Home › Forums › Semonegna Stories › መርፌ ጨርቅ እንጂ አለት አይበሳም ― ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የምክር ደብዳቤ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 8 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
March 20, 2019 at 9:35 pm #10327SemonegnaKeymaster
አዎ አገር እንደ እንደ ካልጠነከረች በመርፌ ስለት በቻ ሳይሆን በዶለዶመ ብረትም ትበሳለች። የመርፌ አቅሙ ጨርቅ ወይም እንደ ጨርቅ በሳሳ ነገር ላይ ነው። ኢትዮጵያ አገራችን ደግሞ ከመቼውም በከፋ ሁኔታ ሳስታለች።
ያሬድ ኃይለማርያም
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትላንትናው እለት የማኅበራዊ ሚዲያዎችን አጠቃቀም በተመለከተ ምክር አዘል ተግሳጽ የያዘ ደብዳቤ ከጽሕፈት ቤታቸው ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል። እርግጥ ነው ጠቅላዩ እንዳሉት ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚተላለፉ ጽንፍ የያዙ እሰጣገባዎች፣ በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጸያፍ ንግግሮች፣ ሕዝብን ለግጭት የሚቀሰቅሱ ጥሪዎች፣ የሃሰት መረጃዎች እና ውንጀላዎች ከመቼው ጊዜ በስፋት እየተስተዋሉ መጥቷል። ይህ ዓይነቱ ችግር በጊዜ ካልታረመ የእርስ በርስ ንቁሪያው ከማኅበራዊ ሚዲያ ወደ መሬት ወርዶ በግልም ሆነ በአገር ደረጃ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ደብዳቤያቸው በግልጽ አስቀምጦታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ጽንፍ ይዘው እና የተሳሳቱ መረጃዎችን እያሰራጩ ሕዝብን የሚያደናግሩ እና ለግጭት የሚያነሳሱ ሰዎችን በመርፌ መስለው አስቀምጠዋል። እንዲህም ይላሉ “መርፌ ዓይናማ ናት ባለ ስለት፤ ችግሩ የፊቷን እንጂ የሚከተላትን አታይም። እናም ጨርቅ ላይ እሷ አለፍኩ ብላ የክር እና የገመድ መአት ታስገባበታለች። የእኛ አገር አንዳንድ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ጦማሪዎች ልክ እንደ መርፌ ናቸው። እነሱ አገር በሚወጋ መርፌያቸው እየወጉን ሲጓዙ እንደ ክር አያሌዎች መድረሻቸውን ሳይጠይቁ ይከተሏቸዋል…” አገላለጻቸው ግሩም ነው። ወድጄዋለሁም፤ ነገር ግን እውነቶች ይጎድሉታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁኔታውን አንድ ገጽታ ብቻ ነው እንደ ዋነኛ ምክንያት ወስደው እና አትኩሮት ሰጥተው ስጋታቸውንና ማሳሰቢያቸውን የሰጡት። እኔ ያላዩት ወይም ችላ ብለው ያለፉት ገጽታ አለ እላለሁ። መርፌ ጨርቅ እንጂ አለት አትሰፋም ወይም አይበሳም።
አዎ አገር እንደ እንደ ካልጠነከረች በመርፌ ስለት በቻ ሳይሆን በዶለዶመ ብረትም ትበሳለች። የመርፌ አቅሙ ጨርቅ ወይም እንደ ጨርቅ በሳሳ ነገር ላይ ነው። አገራችን ደግሞ ከመቼውም በከፋ ሁኔታ ሳስታለች።
አገር እንደ አለት የሚጸናው በጥሩ ሕግ፣ የሕግ የበላይነትን በሚያረጋግጡ ጠንካራ ተቋማት፣ ሕግን በሚያከብሩ እና በሚያስከብሩ የመንግስት ተቋማት እና ሕግ አክባሪ በሆነ ማኅበረሰብ ነው።
በሁሉም አለም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ጥሩም፣ መጥፎም ገጽታ አላቸው። የሕግ የበላይነት በሳሳበት እና መንግስት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ባልቻለበት ስፍራ አሉታዊ ጎኑ ይበረታና አገር እሰከ ማተራመስ አልፎም እስከ ማፍረስ ይደርሳል። በሕግ የጸና ጠንካራ አገር እና ሕግ አክባሪ ማብሀረሰብ ባለበት አገር ደግሞ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ጩኸት ሰሚ አልባ ነው። እዛው አየር ላይ ተንሳፎ ይቀራል።
ክቡርነትዎ፥ የእኛ አገር የማኅበራዊ ድረ-ገጾች መረን የለቀቀ የእርስ በርስ ንቁሪያ እኮ መሬት ላይ ያለው እውነታ ነጸብራቅ ነው። እርሶ በተቀመጡባት መዲና አዲስ አበባ ሳይቀር ሰዎች ሜጫ፣ ድንጋይ፣ ሚስማር የተመታበት ዱላ ይዘው አደባባይ ለፍልሚያ በየቀኑ በሚወጡበት እና ዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት የማይችሉበት አደጋ መሬት ላይ እየታየ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው ጦርነት እንብዛም ትኩረት ሊስብ አይገባውም።
አገሪቱን እንደ ጨርቅ ያሳሳት እንደ እኔ እምነት የመርፌው ጥንካሬ ሳይሆን መንግስት የሕግ የበላይነትን በመላ አገሪቱ ማስፈን አለመቻል ነው። እባክዎ ቅድሚያ አየር ላይ ካለው የቃላት ጦርነት በፊት መሬት ላይ ሕግ ያስከብሩ። የእርሶ ጽሕፈት ቤትም አይደል እንዴ በአደባባይ እና በማኅበራዊ ሚዲያ በሕዝብ ላይ የእልቂት እና የግጭት አዋጅ አውጆ ለቄሮ የክተት ጥሪ ያደረገውን ጃዋር መሃመድን በሕግ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ በቅርቡ በኢሲኤ (ECA) አዳራሽ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ በአገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምን አስመልክቶ ትምህርት እንዲሰጥ ዋና ተናጋሪ አድርጎ ያቀረበው።
ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ያሉት ችግሮች እና ስጋትዎን እኔም ሙሉ በሙሉ እጋራዎታለው። ጽንፈኝነት ነግሷል። የሃሰት መረጃዎች ሕዝብን እያደናገሩ ነው። እኔም ሆንኩ ሌሎች ሚዲያውን የሚጠቀሙ አካላት እርሶንም ጨምሮ ለችግሩ አስተዋጽኦ ይኖረን ይሆናል። ይህ ችግር አገር ሳያሳጣን በፊት በአግባቡ እና በአፋጣኝ ሊፈታ ይገባል። ኢትዮጵያን እንደ አለት የጸናች አገር ማደረግ ከቻልን ግን የማኅበራዊ ሚዲያው ጩኸትም ሆነ ትርምስ ንፋስ ይወስደዋል ወይም እየነጠረ ይመለሳል እንጂ አገር አያፈርስም።
አዎ እርሶ እንዳሉት ኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ያላት አገር ስለሆነች በማኅበራዊ ሚዲያ ወሬ አትፈርስም። መሬት ላይ ያለው ሕግ አልባነት፣ የመንጋ እንቅስቃሴ እና በሕግ ያልተገራና ልቅ የሆነ የግለሰቦች እና የፓርቲዎች እንቅስቃሴ ግን የሞት አፋፍ ሊያደርሳት ይችላል።
የሕግ የበላይነት ትኩረት ይሰጠው!
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.