ እርባታ፣ በንብ እርባታ፣ በአሳ እርባታ በመሳሰሉት ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት አቅዶ በተግባር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል።
ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር
——
See also:- የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀበለ
- አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን አስታወቀ
- የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሠራ ነው
- የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ካምፓስ (በንሳ ዳዬ ካምፓስ) ተማሪዎችን በመቀበል በይፋ ሥራ ጀመረ
- ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 1ሺህ 500 ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ ነው
February 4, 2019 at 6:56 pm #9487AnonymousInactiveጂንካ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ላለባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አርአያ ነው — አፈ ጉባዔ ኬሪያ ኢብራሂም
—–በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ሌሎች ግጭት ላለባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አርአያ እንደሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ገለፁ።
በዞኑ ያለው ሰላምና መረጋጋት በተምሳሌትነት የሚጠቀስ መሆኑን አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ተናግረዋል።
በደቡብ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ የሚገኙ 16 ብሄረሰቦች የተሳተፉበት የባህል ፌስቲቫል ጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል።
ፌስቲቫሉ በዞኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን “ባህላዊ እሴቶች ለአብሮነትና ለልማት” በሚል መሪ ቃል ነው የተካሄደው።
አፈ ጉባዔዋ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በፌስቲቫሉ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ያለው ሰላምና መረጋጋት ለመማር ማስተማር ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ በመሆኑ ለሌሎች ግጭት ላለባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አርአያ ነው።
በርካታ ብሄረሰቦች የሚኖሩበት ዞኑ በአካባቢው ያለው ሰላምና መረጋጋት በአገር አቀፍ ደረጃ በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነውም ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የተካሄደው ፌስቲቫል በዞኑ ያለውን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ለማስተዋወቅ የሚረዳ መልካም ተግባር እንደሆነም ተናግረዋል።
እንዲሁም የዞኑን ባህልና እሴቶች ለሌሎች አካላት ለማሳወቅ የጀመራቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን አንስተዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት፤ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አካባቢያዊ ጥናትና ምርምሮች ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ አገር በቀል እውቀትን ለተማሪዎችና ለኀብረተሰቡ ለማሳወቅ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ የጀመረው ጥናትና ምርምር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው።
ዩኒቨርስቲው በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመደገፍ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ለሚማሩ ተማሪዎች በኮምፒዩተር አማካይነት የሚሰጠውን መጽሕፍ አቅርቦት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዞኑ ባህልና እሴቶች ላይ ለሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች የልህቀት ማዕከል በመሆን ማገልገል እንዳለበት ፕሮፌሰር አፈወርቅ ጠቁመዋል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ገብሬ ይምቲሶ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ብሄረሰቦች የሚያስተዋውቅ ፌስቲቫል ባለመካሄዱ የብሔረሰቦቹን ባህልና እሴት በማስተዋወቅ ረገድ የሚፈለገው ያህል አልተሰራም ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ማህረሰባዊ አገልግሎት ለኀብረተሰቡ አለመስጠቱን ተናግረዋል።
ዘንድሮ የባህል ፌስቲቫሉ ለመጀመሪያ ጊዜ መዘጋጀቱ 16ቱ ብሔረሰቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና የባህል ልውውጥ እንዲያደርጉ ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ በመሆኑ ወደፊት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚካሄድም አመልክተዋል።
የፌስቲቫሉ ዓላማ በዞኑ የሚገኙ ብሔረሰቦችን ከማቀራረብ ባሻገር ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የ16ቱን ብሔረሰቦች ቋንቋ፣ ባህልና እሴት እንዲያውቁ ማድረግ እንደሆነም ገልጸዋል።
እንዲሁም በዞኑ ግጭቶች ሳይከሰቱ የአገር አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ፕሮፌሰር ገብሬ አስረድተዋል።
በፌስቲቫሉ የዞኑ ብሔረሰቦች የምግብ፣ የሙዚቃና የዕደ-ጥበብ ስራዎች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን በባህል ብዝሃነት የሚታወቅና በበርካታ የውጭ አገር ዜጎች የሚጎበኝ አካባቢ ነው።
February 8, 2019 at 5:36 pm #9594AnonymousInactiveየጂንካ ዩኒቨርስቲ ባህላዊ እሴቶች ጉልተው እንዲወጡ የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ
—–የጂንካ ዩኒቨርስቲ ባህላዊ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ የሚያድርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጅንካ ዩኒቨርስቲ ባዘጋጀው ባህላዊ ፌስቲቫል ላይ የተገኙ ተጋባዥ እንግዶችና ታዳሚዎች ገለጹ ።
የጅንካ ዩኒቨርስቲ “ባህላዊ ዕሴቶቻችን ለአንድነታችንና ለልማታችን” በሚል መሪ ቃል በጅንካ ዩኒቨርሲቲ ደማቅ ባህላዊ ፌስቲቫል አካሂዷል፡፡
በፌስቲቫሉ የተገኙ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶችና ታዳሚዎች ለዋልታ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው እያደረገ ያለውን ባህላዊ እሴቶች የማስተዋወቅ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደለበት አንስተዋል፡፡ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ የአከባቢውን ማህበረሰብ በጥናትና ምርምር በቴክኖሎጂ በማገዝ ባህላዊ እሴቶች ይበልጥ ጎልተው የሚወጡበትን የተጠናከረ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ፕሮፌስር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው ፌስቲቫል በዞኑና አከባቢዋ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ይበልጥ ከማጠናክር አንፃር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፤ በተጨማሪም የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለአከባቢው ልዩ ትኩረት በመሥጠት እንደሚሠራ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ አክለው ገልፀዋል፡፡
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.