Home › Forums › Semonegna Stories › ምዕራብ ጎጃም፣ አዲስ ዓለም ከተማ ውስጥ ሁለት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎች በከተማው ተወላጆች ተደብድበው ተገደሉ
Tagged: ምዕራብ ጎጃም, አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ, አዲስ ዓለም
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 26, 2018 at 7:13 pm #8260SemonegnaKeymaster
አዲስ ዓለም ከተማ የሞቱት ሁለቱ ተመራማሪዎች ወሰን ታፈረ እና ማንደፍሮ አብዲ የሚባሉ ሲሆን፥ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰበት የሜጫ ወረዳ ጤና መኮንን (የላቦራቶሪ ባለሙያ) የሆነው ኃይለየሱስ ሙሉ ይባላል።
አዲስ ዓለም፣ አማራ ክልል – በምዕራብ ጎጃም ዞን ጎንጂ ቆለላ ወረዳ ለምርምር ወደ አዲስ ዓለም ከተማ የሄዱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ (ዶክትሬት) ዲግሪ ተማሪዎች እና የሜጫ ወረዳ ጤና መኮንን በከተማው የሚኖሩ ግለሰቦች ባደረሱባቸው ጥቃት ሁለቱ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ አንዱ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶበታል። ሁለቱ የሞቱት ተመራማሪዎች ወሰን ታፈረ እና ማንደፍሮ አብዲ የሚባሉ ሲሆን፥ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰበት የሜጫ ወረዳ ጤና መኮንን (የላቦራቶሪ ባለሙያ) የሆነው ኃይለየሱስ ሙሉ ይባላል።
የዶክትሬት ተማሪዎቹ አዲስ ዓለም ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ለምርምር የሚሆን የሽንትና የዓይነ ምድር ናሙና እየሰበሰቡ ባሉበት ወቅት ከዕለቱ ቀደም ብሎ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች “ሦስት ተማሪዎች ሞቱ” በሚል በተነዛው ወሬ ተቆጥተው በመጡ የአካባቢው ወጣቶች በደረሰባቸው ከፍተኛ ጥቃት ሕይወታቸው ማለፉን የምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አንማው ዳኛቸው ለአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቢቢሲ አማርኛ የጎንጂ ቆለላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ደመቀ መላኩን ጠቅሶ እንደዘገበው “በተሳሳተ መልኩ ልጆቻችን የጤና ክትባት እየተሰጣቸው ነው፤ እየተመረዙብን ነው፤ ሊገደሉብን ነው” በሚል የተቆጡ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የአካባቢው ግለሰቦች የዶክትሬት ተማሪዎቹ (ተመራማሪዎቹን) ወደነብሩበት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ሄደዋል። የትምህርት ቤቱ የጥበቃ ሠራተኞች ሁኔታው ከአቅማቸው በለይ ሲሆን በአካባቢው በነበሩ ጥቂት የጽጥታ አስከባሪ አካላት (ፖሊሶች) ታግዘው ተመራማሪዎቹን ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየወሰዷቸው ሳለ፥ በከተማው መናኸሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ቢቢሲ አማርኛ ጨምሮ ዘግቧል።
ግለሰቦቹ ያደረሱት ጥቃት በተማራማሪዎቹ ላይ ብቻ ሳይገታ ሁኔታው በፈጠረው ግርግር ለቤተ ክርስቲያን ህንፃ ግንባታ ግልጋሎት የሚውል ሲሚንቶ በራሳቸው መኪና ጭነው ወደ አካባቢው ተጉዘው የነበሩ ጥንዶች ንብረትም መቃጠሉን የአሜሪካ ድምፅ አቶ አንማው ዳኛቸውን ጠቅሶ ዘግቧል። አቶ አንማው ለአሜሪካ ድምፅ አክለው በሰጡት ማብራሪያ በዚህ ድርጊት ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ 30 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፣ ብሎም በተፈፀመው ድርጊት የአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ መንግሥት ማዘኑን እና በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉትን እየፈለጉ በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሥራ መቀጠሉን ጠቁመዋል።
ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የጎንጂ ቆለላ ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አንተነህ በላይ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር ውስጥ ለህፃናት ክትባት ሲሰጡ ሞቱ በሚል በተናፈሰ ወሬ ምክንያት መኪና መሰባበር፣ እንዲሁም በአንዳንድ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት (መቁሰል) መድረሱን አስታውሰው አካባቢው ለባህር ዳር ከተማ ቅርብ በመሆኑ ይሄው መረጃ በመናፈሱ ጥቃቱ ሊፈፀም እንደቻለ አስረድተዋል። አቶ አንተነህ አክለው እንደተናገሩ ጥቃቱን ያደረሱት የ አካባቢ ተወላጆች መሆናቸውና አገር ሊጠቅሙ ምሁራን በራሳቸው ወገኖች በመገደላቸው የ አካባቢው ማኅበረሰብ መፀፀቱን፣ በድርጊቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን አጋልጦ መስጠት የጀመረውም ራሱ ህብረተሰቡ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ከምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አንማው ዳኛቸው ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.