Home › Forums › Semonegna Stories › ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ ላይ ክስ መሠረተ
Tagged: ABH Partners, HERQA, አንዱዓለም አድማሴ, የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 3 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
September 4, 2019 at 11:04 pm #11869SemonegnaKeymaster
ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ ላይ ጉዳት አድርሰውብኛል በሚል በመሠረተው የ174.6 ሚሊዮን ብር ክስ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ።
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን ጋዜጣ) – የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ (HERQA) እንዲሁም አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ በድርጅቱ ላይ ላደረሱትና ለሚደርሰው ጉዳት የ174.6 ሚሊዮን ብር ተከፍሎ እስከሚያልቅ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር ክስ እንዳቀረበባቸውና ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ፍርድ ቤት እንደቀርቡ ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ጥምረት ለተሻለ ጤና) /ABH Partners/ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፥ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከማምራቱ በፊት ኤጀንሲው የድርጅቱን መልካም ሥምና ዝናን በማጠልሸቱ ይቅርታ እንዲጠይቅና ችግሩን እንዲያርም ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም።
በዚህም ድርጅቱ ነሐሴ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ-ብሔር ስድስተኛ ምድብ ችሎት የመዝገብ ቁጥር 241863 ክስ ለመመሥረት ተገዷል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴን ጨምሮ አምስት የሥራ ኃላፊዎችም ተከሰዋል።
ኤጀንሲው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ (ABH Partners) ጋር በጥምረት የሚሠሩትን ሥራ እንደማያውቀው ቢያስተባብልም፤ ሁለቱ ተቋማት ውል ተፈራርመው ሥራውን ሲጀምሩ በወቅቱ የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በቦታው ተገኝተው መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተው እንደነበር ዶ/ር ማርቆስ አስታውሰው፤ “ይህም መንግሥት አያውቀውም የሚለውን ሐሳብ ትክክል እንዳልሆነ አመላካች ነው። ከወራት በፊት ትምህርት የሚሰጥበትን ቦታ ተገኝተው የጎበኙ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታዎች ግን ‘ሥራው የዩኒቨርሲቲውን አቅም ለማዳበር ያገዘ ነው’ ሲሉ አሞካሽተውታል። ለጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመስጠት የመምህራን ፍልሰት እንዲቀንስ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱንና ለትምህርት ጥራት እንዲተጋ የሚያግዙ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ሚኒስቴሩ ምስክርነቱን በደብዳቤ ሰጥቷል” ብለዋል።
ሚኒስቴሩ፥ የዚህ መሰል የግሉ ዘርፍና የመንግሥት አጋርነት ለትምህርት ጥራትም ሆነ ተደራሽነት ሚናው የላቀ መሆኑን በመግለጽ፥ ለዚህ ሊበረታታ ለሚገባው ድርጅት አገራዊ ፋይዳውን በማየት የግንባታ መሬት በመስጠት ትብብር እንዲደረግላቸው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የትብብር ደብዳቤ እንደፃፈላቸውም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴሩ ለዩኒቨርሲቲውና ለድርጅቱ ምስክርነት በመስጠት ከመንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ሲያደርግ፥ ኤጀንሲው ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 ከሰጠው ሥልጣን ውጪ “ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ በአዲስ አበባ የሚሰጠው ትምህርት ዕውቅና የለውም፤ ሕጋዊም አይደለም” በማለት እግድ ማስተላለፉ “ባለፉት ሰባት ዓመታት የት ነበረ?” የሚል ጥያቄንም የሚጭር እንደሆነ ዶ/ር ማርቆስ አብራርተዋል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ሥራውን ሊሰራ፤ አማካሪ ድርጅቱ ደግሞ አስተዳደራዊ ድጋፍ ሊሰጥ በገቡት ስምምነት መሠረት ዩኒቨርሲቲው አዲስ አበባ ባለው ካምፓስ ምንም ዓይነት የመንግሥት ድጋፍ ሳይደረግለት ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሙሉ ድጋፍ በማድረግ ለመማር-ማስተማሩ አስፈላጊ ግብዓቶችን አሟልቶ በውሉ መሠረት ግዴታውን ሲወጣ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከዋናው ግቢ ውጪ ማስተማርም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር መሥራት እንደማይችል ኤጀንሲው ቢገልጽም፣ በዩኒቨርሲቲው እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 ግን ዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ከሚገኝበት ጅማ ከተማ ውጪ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን እንዲሁም የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ሊያቋቁም እንደሚችል ተደንግጓል።
በተመሳሳይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸውን ለማሟላት ድጋፍ ሊሰጣቸው ከሚችል ከማንኛውም ተቋም ጋር መሥራት እንደሚችሉ ይደነግጋል። በዚህም በአዋጁ ያልተከለከለን ሥልጣን ኤጀንሲው በደብዳቤ መሻሩ ተገቢነት እንደሌለው ዶ/ር ማርቆስ ገልፀዋል። በመሆኑም ለቀጣይ የትምህርት ዘመን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንና ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች በሁኔታው መደናገጥ እንደማይገባቸው ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ (ቁጥር 650/2001) አንቀጽ 93፣ ንዑስ አንቀጽ አንድ አገልግሎት በሌሎች ወገኖች እንዲሰጥ ስለማድረግ ይደነግጋል። በዚህም ማንኛውም የመንግሥት ተቋም ተገቢና ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ሆኖ ሲያገኘው የድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን በሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች እንዲሰጥ ሊያደርግ እንደሚችል አስቀምጧል።
በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ (ቁጥር 240/2003) በአንቀጽ ሦስት መሠረት የዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ጅማ ከተማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችን፣ የምርምርና የሕብረተሰብ አገልግሎት ማዕከሎችን ሊያቋቁም እንደሚችል ተቀምጧል።
ባለፉት 15 ቀናት ኤጀንሲው “የትብብር ሥልጠና ትክክል ባለመሆኑ እንዲያቆሙ” በሚል ሚኒስቴሩ በደብዳቤ ማሳወቁን መግለጹ ይታወሳል። በዚህ መልኩ ሲሠሩ የነበሩ የጅማ፣ የደብረ ማርቆስ፣ የባህር ዳር እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች እንደታገዱ አሳውቋል።
ሆኖም ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ኤ.ቢ.ኤች. ፓርትነርስ ሥራቸውን በመቀጠላቸው “አደብ ሊገዙ ይገባል” ብሎም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ኤጀንሲው በተቋማቱ በመማር ላይ ያሉትን ተማሪዎች ዝርዝር እንዲላክለት የጠየቀ ሲሆን፤ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ ግን ቀጣይ ውይይት እንደሚያስፈልገው አሳውቆ ነበር።
ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.