Home › Forums › Semonegna Stories › ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ አበባ ካምፓስ ተማሪዎች የሰጠው መግለጫ
Tagged: የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ, ጅማ ዩኒቨርሲቲ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 4 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
September 18, 2019 at 11:59 am #12003SemonegnaKeymaster
ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ አበባ ካምፓስ (Jimma University Addis Ababa Campus) ተማሪዎች የሰጠው መግለጫ
ጉዳዩ፡- ተገቢነት በሌላቸው ጽሁፎችና መግለጫዎች እንዳትደናገሩ ስለማሳሰብ
ጅማ (ጅማ ዩኒቨርሲቲ) – ዩኒቨርሲቲያችን መንግሥት የከፍተኛ ትምህርትን ለማዳረስ የሚያደርገውን ጥረት በማሳካት ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ያለው መሆኑ ከሁላችሁም የተሰወረ አይደለም። የመንግሥትን የትምህርት ፖሊሲ ተግባራዊነት ከማረጋገጥ አኳያ ዩኒቨርሲቲያችን በተለያዩ ደረጃዎች የሚሰጠውን ትምህርት አድማስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ መምጣቱ የቁርጠኝነቱ ዓይነተኛ ማሳያ ነው። ይኸውም ዋና መቀመጫው ጅማ ከተማ ሆኖ በአገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎችና ከአገር ውጪም በሐርጌሳ ጭምር ካምፓሶችንና የትምህርት ማዕከሎችን ከፍቶ ትምህርቱን በማስፋፋት ላይ የሚገኘውም በዚሁ አግባብ ነው።
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዩኒቨርሲቲያችን የሚያደርገውን ሕጋዊ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍና ለማስቆም የሚሞክሩ አካላት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተገንዝበናል። ይኸውም የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና ጥቂት የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች በኤጀንሲው የፌስቡክ ገጽ እና በግል የፌስቡክ ገጽ በለቀቋቸው መረጃዎች እንዲሁም የፕሬስ ኮንፈረንስ ጠርተው በመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የዩኒቨርሲቲያችንን ስም ሲያጠፉና ሲያቆሽሹ መቆየታቸው ይታወቃል። አሁን ደግሞ የዩኒቨርሲቲያችንን ስም ከማጥፋት አልፈው በቁጥር 01/መ-4/2688/11 መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በተፃፈ ደብዳቤ በአዲስ አበባው ካምፓሳችን (Jimma University Addis Ababa Campus) በመማር ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች ጥሪ በማድረግ ወደ ሌላ ተቋም እንደሚያዛውሯቸው በኤጀንሲው የፌስቡክ ገጽ መረጃ ለቀዋል።
ነገር ግን ዩኒቨርሲቲያችን የአዲስ አበባውን ካምፓስ (Jimma University Addis Ababa Campus) የከፈተውም ሆነ ላለፉት ሰባት ዓመታት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ሲሰጥ የቆየው ዩኒቨርሲቲውን እንደገና ለማቋቋም በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 አንቀጽ 2(1) እና አንቀጽ 3 መሠረት ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሆኖ ስለተቋቋመ እና ዋና ግቢው ጅማ ከተማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎች እና የምርምርና የማሕበረሰብ አገልግሎት ማዕከሎችን የማቋቋም መብት በሕግ ስተሰጠው ነው። የድጋፍ አገልግሎት ከሚሰጥ የግል ተቋም ጋር ሕጋዊ ስምምነት ተፈራርሞ ለትምህርቱ የሚያስፈልጉ የአገልግሎት ግብአቶችን በማግኘት ላይ ያለው ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 93(1) ስር ማንኛውም የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን በሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችል ሕጋዊ መብት እንዳለው በተደነገገው መሠረት ነው። ይህም ሆኖ በሕግ ድንጋጌዉ ላይ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ትርጓሜ እንዲሰጥ ተጠይቆ ዉጤቱን እየተጠባበቅን ባለንበት ወቅት ሁከት ለመፍጠር የሚደረገዉ እንቅስቃሴ አግባብነት የጎደለዉ ነዉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ሥልጣንና ተግባር ኤጀንሲው በተቋቋመበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 261/2004 አንቀጽ 6 እና በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 89 ስር የተዘረዘረ ሲሆን በሁለቱም ሕጎች ኤጀንሲው ተማሪዎችን ከአንድ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ነጥቆ ለሌላ ተቋም ለመስጠትም ሆነ አንድን ካምፓስ ለመዝጋት የሚያስችል ሥልጣንና ኃላፊነት አልተሰጠውም። ስለሆነም ኤጀንሲውንና የሥራ ኃላፊዎቹ በዩኒቨርሲቲያችን ዙሪያ የሚያደርጓቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች በሙሉ ተገቢነት የሌላቸዉ እና በሌላቸው ስልጣን የተፈፀሙ በመሆናቸው በሕግ የሚያስጠይቁ ናቸው።
ውድ ተማሪዎቻችን! ዩኒቨርሲቲያችን በአዲስ አበባ ካምፓስ ከፍቶ ለተማሪዎች ትምህርት ሲሰጥ የቆየው በሕጋዊ መንገድ መሆኑን እያረጋገጥን ይህንኑ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን በመጋፋት ኤጀንሲውና የሥራ ኃላፊዎቹ በማድረግ ላይ ያሉት አግባብ የሌለዉ እንቅስቃሴ ሕዝብና መንግሥት እንዳይረጋጋ የሚያደርግ በመሆኑ በፅኑ የምናወግዘው ነው። ዩኒቨርሲቲያችን እስከ አሁን ድረስ በኤጀንሲው በበላይ የሥራ ኃላፊዎች ሲፈፀሙ የነበሩትን አግባብነት የሌላቸዉን ተግባራት በትዕግስትና በሰከነ መንፈስ ሲከታተልና መፍትሄ ሲያፈላልግ የቆየ ሲሆን፤ የአሁኑ ተግባር ግን የዩኒቨርሲቲውን ህልውና የሚፈታተንና የኤጀንሲውን የስልጣን እና ኃላፊነት ገደብ የጣሰ በመሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲያችን ጉዳዩን ከሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት መፍታትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ለመፈፀም ቁርጠኛ አቋም የያዘ መሆኑን እየገለፅን፤ በኤጀንሲው ጥሪ ሳትረበሹና ሳትሳሳቱ ዩኒቨርሲቲዉ ከተማሪ እና ከወላጅ ተወካዮች ጋር ባደረገዉ ዉይይት መሠረት ጉዳዩን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን አዉቃችሁ በትዕግስት እንድትጠብቁን እናሳስባለን።
ምንጭ፦ ጅማ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.