እስከ 2012 ዓ.ም መጨረሻ በአጠቃላይ 15 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ማምረት ይገባሉ

Home Forums Semonegna Stories እስከ 2012 ዓ.ም መጨረሻ በአጠቃላይ 15 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ማምረት ይገባሉ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #8065
    Semonegna
    Keymaster

    እንደ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጻ፥ እስካሁን ባለው ተሞክሮ የአንድ ፓርክ ግንባታ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ይጠናቀቃል፤ በዚህ መሠረት  አሁን በግንባታ ላይ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃሉ።

    አዲስ አበባ – እስከ አሁን ወደ ምርት የገቡትን አራቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮችና በቅርቡ የተመረቀውን የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጨምሮ በ2012 ዓ.ም ማጠናቀቂያ 15 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ማምረት እንደሚገቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

    የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽንና ማኔጅመንት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን በተለይ እንደተናገሩት፤ እስካሁን የሀዋሳ፣ የቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ አይሲቲ፣ የመቐለ እና ኮምቦልቻ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ገብተዋል። ከቀናት በፊት የተመረቀውን የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጨምሮ የጅማና የደብረ ብርሃን በሁለት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ ይገባሉ።

    የቦሌ ለሚ ቁጥር ሁለት፣ የባህር ዳር፣ የድሬዳዋና የቂሊንጦ ፋርማስቲዩካል ፓርኮች በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠናቀቁ መሆናቸውን ገልፀው ከዚህ በተጨማሪ የአይሻ፣ የአረርቲ የአሶሳና ሠመራ ፓርኮች በዚሁ ዓመት ግንባታቸውን ለመጀመር የአዋጭነት ጥናቶቻቸው ተጠናቆ ወደ ስምምነት እየተገባ መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁን ባለው ተሞክሮ የአንድ ፓርክ ግንባታ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ይጠናቀቃል ያሉት ኃላፊው ሌሎቹም በዚሁ መሠረት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃሉ ብለዋል።

    ተያያዥ ዜና፦ ቬሎሲቲ አፓረልዝ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመርያ የሆነውን የግል የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነባ ነው።

    ፓርኮቹ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ ቢሆንም በዋናነት መንግሥት በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ባስቀመጠው መሠረት በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ በህክምና መገልገያዎችና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። እነዚህ ዘርፎች በአነስተኛ ካፒታል የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉም ናቸው። በተጨማሪም ፓርኮቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከማበረታታት ባሻገር የውጭ ባለሀብቶችን በስፋት ለመሳብ የሚያስችሉ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።

    እንደ አቶ ሽፈራው ገለፃ፤ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ በውጭ ምንዛሬ የሚገቡትን ምርቶች የሚተኩና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ የሚያሳድጉ ይሆናሉ። በዚህ ረገድ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በመድኃኒት ምርት፣ የድሬዳዋና የአዳማ ደግሞ በኮንስትራክሽን ማቴርያልና ከውጭ የሚገቡ ኬሚካሎችን በአገር ውስጥ ለመተካት የተያዙ ሲሆን፤ በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የሚሰማሩት የወጪ ንግድ ላይ የሚያተኩሩ እንደሆኑም ገልፀዋል።

    በ2006 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን (IDPC) ሀገሪቱ ውስጥ በመንግስት ውጪ የሚገነቡትናና ወደ ሥራ የገቡትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች በበላይነት ይቆጣጠራል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬሥ ድርጅት

    የኢንዱስትሪ ፓርኮች

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.