ዓመታዊው የትምህርት ጉባዔ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት ተጠናቆ ለመንግስት ውሳኔ በሚቀርብበት፣ 5ኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር የሦስት ዓመት አፈጻጸም የሚዳሰስበት፣ ለቀጣይ ሥራ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነበር።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የሚያዘጋጀው 28ኛው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በትግራይ ብሔራዊ ክልል መቐለ ከተማ ተካሔደ። በየዓመቱ ሚካሄደው እና ከመጋቢት 12 እስከ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በቆየው 28ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በመድረኩ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ከሁሉም ክልሎችና ከተለያዩ ከተማዎች አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች የተውጣጡ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለ ድርሻ አካላት እንዲሁም የትምህርት ልማት አጋር አካላት በሀገር አቀፉ የትምህርት ጉባዔ ተሳታፊ ሆነዋል።
● SEMONEGNA on Social Media: Facebook | Twitter | Instagram | Pinterest
ዓመታዊ ጉባዔው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት ተጠናቆ ለመንግስት ውሳኔ በሚቀርብበት፣ 5ኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር የሦስት ዓመት አፈጻጸም የሚዳሰስበት፣ ለቀጣይ ሥራ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው አቅጣጫ የሚቀመጥበት ሁነኛ ጉባዔ እንደነበር የትምህርት ሚኒስቴር ዘግቧል።
በተጨማሪም በአፈፃጸም ሂደት የተገኙ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ለአብነት የትምህርት ጥራትና የትምህርት ቤቶች ደረጃ ምደባ ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት እንደተደረገባቸው ታውቋል።
የዘንድሮውን ትምህርት ጉባዔን ለየት የሚያደርገው ሀገር አቀፍ የተማሪዎች ስፓርት ጨዋታ ጋር አቀናጅቶ እንዲካሄድ መደረጉ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።
ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦