Home › Forums › Semonegna Stories › ጉዞ ዓድዋ ― ታላቁ የዓድዋ ድልን የሚገባው የታሪክ ማማ ላይ ለመስቀል የሚጥር ኢትዮጵያዊ ማኅበር
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 11 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
January 21, 2019 at 6:08 am #9310SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በ2006 ዓ.ም. በሰባት የየመገናኛ ብዙሃን (ሚዲያ) እና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተቋቋመው ጉዞ ዓድዋ፥ አንድ ሺሕ አስር ኪሎሜትሮችን የሚሸፍን፣ ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ተነስቶ መዳረሻውን የዓድዋ ድል አምባ ተራሮች ጫፍ ላይ የሚያደርግ ረዥም የእግር ጉዞ ነው። ላለፉት ስድስት ዓመታት ከጥር ወር ጀምሮ የዓድዋ ድል በዓል እስከ ሚከበርበት የካቲት 23 ቀን ድረስ ከስድስት ሳምንታት ላላነሰ በየዓመቱ ሳይቋረጥ የቆየው ጉዞ ዓድዋ፥ ዘንድሮ የኢትዮጵያዊነቱ ስሜት እጅግ ጎልቶ በጉዞው ላይ የሚሳተፉት ቁጥርም ጨምሯል። በዘንድሮው ጊዞ ዓድዋ 44 ተጋዦች ከአዲስ አበባ እና 4 ተጓዦች ከሐረር በአጠቃላይ 48 ተጓዦች ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀን ከአዲስ አበባ ተነስተዋል።
የመላው አፍሪቃውያን ድል እስከመባል የደረሰው ታላቁ የዓድዋ ድል፥ የግዝፈቱን ያህል ክብር እና መታወሻ ሥነሥርዐት ሳይኖረው እየተከታተለ ከመጣው ትውልድ ጋር የበዓሉ አከባበር ዐውድ እየወረደ ጭራሽ እየተዘነጋ እና እየደበዘዘ መሔድ ያሳሰባቸው የጉዞ ዓድዋ መሥራቾች ትውልዱ ትኩረት ሰጥቶ የድሉን መንፈስ እንዲጋራ ለማድረግ ይህንን የጉዞ ሐሳብ አመንጭተዋል።
◌ የጉዞ ዓድዋ ተጓዦችና የኢትዮጵያዊያን አስተያየት
በዚህም የተነሣ ጉዞ ዓድዋ ባለፉት ስድስት ዓመታት ብቻ ከታለመው ዓላማ አንጻር ከፍተኛ የሆነ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ የዓድዋ ድል በዓል ቀድሞ ከነበረበት አከባበር የላቀ ተሳትፎ ያለው የድል በዓል እንዲሆን አስተዋጽዖ ለማድረግ ተችሏል።
ጉዞውን ከማካሔድ በተጓዳኝ በየመንገዱ ተንቀሳቃሽ የመጻሕፍት ንባብ መሰናዶ በማካሔድ በየዓመቱ የሚጓዙ አባላትን በዓድዋ ጦርነት እና ድል ዙሪያ በቂ የሆነ ግንዛቤ እና ዕውቀት የማጋራት ዝግጅቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል። ከአንድ ወር በላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን የሚሰጠው የጉዞው የዕለት ተእለት ውሎ፣ በዓሉ ከመድረሱ አስቀድሞ በበርካታው ሕዝባችን ላይ የካቲት 23 ዕለትን በጉጉት የመጠበቅ ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል።
◌ የዓድዋ ድል በዓል በጎሰኞች ዓይን የዲያቆን ዳንኤል ክብረት መጣጥፍ
ከዚህ ቀደም የድል በዓሉ በብቸኝነት ከሚከበርባቸው የአዲስ አበባ እና የዓድዋ ከተሞች በተጨማሪ ከ28 በላይየሚሆኑ የክልል ከተሞች እና በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸው የገጠር ወረዳዎች ተጓዥ ቡድኑ በየደረሰበት በሚኖሩ ደማቅ አቀባበሎች ላይ በሚሰጡ የግንዛቤ መስጫ መልዕክቶች ስለ ዓድዋ ድል ታሪክ ግንዛቤ በመሰጠቱ የበዓሉአከባበር ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛል። የጉዞ ዓድዋ ትሩፋቶች፦
- በዓድዋ ከተማ ውስጥ በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የነበረው የዓድዋ ድል በዓል አከባበር ሥነ ሥርዐትበየዓመቱ እንዲካሔድ አስችሏል።
- የበዓሉ አከባበር በፌደራል መንግሥት ደረጃ እንዲከበር ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል።
- ከ120 ዓመታት በፊት መቀሌ ከተማ በሚገኘው የእንዳየሱስን ምሽግ ለማስለቀቅ ከጣሊያን ጦር ጋር ሲዋጉ ሕይወታቸው ያለፉ ጀግና ኢትዮጵያውያን አጽም የትም ተበታትኖ በመቅረቱ፥ ጉዞ ዓድዋ በአሁኑ ሰዓት የቦታው አስተዳዳሪ የሆነውን የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በማንቃት፤ የካቲት 26 ቀን 2008 ዓ. ም አጽማቸውን አሰባስቦ በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል። ከዚህም ባሻገር በዓመቱ የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ወጪ “የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን መታሰቢያ ሙዚየም” የተሰኘ ጣራ አልባ ቤተ መዘክር በእንዳየሱስ ታሪካዊ ምሽግ ላይ ተገንብቶ ለመመረቅ በቅቷል።
- የዓድዋ ጦርነት መንስዔ የሆነው የዉጫሌ ውል የተፈረመበት “ይስማ ንጉሥ” የተባለው ታሪካዊ ቦታ ተከልሎ ጥበቃ እንዲደረግለት በማድረግ ጉዞ ዓድዋ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ከዚህም በተጨማሪ ውሉ በተፈረመበት ዕለት ሚያዝያ 25 ቀን በየዓመቱ፤ ምሁራዊ ተዋስዖ የሚደረግባቸው መድረኮች በመፍጠር፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት ባበረከተው የላቀ አስተጽዖ የአምባሰል ወረዳ የዓድዋ ድልን ለመዘከርና ቦታውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ያለመቋሚ ቤተ መዘክር በቦታው ላይ እንዲገነባ የሚያስችል የ19 ሚልዮን ብር የበጀት ድጋፍ ከአማራ ክልል መንግሥት እንዲያገኝ ጉዞ ዓድዋ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
- ለበርካታ ዓመታት አገልግሎቱ ተዘግቶ የቆየው በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የትውልድ መንደር “አንጎለላ” የሚገኘው የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ መታሰቢያ ክሊኒክ እንዲከፈት ከፍተኛ ቅስቀሳ በማድረግ፤ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድጋፍ ክሊኒኩ ታዳጊ የጤና ጣቢያ ሆኖ በድጋሚ አገልግሎት እንዲሰጥ ጉዞ ዓድዋ አስተዋጽዖ ካደረጉ መካከል ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውቷል።
- የዓድዋ ጀግና የሆኑት ራስ አሉላ አባ ነጋ የቀብር ቦታ በሆነው የአባ ገሪማ ገዳም ውስጥ ለሁለቱም ጾታዎች ጉብኝት ምቹ በሆነ ቦታ ላይ ሐውልት እንዲቆምላቸው ጉዞ ዓድዋ ባመቻቸው ዕድል በአንድ ባለ ሀብት ሐውልታቸው ተሠርቶ ለምረቃ በቅቷል።
- በየዓመቱ በሚካሔዱ ጉዞዎች ከዓድዋ ድል ጋር ግንኙነት ያላቸው ቦታዋችን እና ልዩ ታሪካዊ መረጃዎችን በምስል እና በጽሑፍ በመሰብሰብ ለጥናትና ምርምር አስተዋጽዖ ማበርከት የሚችሉ የታሪክ ግብዓቶችን በማደራጀት በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በተለይም የማኅበራዊ ድረ ገጽን በመጠቀም ቅርሶችን የማስተዋወቅና የመጠበቅ ሥራዎችንበ መሥራት ላይ ይገኛል።
የጉዞ ዓድዋ ማኅበር የዓድዋ ድል በዓል በኢትዮጵያውያን እንዲሁም በጥቁር አፍሪካውያን ዘንድ የሚገባውን ክብር እንዲያገኝ ላደረገው ጥረት፣ ከላይ ለተጠቀሱት እና በየዓመቱ በሚያደርጋቸው እጅግ አመርቂ ክንዋኔዎች ምክንያት በ2009 ዓም በቅርስና ባሕል ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ተሸላሚ ሆኗል።
ላይ የሚሳተፉ ተጓዦች በጉዞአቸው ላይ የሚያደርጓቸውን የተለያዩ ክንዋኔዎችና የሚዘግቧቸውን ታሪክ ተኮር ዘገባዎች ለመከታተል የማኅበሩን የፌስቦክ ገጽ ይጎብኙ።
◌ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በደብረ ብርሃን ከተማ ሃውልት ሊቆምላቸው ነው
ምንጭ፦ በጎ ሰው ሽልማት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.