በአዲስ አበባ ለሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ዝግጅቱ ተጠናቋል ― የፌደሬሽን ምክር ቤት

Home Forums Semonegna Stories በአዲስ አበባ ለሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ዝግጅቱ ተጠናቋል ― የፌደሬሽን ምክር ቤት

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #8826
    Semonegna
    Keymaster

    ኢትዮጵያዊያን አያሌ የሚያስተሳስሯቸው ነገሮች ያሏቸው በመሆኑ የሚያለያዩዋቸውን ጥቂት ነገሮች በመቻቻል አንድነታቸውን የሚያጎለብቱ ጉዳዮችን ጎልቶ እንዲወጣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል።

    አዲስ አበባ (ኢ.ፕ.ድ) – የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ከልዩነት በላይ ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ የፊዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ።

    የፊታችን ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀን በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ዝግጅት መጠናቀቁንም ምክር ቤቱ አስታውቋል።

    ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረውን በዓል ከልዩነት በላይ ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ በምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረሥላሴ በተለይ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢ.ቢ.ሲ) ተናግረዋል። በዚህም ብሔረሰቦች የራሳቸውን ባህል ከማስተዋወቅ በዘለለ የባህል ልውውጥ የሚያደርጉበት መድረክ እንደሚፈጠር ገልፀዋል።

    በዚህም አንዱ ብሔር የሌላውን ባህል እንዲያንፀባርቅ በማድረግ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጎለብት ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል ዳይሬክተሩ አቶ ገብሩ።

    ኢትዮጵያዊያን አያሌ የሚያስተሳስሯቸው ነገሮች ያሏቸው በመሆኑ የሚያለያዩዋቸውን ጥቂት ነገሮች በመቻቻል አንድነታቸውን የሚያጎለብቱ ጉዳዮችን ጎልቶ እንዲወጣ በዓሉ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

    አቶ ገብሩ አክለውም ዘንድሮ በአዲስ አበባ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው የበዓሉ ተሳታፊዎች እየተጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል። በበዓሉ ዕለትም በክልሎች ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲምፖዚየሞች፣ የተለያዩ ውይይቶችና ዝግጅቶች እንደሚካሄዱም ይጠበቃል ብለዋል።

    በበዓሉ በሚካሄዱ ውይይቶች ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በግጭቶች መንስዔ ዙሪያ ምክክር ተደርጎ የመፍትሄ ሀሳቦች እንዲቀመጡም እንደሚደረግ አቶ ገብሩ አመላክተዋል።

    የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገ-መንግስት የፀደቀበት ቀን የሆነው ህዳር 29 ቀን‹‹በብዝሃነት የደቀመ ኢትዮጵያዊ አንድነት›› በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ይከበራል።

    በበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ወቅትም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ የሰላም ጉባኤዎች በተለያዩ ክልሎች ሲካሄዱ መቆየታቸውንም ምክር ቤት አስታውቋል። ባለፈው ዓመት 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በሆነችው ሰመራ መከበሩ ይታወሳል

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢ.ፕ.ድ) | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.