Home › Forums › Semonegna Stories › ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ በሙዚቃ ሥራ ምርምርና ጥናት ውስጥ ቀዳሚ ኢትዮጵያዊ ናቸው ― አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት
Tagged: Ashenafi Kebede, Sertse Firesbhat, ሠርፀ ፍሬስብሐት, እንዳለጌታ ከበደ, ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት, ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 1 month ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
November 19, 2018 at 8:55 am #8575SemonegnaKeymaster
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት አውስቷል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር ያለው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ-ጥበባት ማዕከል 40ኛ የጥበብ ውሎ መድረኩን ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ አካሒዷል።
በዝግጅቱ ላይ የዕውቁ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ሰው የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ተደርጓል። ሥራዎቹን እና ሕይወቱን አስመልክቶ የሙዚቃ ባለሙያ እና በቅርቡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ሆኖ የተሾመው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት የውይይት መነሻ ጥናት አቅርቦ በታዳሚዎች ውይይት ተካሂዶ ነበር።
“ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ <ባለዋሽንቱ እረኛ>(The Shepherd Flutist) በተሰኘ ታላቂ ሥራ የኢትዮጵያን መልክ በረቂቅ ሙዚቃ ያሳዩ ናቸው” በማለት አቶ ሠርፀ የገለጿቸው የሙዚቃውን ረቂቅነት በመጥቀስ ሲሆን፤ ፕሮፌሰር አሸናፊ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አውስቷል።
በሙዚቃ ላይ ከሠሯቸው ከበርካታ የምርምር ሥራዎቻቸው ውስጥ “Roots of Black Music” የተሰኘው መጽሐፋቸው በብዙ የዓለማችን የሙዚቃ አጥኚዎች የተዘነጉ (የተዘለሉ) የአፍሪካ/የምሥራቁ ዓለምን የሙዚቃ ስልትና ፍልስፍናን አጉልተው ለተቀረው ዓለም ያሳዩበት እንደሆነም አቅራቢው አብራርተዋል።
በውይይቱም ከተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዘመናት መካከል የመድመቅና መልሶ የመደብዘዝ ችግር ከምን የመነጨ እንደሆነ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፥ “ዋናው ችግር በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተቋም ፈርሷል፤ እሱን መልሶ መገንባት የቤት ሥራችን ነው” ብለዋል አቶ ሠርፀ። አክለውም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ትምህርት ሥርዓት ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከምዕራባውያን የሙዚቃ ሥርዓተ-ትምህርት ነፃ መውጣት ያለመቻሉም ሌላ ምክንያት እንደሆነ አቅራቢው ጠቅሰዋል።
ውይቱን የመሩት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ እንዳለጌታ ከበደ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ማደግ ብርቱ ጥረት ያደረጉ የጥበብ ሰዎችን ፈለግ እና ሥራዎቻቸውን ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ በሁሉም አካላት ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ አዲስ አበባ ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። አባታቸው ግራዝማች ከበደ አድነው፣ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ፋንታዬ ነከሬ ያባሉ ነበር። የሙዚቃ ፍቅርን ገና በልጅነታቸው ያሳደሩባቸው እናታቸው ቢሆኑም ታዳጊው አሸናፊ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳሉ እናታቸውን በሞት አጥተዋል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ መሠረታዊ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (አሁን ኮከበ ጽባሕ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚባለው) ካጠናቀቁ በኋላ ከሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ተመርቀዋል። ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት ኒው ዮርክ ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሮቸስተር፣ ኢስትማን የሙዚቃ ትምህርት ቤት (University of Rochester’s Eastman School of Music) በ1954 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሰ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን መሥርተዋል። የትምህርት ቤቱም የመጀመሪያው ዳይሬክተር ከመሆናቸውም ባሻገር በመሆን ሙዚቃን ከማስተማሩ ባሻገር አገልግለዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ.ወ.ክ.ማ.)፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት መርሓ-ዕውራን ትምህርት ቤት እና በመሳሰሉ የወጣቶች ማኅበራት እየተገኙ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጡ ነበር።
በድጋሚ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ተመልሰው፣ ኮነቲከት ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዌስልያን ዩኒቨርሲቲ (Wesleyan University) በ1961 ዓ.ም የማስትሬት፣ እንዲሁም በ1963 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ምዕራባዊ ባልሆኑ ሙዚቃዎች ምርምር (ethnomusicology) አግኝተዋል።
ከሙዚቃው መምህርነትና ተመራማሪነት ባሻገር ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ደራሲም ነበሩ። እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም ኮንፌሽን (Confession)፣ እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም ሩትስ ኦፍ ብላክ ሙዚክ (Roots of Black Music) የሚሉ መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲሆን፣ በሙዚቃ ላይ ያተኮሩ በርካታ ጽሁፎችን፥ በተለይም ደግሞ በአፍሪካ-አሜሪካውያን ባህልና አኗኗር ላይ ለሚያተኩረው “The Chronicler” ለተሰኘው መጽሔት ጽፈዋል።
በአሜሪካ ፕሮፌሰር አሸናፊ ኑሯቸው ፍሎሪዳ ክፍለ ሀገር በሚገኘው ፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርሲቲ (Florida State University) የሙዚቃ ኮሌጅ ውስጥ በመምህርነት የሠራ ሲሆን፣ ተቀማጭነቱን እዚያው አሜሪካ ያደረገውናታዋቂውን የኢትዮጵያ ምርምር ካውንስልን (Ethiopian Research Council) በዳይረክተርነት መርቷል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ባለቤታቸው (ወ/ሮ እሌኒ ገብረመስቀል) እና ሁለተኛ ባለቤታቸው (አሜሪካዊ) አራት ልጆችን (ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ) ልጆችን አፍርተዋል። ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የ60ኛ የልደት በዓላቸው ዕለት በመኖሪያ ቤታቸው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሞተው የተገኙ ሲሆን፤ ምናልባትም የራሳቸውን ሕይወት ሳያጠፉ እንዳልቀሩ ብዙዎች ይገምታሉ።
PHOTO: Ethiopian Academy of Sciences -
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.