Home › Forums › Semonegna Stories › ባለፉት 6 ወራት ለኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 484 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ
Tagged: ኃይሉ አብርሃም, የህዳሴ ግድብ, የኢትዮጵያ ዳያስፖራ, ደመቀ መኮንን
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 5 years, 11 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
February 2, 2019 at 11:54 pm #9443SemonegnaKeymaster
መቀዛቀዝ የታየበትን የህዝባዊ ተሣትፎ ለማነቃቃት የተለያዩ መድረኮችን በቀጣይነት እንደሚያዘጋጅ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሣትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ገልጸዋል።
አዲስ አበባ (ዋልታ)– የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሣትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባለፉት 6 ወራት 484 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቋል።
ጽህፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ ሲሆን በቀጣይ የተጠናከረ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚንቀሳቀስ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር እና የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል።
መቀዛቀዝ የታየበትን የህዝባዊ ተሣትፎ ለማነቃቃት የተለያዩ መድረኮችን በቀጣይነት እንደሚያዘጋጅ የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ገልጸዋል።
◌ ቪዲዮ፦ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ድጋፍ ዙሪያ ከኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ጋር የተደረገው ውይይት
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ከንቅናቄ መድረኮች አንዱ የሆነው ሁሉም የዳያስፖራ አካላት የሚገኙበት መድረክ በራስ ሆቴል መድረክ አዘጋጅቶ ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋር በቀጣይነት እና በተሻለ ሁኔታ ግድቡን ሊደግፉ በሚችሉበት መንገድ ላይ ውይይት አድርጓል።
ዳያስፖራው ባለፉት ሰባት ዓመታት 46 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን ሃገሪቱ ካላት ዲያስፖራ ቁጥር አንጻር ድጋፉ አነስተኛ መሆኑ ተጠቁሟል። በመሆኑም በተለይም በምዕራብ አውሮፓ የሚገኙ ዲያስፖራዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል ድጋፍ ስላላደረጉ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ የዳያስፖራ ማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም አስታውቋል።
ለዚህም ዳያስፖራው ለህዳሴው ግድብ አዲስ የዳያስፖራ ተሳትፎ ንቅናቄ ለመፍጠር እና በዳያስፖራው ዘንድ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ያለውን ብዥታ ለማጥራት መድረክ ፈጥሮ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እንደነበርና፣ የራስ ሆቴሉ ውይይትም የዚሁ ዋነኛ አካል እንደነበር ተገልጿል። በተመሳሳይ ሁኔታም በዕለቱ የተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶች የሚሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ በካፒታል ሆቴል ተካሂዶ ነበር።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሁለት ዓመት በኋላ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር የተገለጸ ሲሆን ከአራት ዓመት በኋላ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
ምንጭ፦ ዋልታ ሚዲያ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- በመንግስትና በግል አጋርነት የሚሠሩ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ይፋ ሆኑ
- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
- “በምንም ተአምር ለኢትዮያ ሕዝብ ውሸት አልነግርም” ከኮሚሽነር ጄነራል ዘይኑ ጀማል ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ
- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራዎችን በአዲስ ኃይል ወደቀድሞ ፍጥነት ለመመለስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
- ቮልስዋገን በኢትዮጵያ የመኪና መገጥጠሚያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፤ የጀርመን የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በስፋት ለመግባት እያመቻቹ ነው
February 12, 2019 at 3:04 am #9640AnonymousInactiveለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የህብረተሰቡን አመኔታ ማሳደግ ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን
—–ለቀጣይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም ስኬት ዳግም በህብረተሰቡ ዘንድ አመኔታ ማሳደግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት በዛሬው ዕለት 10ኛ መደበኛ ጉባኤን አካሂደዋል፡፡
ምክር ቤቱ ጉባኤውን በቀድሞ የግድቡ ሥራአስኪያጅ ኢንጂነር ሰመኘው በቀለ ህልፈት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነው የጀመረው፡፡
በጉባኤውም የህዝባዊ ንቅናቄን የሚያሳዩና የግድቡ አጠቃላይ ቴክኒካል ሪፖርትን የሚያሳዩ ሁለት ሪፖርቶች ቀርቧል፡፡
በጉባኤው ላይ የተገኙት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ከታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ጋር መተማመንን የማጉልበት ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መላው ኢትዮጵያውያን በታላቁ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ተጠናከሮ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 6 ወራት ግማሽ ቢሊዮን ብር ገደማ የሚደርስ የቦንድ ግዥ የተከናወነ ሲሆን የኢትጵያውያን አሻራ የሆነው የህዳሴው ግድብ ላይ የህዝቡን ተሳትፎ ለማጠናከር ችግሮችን በመፈተሸ እንደሚሰራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገልጸዋል፡፡
በግድቡ ቴክኒካል ሪፖርት ላይ የሲቪል ሥራዎች 82 በመቶ መድረሱና የኃይል ማመንጫ ተርባይንና ቴክንክ ሥራዎቹ ብዙ እንደሚቀራቸው ተገልጿል፡፡
ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ የብረታብረት ሥራ ጥራትን ማረጋገጥ፣ የወንዝ አቅጣጫ ማስቀየሪያና ማስተንፈሻን ማጠናቀቅ ጋር ተያይዞ ሥራውን ከሚያከናወኑ ተቋማት ጋር ተጨማሪ ስምምነቶችን በፍጥነት ተፈራርሞ ወደ ሥራ ለመግባት ትኩረት መሰጠቱ ተነግሯል፡፡
በቀጣይ ሁለት ዓመታት ሁለት ተርባይነሮችን ማስጀመርና በቀጣይ አራት አመት ውስጥ ግድቡን በማጠናቀቅ ሥራ ለማስጀመር በሁሉም በኩል ርብርብ ይደረጋልም ተብሏል፡፡
እስከአሁን ግንባታውን ለሚያከናውነው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን የተከፈለውን 25 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ጨምሮ ከ98 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ተገጸዋል፡፡
ለህዳሴ ግድብ ግንባታው ስባል ከአካባቢው ተነስተው በተለዋጭ ቦታ ለሰፈሩ ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አባወራዎች የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርናና መሰል የመሰረተ ልማት ግንባታ 70 በመቶ መድረሱም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
በጉባኤው የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽ ተሰጥተውበታል፡፡
ምንጭ፦ ዋልታ ሚዲያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.