Home › Forums › Semonegna Stories › ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እየተገነባ ያለው መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል እየተጠናቀቀ ነው
Tagged: መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 4 years, 4 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
July 27, 2020 at 1:45 am #15197SemonegnaKeymaster
ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እየተገነባ ያለው መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል እየተጠናቀቀ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እየተገነባ ያለው መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ። በቀጣዩ ዓመት ተጨማሪ 3 ሺህ የከተማ አውቶቡሶችን ለማሰማራት የግዥ ሂደት ላይ መሆኑንም የትራንስፖርት ቢሮው አክሎ አስታውቋል።
በቢሮው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መሀንዲስ ኢ/ር ናትናኤል ጫላ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደጠቆሙት፥ መንግሥት በመደበው ከፍተኛ በጀት መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል ግንባታው ከነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በመከናወን ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከ87 በመቶ በላይ መድረሱንም ኢ/ር ናትናኤል አመልክተዋል።
በዘመናዊ መልኩ እየተገነባ ያለው መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ያሉት መሆኑንም ኢ/ር ናትናኤል ጨምረው ጠቅሰዋል። ከነዚሁ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መካከል ዘመናዊ የትኬት መቁረጫ፣ የደህንነት መቆጣጠሪያ፣ የተገልጋይ ማረፊያ፣ ለአቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች አገልግሎት የሚውል ዘመናዊ አሳንሰር፣ የመረጃ ማዕከልእና የተገልጋይ መጸዳጃ ቤቶች ይገኙበታል።
በመሀል ገበያ 4 ሺህ ካሬ ስፋት ባለው ቦታ ላይ የሚገነባው የአውቶቡስ ተርሚናል ባለ ሁለት ወለል ከፍታ ያለው መሆኑን ኢ/ር ናትናኤል አስረድተዋል። በአፍሪካ ትልቁ ክፍት የገበያ ማዕከል በሆነው መርካቶ በአንድ ቀን ብቻ ከ50,000 እስከ 80,000 ገበያተኛ ሕዝብ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግበት የሚገመት ሲሆን የአውቶቡስ ተርሚናሉ በዚህ የገበያ ማዕከል አቅራቢያ መገንባቱ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባብሪያ ጽሕፈት ቤት በከተማዋ ውስጥ አራት (ማለትም፥ መርካቶ፣ ፒያሳ፣ ሰሚት እና መገናኛ አካባቢዎች) ዘመናዊ የአውቶቡስ ተርሚናሎችን ለመገንባት ከ2008 ዓም ጀምሮ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል።
ከሚገነቡት ተርሚናሎች ውስጥ አስተዳደሩ በ2013 ዓ.ም በመገናኛ አካባቢ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አንድ ዘመናዊ የብዙኃን ትራንስፖርት ተርሚናል ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ኢ/ር ናትናኤል ጠቁመዋል። ይህ የአውቶቡስ ተርሚናል ተገንብቶ ሲጠናቀቅዘመናዊ ተርሚናሉ የአንበሳ አውቶቡስ፣ ሸገር ባስንና ታክሲዎችን ጨምሮ የተለያዩ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በማጣመር በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኢ/ር ናትናኤል እንዳሉት የመገናኛው የአውቶቡስ ተርሚናል በአንድ ሄክታር ቦታ ላይ የሚገነና እና ባለስምንት ወለል ሲሆን አራቱ ወለሎች የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥበት ነው። በተጨማሪም የፈጣን አውቶቡስ፣ የታክሲ እና የቀላል ባቡር አገልግሎቶች በጣምራ የሚሰጥበት መሆኑንም አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ ለእግረኞች አገልግሎት የሚውል አንድ ዘመናዊ ድልድይና 200 መኪኖችን በአንድ ቦታ ለማስቆም በሚያስችል የመኪና ማቆሚያ ቦታ (ፓርኪንግ) እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የብዙኃን ትራንስፖርትን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ኢንጅነር ናትናኤል፥ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት ግንባታን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ከእነዚህ ሥራዎች ጎን ለጎን በከተማዋ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን 1 ሺህ የከተማ አውቶቡሶች ቁጥር ለማሳደግ በቀጣዩ ዓመት 3 ሺህ አውቶቡሶችን ግዥ ለመፈጸም እተሠራ መሆኑንም ኢ/ር ናትናኤል ጨምረው ገልጸዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.