ለሥራ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ለመጓዝ የሚፈልጉ ዜጎች ሊያውቋቸው የሚገቡ መሠረታዊ ጉዳዮች

Home Forums Semonegna Stories ለሥራ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ለመጓዝ የሚፈልጉ ዜጎች ሊያውቋቸው የሚገቡ መሠረታዊ ጉዳዮች

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #10732
    Semonegna
    Keymaster

    መንግስት በሀገር ውስጥ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን በማስፋፋት ለሥራ ፈላጊ ዜጎች አስፈላጊውን ጥቅም ለማዳረስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። መሥራት ለሚችሉ ዜጎች ሁሉ በሀገር ውስጥ ላሉ የሥራ ዕድሎች ቅድሚያ በመስጠት ሠርተው የሚለወጡበትን ሁኔታዎች በማመቻቸት ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል።

    ኢትዮጵያ ውስጥ ሠርቶ ለመኖር በርካታ መልካም አጋጣሚዎች አሉ። ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑ በሀገራቸው ሠርተው የተለወጡ በርካታ ወጣቶችን መጥቀስ ይቻላል።

    ከዚህ ባለፈ ወደ ውጭ ሀገራት ለሥራ መሄድ የሚያስቡ ዜጎች እራሳቸውን ከአቻ ግፊትና ከሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሊጠብቁ ይገባል። ዜጎች ስለሚሄዱበት ሀገር ስላለው እውነታ ያላቸው ግንዛቤና መረጃ ውስንና የተዛባ በመሆኑ ከመሄዳቸው በፊት ስለሚሄዱበት ሀገር ባህል፣ ወግና ልማድ መረዳትና እና የዜጎችን መብት ደህንነትና ክብር ለማስጠበቅ ሲባል በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 923/2008 ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል።

    ለጉዞ ከመነሳታችን በፊት ምን ማወቅ ይጠበቅብናል?

    ወደ ውጭ ሀገር ሄደን ለመሥራት በምናስብበት ወቅት ጊዜ ሰጥቶ ማሰብ ይገባል። ለምን እንደምንሄድ፣ ከሄድን በኋላ የሚያጋጥሙንን መልካምና መጥፎ አጋጣሚዎች እንዴት መቋቋምና ማለፍ እንደሚገባን፣ የምንሄድበትን ሀገር ባህል፣ ወግ፣ ልማድና ስርዓት እንዴት ተላምደን መኖር እንደምንችል፣ የሠራንበትን ገንዘብ ወደ ሀገራች እንዴት መላክና መቆጠብ እንደምንችል፣ ኮንትራታችንን ጨርሰን መቼ ወደ ሀገራችን መመለስ እንዳለብን አስቀድመን ማቀድ ያስፈልጋል።

    በአዋጅ ቁጥር 923/2008 መሠረት በውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ፣ 8ኛ ክፍል ያጠናቀቁ (ወደ 9ኛ ክፍል የተዛወሩ)፣ በሚሄዱበት የሥራ መስክ ስልጠና ወስደው የብቃት ማረጋገጫ ያገኙ፣ የቅድመ ጉዞ ስልጠና ወስደው ሰርተፊኬት የያዙ፣ የጤና ኢንሹራንስ የተገባላቸው፣ ሙሉ የጤና ምርምራ ያደረጉና ከወንጀል ነጻ ሊሆኑ ይገባል።

    ይህን ያሟሉ ዜጎች በአስቀጣሪ ኤጀንሲ በኩል ወይም በራሳቸው አማካኝነት ሥራውን በማፈላለግ ማለትም በቀጥታ ቅጥር አስፈላጊውን የቅጥር ፎርማሊቲ በማሟላት ቪዛውን አግኝተው መሄድ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ በቀጥታ ቅጥር የሚጓዙ ሠራተኞች መደበኛ ስልጠና የወሰዱና ከቤት ሠራተኝነት ውጭ በልዩ ልዩ ሙያዎች የሰለጠኑ ሲሆን የሚሠሩትም በካምፓኒና በልዩ ልዩ አነስተኛ የቢዝነስ ተቋማት ውስጥ ነው። ከዚህ በፊት በውጭ ሀገር ሠርተው የተመለሱ ልምድ ይኖራቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ መረጃ ማቅረብ የሚችሉ ከሆነ ስልጠናውን መውሰድ ግዴታ ባይሆንም የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

    ለሥራ የት ሀገር ነው መሄድ የሚቻለው?

    ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቤት ሠራተኝነት የሚሄድ ከሆነ ሊጓዝ የሚችለው በኤጀንሲዎች አማካኝነት ብቻ መሆኑን ሊረዳ ይገባል። የሥራ ስምሪት ማድረግ የሚችለውም አገሪቷ የሁለትዮሽ ስምምነት ወደተፈራረመችባቸው ሀገራት ብቻ ነው። የሁለትዮሽ ስምምነት የተፈፀመባቸው መዳረሻ ሀገራት ለጊዜው ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታርና ጆርዳን ሲሆኑ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚደረገው ስምምነትም በሂደት ይቀጥላል።

    ስምምነት በተፈፀመባቸው ሀገሮች የደመወዝ መጠን ስንመለከት ከኳታር መንግስት 1200 ለቤት ሠራተኛና 1300 ለእንክብካቤ (care giver) የኳታር ሪያል፣ ከጆርዳን መንግስት ለጀማሪ 225 ዶላር፣ ልምድ ላላው 250 ዶላር፣ ከሳውዲ አረቢያ መንግሰት ጋር 1000 የሳውዲ ሪያል እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሷል።

    በሠራተኞችና በአሠሪዎች የሚሸፈኑ ወጪዎች

    አንድ ሠራተኛ በሥራ ለመሰማራት አስፈላጊውን መስፈርት ካሟላና ብቁ ከሆነ በአዋጁ የተደነገጉ የቅጥርና ምልመላ መንገዶችን በመከተል አስፈላጊውን መፈጸም እና ወጪዎችን መሸፈን ይገባል።

    1. አሠሪው ወይንም ኤጀንሲው የሚሸፍናቸው ወጪዎች

    በአሠሪው የሚሸፈኑ ወጪዎች ሠራተኛውን ወደ ተቀባይ አገር ለማድረስ፣ በተቀባይ አገር ያለችግር እንዲቆይና እንዲሠራ ለማድረግ፣ እንዲሁም በሥራ ላይ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚወጡ ወጪዎች ናቸው።

    እነርሱም የተቀባይ አገር የመግቢያ ቪዛ፣ የደርሶ መልስ መጓጓዣ፣ የሥራ ፍቃድ፣ የመኖሪያ ፍቃድ፣ የሥራ ውል ማጽደቂያ ክፍያዎች፣ የመድህን ዋስትና ሽፋን እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኝ የተቀባይ አገር ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ጽህፈት ቤት የሚከፈል ከቪዛና ከሰነድ ማረጋገጥ ጋር የተያያዘ ማናቸውም ወጪዎች ናቸው።

    1. በሠራተኛው የሚሸፈኑ ወጪዎች

    አንድ ሠራተኛ ለሥራ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በሚጓዝበት ወቅት የሚያወጣው ወጪ በአብዛኛው በህይወት ዘመኑና በማህበራዊ ህይወቱ ውስጥ የትኛውም ሰው ስለሚጠቀምባቸው የሚያወጣቸው ወጪዎች ናቸው።

    እነርሱም ለልደት ሰርተፊኬት፣ ለፓስፖርት፣ ለክትባት፣ ለህክምና ምርመራ፣ ለሙያ ብቃት ማረጋገጫ፣ ከወንጀል ነፃ ማስረጃ ማረጋገጫ ወጪዎች ናቸው። እነኝህ ክፍያዎች በሙሉ አገልግሎቱን ለሰጡ ሌሎች መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት የሚከፈል እንጂ ምልመላውን ለሚያከናውነው ኤጀንሲ የሚከፈል አይደለም። ኤጀንሲው ምንም አይነት ክፍያ ከሠራተኛው ቢጠይቅ ህገወጥ ያደርገዋል።

    ይሁን እንጂ ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ አስፈላጊ ሁኔታዎች ተጠናቀው ያለበቂ ምክንያት ሠራተኛው ወደ ሥራ ባይሰማራ ከቅጥሩ ጋር በተያያዘ አሠሪው ያወጣውን ወጪ ሠራተኛው እንዲከፍለው ሊጠይቅ ይችላል። በተመሳሳይ መንገድ በተራ ቁጥር 2 ላይ የተጠቀሱትን ወጪዎች ሠራተኛው አውጥቶ በራሱ ጉድለት ባልሆነ ምክንያት በሥራ ላይ ካልተሰማራ ኤጀንሲው ወይም አሠሪው የሠራተኛውን ወጪ የመተካት ግዴታ ይኖርበታል።

    ለውጭ አገር ለሥራ ስምሪት የሚሰጡ ስልጠናዎችና ማሰልጠኛ ተቋማቱ

    ለውጭ አገር ሥራ ስምሪት የሚሰጡ ስልጠናዎች ሶስት ሲሆኑ እነሱም በቤት አያያዝ (Household Service) በቤት ውስጥ ሥራ (Domestic Help) እና በእንክብካቤ ሥራ (Care Giving) ናቸው።

    የእነዚህ ሙያዎች የስልጠና መሳሪያዎች፣ የሙያ ደረጃ፤ ሥርዓተ ትምህርት እና የብቃት ማረጋገጫ ምዘና መሳሪያዎች ሲዘጋጁ ለማንኛውም ዜጋ እንዲያገለግል ሲሆን ወንድም ሆነ ሴት በፍላጎቱ ሊሰለጥን ይችላል። ሠልጣኞች ስልጠናውን በግላቸው ሊሠሩበት፣ በአገር ውስጥ ሊቀጠሩበት እንዲሁም ወደውጭ አገር ሊሰማሩበት እንደሚችሉ ሊገነዘቡና በምልመላ ወቅትም ሊነገራቸው ይገባል። በተጨማሪም በስልጠናው የተሳተፈ ሁሉ የብቃት ምዘናውን ያልፋል ማለት አይደለም፣ የብቃት ምዘናውን ያለፈ ሁሉ ቀጣሪ ያገኛል ማለትም አይደለም። በመሆኑም በተጠቀሱት ሙያ እንዲሰለጥኑ የተደረጉ ሁሉ ወደአረብ ሀገር መሄድን እንደመብት ሊያዩት አይገባም።

    ይሁን እንጂ ወደአረብ አገር መሄድ የሚፈልጉ ሰልጣኞች ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ሙያዎች ከሰለጠኑ በኋላም የብቃት ምዘና ማረጋገጫ ተፈትነው ማለፍና ሰርተፊኬት መያዝ ይኖርባቸዋል። ስልጠናው በየክልላቸውና በአቅራቢያቸው በሚገኙ በተመረጡ ማሰልጠኛ ተቋማት ይሰጣል። ስልጠናው በየክልላቸውና አቅራቢያቸው የመሰጠቱ ጠቀሜታም የሠራተኞች ምልመላ በየክልላቸው የሚካሄድ በመሆኑ፣ አስፈላጊ መረጃዎችን ለማጣራትና ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን ደህንነትና ክብር በቅርብ ለመከታተል እና ከስልጠና፣ ከምልመላ ጋር ተያይዞ ለአላስፈላጊ ወጪና የመብት ጥሰቶች እንዳይጋለጡ ያግዛል።

    ስልጠናን በተመለከተም፣ የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት ትምህርቱን በነፃ የሚሰጡ ሲሆን ማንኛውም ሰልጣኝ በክልሉ በሚገኝ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ወይም በየዞኑና ክፍለ ከተማው ወይም ወረዳዎች በሚገኙ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤቶች በመመዝገብ ለየማሰልጠኛዎቹ በመላክ እንዲሰለጥኑ ይደረጋል።

    በተጨማሪም የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት የተደራሽነትና የአቅም ውስንነት ስላለባቸው በፌደራልና በክልል በሚገኙት የቴ/ሙ/ት/ስ/ኤጀንሲ ቢሮዎች ለግል ማሰልጠኛ ተቋማት ፍቃድ በመስጠት በማሰልጠን ሥራው እንዲሳተፉ ተደርጓል። በመሆኑም የግል ማሰልጠኛ ተቋማት የስልጠና ጥራታቸው ላይ ጥንቃቄ በማድረግና አስፈላጊ የስልጠና ቁሳቁሶችን በማሟላት የትምህርቱን ጥራት እንዲጠብቁ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ፍቃድ ሰጪ አካላትም የጀመሩትን ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ በማጠናከር እገዛ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።

    በየክልሉ የተመረጡ የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት ዝርዝር

    በመንግስት የተመረጡ 66 ማሰልጠኛ ተቋማት ሲሆኑ ስልጠናውም በሁሉም ክልል በነፃ ይሰጣል።

    የማሰልጠኛ ተቋማት ዝርዝር በየክልሉ፡-

    አማራ ክልል

    1. ባህርዳር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    2. ወልድያ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    3. ደሴ ወ/ሮ ስህን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    4. ከሚሴ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ
    5. ደ/ብርሃን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    6. ጎንደር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    7. እንጂባራ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    8. ቡሬ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ
    9. ደብረታቦር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    10. ደብረ ማርቆስ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    11. ሠቆጣ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ

    ደቡብ ክልል

    1. አዋሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    2. አርባ ምንጭ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    3. ሶዶ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    4. ዱራሜ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
    5. ሆሳዕና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    6. ወራቤ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
    7. ወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    8. ቡታጅራ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
    9. ሀላባ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
    10. ይርጋለም ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
    11. ዲላ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ

    ትግራይ ክልል

    1. መቀሌ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    2. ዶ/ር ተወልደ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ
    3. አክሱም ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    4. ዶ/ር አርዕያ ካሳ ኮሌጅ
    5. ውቅሮ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
    6. (ማይጨው) ጥላሁን ይግዛው ፖሊቴክኒክ
    7. አላማጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ

    አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

    1. እንጦጦ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና (ቴ/ሙ/ት/ስልጠና) ኮሌጅ
    2. ጄነራል ዊንጌት ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
    3. ንፋስ ስልክ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
    4. ምሥራቅ አጠቃላይ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
    5. የካ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
    6. ልደታ ማኒፋክቸሪንግ ኮሌጅ
    7. አዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
    8. ቂርቆስ ማኒፋክቸሪንግ ኮሌጅ
    9. አቃቂ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ

    ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር

    1. መለስ ዜናዊ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ

    ኦሮሚያ ክልል

    1. ሀሮማያ ቴክኒክና ሙያ
    2. አሰላ ቴክኒክና ሙያ
    3. ሻሸመኔ ቴክኒክና ሙያ
    4. መርቲ ፖሊ ቴክኒክ
    5. ቢሾፍቱ ቴክኒክና ሙያ
    6. ጂማ ቴክኒክና ሙያ
    7. መቱ ቴክኒክና ሙያ
    8. መቱ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ
    9. ነቀምት ቴክኒክና ሙያ
    10. ነቀምት ጤና ሳይንስ ኮሌጅ
    11. ባቱ ተራራ ቴክኒክና ሙያ
    12. ዶና ባርበር ቴክኒክና ሙያ
    13. ፍቼ ቴክኒክና ሙያ
    14. መርቲ ፖሊ ቴክኒክ
    15. አዳማ ፖሊ ቴክኒክ
    16. አብቦ ፖሊ ቴክኒክ
    17. ሰበታ ፖሊ ቴክኒክ
    18. ወሊሶ ፖሊ ቴክኒክ
    19. አጋሮ ፖሊ ቴክኒከ
    20. አደላ ፖሊ ቴክኒክ
    21. ቡሌ ሆራ ፖሊ ቴክኒክ
    22. ጨርጭር ፖሊ ቴክኒክ
    23. ደደር ፖሊ ቴክኒክ
    24. አርሲ ነገሌ ፖሊ ቴክኒክ
    25. ሀሰሳ ፖሊ ቴክኒክ
    26. ጊምቢ ፖሊ ቴክኒክ
    27. ወንጂ ፖሊ ቴክኒክ

    ምንጭ፦ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ለሥራ ወደ መካከለኛው


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.