Home › Forums › Semonegna Stories › በመላው ዓለም የተስፋፋውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመግታት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ
Tagged: ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን, የኮሮና ወረርሽኝ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 4 years, 10 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
March 24, 2020 at 4:40 am #13961SemonegnaKeymaster
በመላው ዓለም የተስፋፋውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመግታት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ
በሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠር፣ በከተማና በመላው ዓለም ለምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ!
ወቅታዊ የሰው ልጅ ሥጋት በመሆን በመላው ዓለም በፍጥነት በተስፋፋው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም አቀፍ ሥጋት ስለተከሰተ መንግሥታት ሀገርን ከጥፋት፣ ሕዝብን ከሞት ለመጠበቅ አዋጆችን እያወጡ ይገኛሉ።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ለመታደግ እምነትና ቀኖናን ጠብቆ ሃይማኖታዊ መመሪያ የመስጠት ሐዋርያዊ ኃላፊነት አለባት።
ስለዚህ ቋሚ ሲኖዶስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሠረተ እምነትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ ለሁሉም ካህናትና ለሕዝበ እግዚአብሔር ደኅንነት ሲባል የሚከተሉትን መመሪያዎች አስተላልፏል፡-
- በሰሙነ ሕማማት እንደምናደርገው የእርስ በርስ መሳሳም ቀርቶ ራስን ዝቅ በማድረግ፣ እጅ በመንሳት ወይም በእማሄ ሰላምታ በማቅረብ እንዲፈጸም፣
- ወረርሽኙ በሰዎች መሰባሰብ የሚስፋፋ ስለሆነ ማናቸውም መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት፣ ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች እና ምዕመናን የሚሳተፉባቸው ታላላቅ መርሐ ግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጡ፣
- ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ሆነ አሰፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ እጆቻንን በመታጠብና ዘርዘር ብሎ በመቆም ሥርዓተ አምልኮ እንዲፈጸም፣
- ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በቅዳሴና በማኅሌት ታስበው ክብረ በዓላቱ በሌላ ጊዜ እንዲከበሩ፣
- የጉንፋን ምልክት ያለባቸው ለሌሎች እንዳያስተላልፉ በቤታቸው በጥንቃቄ ተለይተው በጸሎትና በሕክምና እንዲቆዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎትም በልዩ ሁኔታ እንዲያገኙ፣
- በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የተስፋ ልዑክ በመሆን እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተደራጅቶ ተልዕኮውን በአስቸኳይ እንዲጀምር
- ሥርዓተ ቅዳሴን በተመለከተ፡-
-
- በቤተ መቅደስ ቀዳስያን በሆኑት ልዑካን ብቻ ሥርዓተ ቅዳሴው እንዲፈጸምና ሌሎች አገልጋዮች በቅድስቱ ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያገለግሉ፣
- በዕለቱ ለሚቆርቡ ምዕመናን ለአረጋውያን፣ ለወጣቶችና ለሕፃናት የፈረቃ ተራ በማዘጋጀት ቆራቢዎች ብቻ ወደ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያስቀድሱ፣
- ሌሎች ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ቢያንስ ሁለት የትልቅ ሰው እርምጃ ያህል በመራራቅ ቆመው እንዲያስቀድሱ፣
- የቅዳሴ ጠበል በየግል መጠቀሚያ ምእመናን በየቆሙበት ቦታ በጥንቃቄ እንዲሰጥ፣
- ሌሎች ከቅዳሴ ጋር የተያያዙ ዝርዝር የአፈፃፀም ጉዳዮችን ግብረ ኃይሉ አዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ በማጸደቅ ለአህጉረ ስብከት በሚልከው መመሪያ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ፤
- ከሥርዓተ ቅዳሴ በተጨማሪ እንደ ስብሐተ ነግሕ፣ ሰዓታት፣ ቁመተ ማኅሌት፣ ጥምቀተ ክርስትና፣ ጸሎተ ፍትሐት፣ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለሥርዓቱ በሚያስፈልገው ቁጥር ብቻ እና በውሱን ሊቃውንት በተራ እንዲፈፀም፣
- ወረርሽኙ ከዓለም እንዲጠፋ ካህናት ብቻ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምኅረትና በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ እጣን በማድረስ ማዕጠንት እንዲፈጽሙ፣
- በማኅበራዊ ግንኙነት በደስታ፣ በሐዘን፣ በእድር፣ በሥርዓተ ቀብር አፈፃፀምና በመሳሰሉት መሰባሰቦች በሽታው እንዳይሠራጭ አገልግሎቱ በውስን የሰው ቁጥር በጥንቃቄ እንዲፈፀም፤
- ምዕመናን ራሳቸውን እየጠበቁ በቫይረሱ የተጠቁና አገግመው የወጡ ወገኖችን፣ እንዲሁም በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ከሃይማኖትና ከምግባር የወጣ መገለልና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በክርስቲያናዊ ፍቅርና በኢትጵያዊ ጨዋነት እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፣
- ለነዳያን እና ለተቸገሩ ወገኖች አስፈላጊው ማኅበራዊ እና ቁሳዊ እገዛ በሁሉም አጥቢያዎች እንዲደረግ፣
- ቤተ ክርስቲያንን ከማይወክሉና ቀኖናዊ ካልሆኑ አሳሳች መረጃዎች በመቆጠብ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያችሁና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንድትፈጽሙ እና እንድታስፈጽሙ ተወስኗል።
በአጠቃላይ በበሽታው እስካሁን ለተያዙት፣ በጊዜያዊ ማቆያ ለሚገኙት በሙሉ እግዚአብሔር አምላካችን ምህረቱን እንዲሰጥልን እንጸልያለን፤
በመላው ዓለም ዜጎቻቸውን በበሽታው ለተነጠቁ ሁሉ መጽናናቱን እንዲሰጥልን ያረፉትንም እንዲምርልን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቃለን፤
በመላው ዓለም የምትገኙ ወገኖቻችን የራሳችሁና የሌሎች ሕይወት ከወረርሽኙ እንዲጠበቅ እንዲሁም የበሽታው ሥርጭት እንዲቆም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እያሳሰብን የተሰጡት መመሪያዎች ወረርሽኙ እስኪጠፋ ድረስ የጸኑ እንዲሆኑ በጥብቅ እናስታውቃለን።
ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱና በይቅርታው ብዛት ዓለማችንን ከጥፋት የሰውን ልጅ ሁሉ ከመከራ ሞት ይጠብቅልን። አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
(መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም.)
አዲስ አበባ -
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.