Home › Forums › Semonegna Stories › በመቀሌ ከተማ በ147 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ምርት ማከፋፈል ጀመረ
Tagged: ሃፍቶም ፋንታሁን, መቀሌ, ትግራይ ክልል
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 1 month ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 13, 2018 at 10:16 am #8061SemonegnaKeymaster
በመቀሌ ከተማ በ147 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሙሉ ብርሃን ኢንዱስቱሪና ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ያቋቋመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
መቀሌ (ኢዜአ) – በ147 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ገመድ ተሸካሚ የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ምርት ማከፋፈል መጀመሩን አስታወቀ።
“ሙሉ ብርሃን ኢንዱስቱሪና ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር” በሚል የተቋቋመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ እሥራኤል ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት ፋብሪካው በአገር አቀፍ ደራጃ ያለውን የኮንክሪት ምሶሶ ችግር ለመፍታት ታሳቢ ተደርጎ የተቋቋመ ነው።
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 90 የሚደርስ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ምሶሶዎችን በማምረት ላይ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር በቀን እስከ 300 የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ምሶሶዎችን የማምረት አቅም እንደሚኖረው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመነጋገር ፋብሪካው ምርቶቹን ለትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ማከፋፈል መጀመሩን አቶ እሥራኤል አስታውቀዋል።
ፋብሪካው ከአገር ውስጥ ስሚንቶ፣ አሸዋና ጠጠር የሚጠቀም ሲሆን ለምሶሶው መሥሪያ የሚውሉ ብረቶችን ከውጭ በማስገባት ለአገልግሎት ያውላል።
ፋብሪካው በሚያመርተው ምርት መንግስት በከተማና በገጠር የኤሌክትሪክ ሽፋን ለማዳረስ እያከናወነ ላለው ሥራ አጋዥ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት በቦታ አቅርቦትና ብድር በማመቻቸት እገዛ እንዳደረገላቸው የገለጹት አቶ እሥራኤል ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት እንዲችል ከውጭ ለሚመጡ ጥሬ ዕቃዎች መግዣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትግራይ ቅርንጫፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርቶች ማምረት መጀመሩን ተናግረዋል።
የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው በመቀሌ ማምረት መጀመሩ ከአሁን ቀደም ከአዲስ አበባ ለማጓጓዝ ለትራንስፖርት ይወጣ የነበረውን ወጪ ይቀንሳል ብለዋል።
ከፍትኛ የኤሌክትሪክ ምሶሶዎች ለ20 ዓመታት ዋስትና ያላቸው መሆኑን የገለጹት ሥራ አስፈፃሚው ካሁን በፊት ለአገልግሎት ይውሉ የነበሩ የባህርዛፍ ምሶሶዎች በጉዳት ምክንያት ያደርሱ የነበሩትን አደጋና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሚቀንስ ነው።
የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃፍቶም ፋንታሁን እንደገለጹት የምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው በመቀሌ ከተማ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ቦታ ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል በፍጥነት ወደ ማምረት ሥራ መሸጋገር መቻሉ በአርያነቱ እንዲቀመጥ የሚያደርገው ነው።
የትግራይ ክልል የተረጋጋ ሰላም ያለው በመሆኑ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል።
በመካኒካል ምህንድስና የተመረቀው ወጣት አማኑኤል ሀይሉ በፋብሪካው በመቀጠር በወር 6ሺህ ብር የወር ደሞዝ እየተከፈለው ይሠራል። በፋብሪካው የሥራ እድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን የሚናገረው ወጣት አማኑኤል ገቢ ማግኘት መጀመሩ ከቤተሰብ ጥገኝነት ወጥቶ የራሱን ቤተሰብ ለመመስረት መቻሉን ገልጿል።
ወጣት ዙፋን ኪዳኑ በበኩሏ “ማኅበሩ በዘርፉ ኢንቨስት በማድረጉ የአካባቢውን ወጣቶች የሥራ አድል ተጠቃሚ አድርጎናል” ብላለች።
በትግራይ ክልል በ2010 ዓ.ም 24 ቢልዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺህ 328 ባለሀብቶች በሥራ እንዳሉ ከክልሉ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመልክታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.