5ኛውን አዲስ ፎቶ ፌስት የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ያዘጋጁት ደስታ ለአፍሪካ [የፈጠራ አማካሪ] ከስዊዘርላንድ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ሲሆን፥ አውደ ርዕዩ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ይቆያል።
አዲስ አበባ (ቢቢሲ አማርኛ) – በአፍሪካ ውስጥ ስመጥር ከሆኑት የፎቶ ፌስቲቫሎች ከፍተኛ ቦታ ያለው አዲስ ፎቶ ፌስት ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል ተከፍቷል።
ለአምስተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከ61 ሃገራት የተወጣጡ 152 የፎቶ ግራፍ ባለሙያዎች የተለያዩ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ። ይህ አውደ ርዕይ በየዓመቱ አሳታፊነቱ እየጨመረ የመጣ እንደሆነ የምትናገረው ‘ደስታለ አፍሪካ የፈጠራ አማካሪ’ (Desta for Africa Creative Consulting) የተባለ ድርጅት መሥራችና የአዲስ ፎቶ ፌስት ዋና አዘጋጅ የሆነችው የፎቶ ባለሙያዋ አይዳ ሙሉነህ ዋና ትኩረቱም የውክልና ጉዳይ ነው ትላለች።
አፍሪካ በተለያዩ ምስሎችም ሆነ በውጭው ዓለማት የምትታወቀው ሁሌም ከችግር፣ ድርቅና ረሀብ ጋር ብቻ ከመሆኑ አንፃር አዲስ ፎቶ ፌስት በጎ ጎኗንም ለማሳየት እንዳለመ አይዳ ታስረዳለች።
“ይህንን የፎቶ አውደ ርዕይ የምናየው እንደ አቅም ግንባታ ነው፤ እነዚህን ሁሉ ወጣት የፎቶ ባለሙያዎች ስናሰባስብ ወይም ስልጠና ስንሰጥ የኢትዮጵያን እውነታ በምን መንገድ ሊያሳዩ ይችላሉ የሚለውን ለማሳየት ነው” በማለት ታስረዳለች አይዳ።
በተለይም አፍሪካ እንደ ጨለምተኛ ብቻ አህጉር ተደርጋ መታየቷ ትክክለኛ እይታ እንዳልሆነ የምትናገረው አይዳ “ሁሉም ነገር በጎ አይደለም፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር ደግሞ መጥፎ አይደለም። በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጎልቶና ገኖ የሚታየው መጥፎ ነገር ነው” በማለት ይህንንም ለመቀየር ኢትዮጵያዊ ወይም አፍሪካዊ ፎቶ ባለሙያዎችን ማፍራትና እይታዎችንም መፍጠር እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ትሰጣለች።
በዚህ ዓመት አዲስ ፎቶ ፌስት ዓውደ ርዕይ ላይ 1200 ፎቶዎች የሚቀርቡ ሲሆን ከዓመት ወደ ዓመት የተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ አይዳ ሙሉነህ ተናገራለች።
በባለፈው አመት ለመሳተፍ የጠየቁ የፎቶ ባለሙያዎች ቁጥር 500 የነበረ ሲሆን በዚህ አመት ወደ 832 ደርሷል። ከነሱም ውስጥ 152 ባለሙያዎች ተመርጠው ተሳታፊ ሆነዋል። ለአይዳ ሙሉነህ የተሳታፊዎች ቁጥር መብዛት የሚያሳየው አዲስ ፎቶ ፌስት በዓለም ላይ ያለው ስፍራ እየጨመረ መሆኑን ነው።
በተጀመረበት ወቅት አምስትዓ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ያሳተፉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም 35 እንደደረሱ አይዳ ትናገራለች። ምንም እንኳን በፈተናዎች የተሞላ መሆኑን አይዳ ባትክድም “ይሄን ሁሉ ሥራ የምንሰራው ሃገሪቷን ለማሳወቅ ነው” ትላለች።
5ኛውን አዲስ ፎቶ ፌስት የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ያዘጋጁት ደስታ ለአፍሪካ የፈጠራ አማካሪ ከስዊዘርላንድ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ሲሆን፥ አውደ ርዕዩ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ይቆያል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ አማርኛ | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ