Home › Forums › Semonegna Stories › መንግሥት ሆይ፥ የጤና ባለሙያውን ጥያቄ ከልብህ አድምጥና መፍትሄ ስጥ
Tagged: ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 7 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
May 18, 2019 at 1:20 am #10890SemonegnaKeymaster
መንግሥት ሆይ፥ የጤና ባለሙያውን ጥያቄ ከልብህ አድምጥና መፍትሄ ስጥ
(ዶ/ር አክሊሉ ደበላ)አሁን ነገሮች ወዴት እያመሩ እንደሆነ ሁሉም እያየው ነው። አነሰም በዛ መንግሥትም በዚህ ምክንያት መጨነቁ አልቀረ። በዚህ ችግር የሚነካካ አካል ብዙ እንደሆነም አምናሁ። የጤና ባለሙያው፣ መንግሥትና ሕዝብ ሳይወዱ በግድ ባለጉዳዮች ናቸው። የባለሙያው ጥያቄ ግልጽ ሆኖ ቀርቧል። በዚህ ጥያቄ ላይ የተለያየ አስተያየት ያላቸው ሰዎች አሉ። የሚሰጡትም አስተያየቶች ነገሩን የከፋ እንዳያደርጉ መጠንቀቅ ከሁሉም ይጠበቃል።
የሐኪሙ ጥያቄ ዛሬ የበቀለ የሚመስላቸው ተሳስተዋል። ጥያቄውም ሆነ ተግባር ያልታየበት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መልስ ሲንከባለሉ ቆይተው ዛሬ ወደ አደባባይ የወጡ ናቸው። “እስከዛሬ የት ነበራችሁ?” ማለት ቢቻልም በጥልቅ ሲታሰብ ልክ አይሆንም። የመቶ ዓመት ጥያቄ እንኳን ቢሆን የሆነ ጊዜ በሥርዓቱ መመለስ አለበት። ችግሮቹን የፈጠረ የዶ/ር አቢይ መንግሥት ነው ያለ የለም፣ መመለስ ያለበት ግን አሁን እሱ ነው። ሕዝቡ በደፈናው በሐኪሙ ላይ መጥፎ አስተያየት ከመስጠቱ በፊት ነገሩን አዙሮ አዟዙሮ ቢያስብ መልካም ነው። ዛሬ ገንፍሎ የወጣው ጩኸት የፖለቲካ ሁኔታ ምቹ ስለሆነ ብቻ አይደለም (መሆኑ አንድ ነገር ቢሆንም)፤ ይልቅስ እየተባባሰ የመጣው የችግሩ ተፈጥሮ ራሱ የመገንፈል ልክ ላይ ደርሶ ነው እንጂ። እዚህ ላይ የደረሰውን ጉዳይ ሁሉም በጥንቃቄ ካልያዘ ጉዳቱ ከተፈጥሯዊነት ይልቅ ሰው-ሠራሽ አንዳናደርገው።
ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተጠየቀውን ነገር ለመመለስ ምን ያህል እምነት የሚጣልበት አካል እንደሆነ አላውቅም። ነገሮችን እየመለሰ ያለበት አኳኋን ግን መልካም አይደለም። እስከሚገባኝ ድረስ በውይይቱም ላይ ለመመለስ ቃል የገባባቸው ጉዳዮች ራሱ ሲፈጽም የነበረ ሕግን የጣሰ አሠራር ነው። የሀገሪቷን ሕግ ጥሶ ወጪ መጋራትን (cost-sharing) ቢያስተካክል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሲሠራ የነበረውን የወንጀል ሂሳቡን አወራረደ ይባላል እንጂ የሐኪሙን ጥያቄ መለሰ ተብሎ ለዜና የሚቀርብ ጉዳይ አልነበረም። ወሃ የማይቋጥር ጥቃቅን ነገሮች አስር ጊዜ እንደሰበር ዜና የሚለጥፍበት መንፈስ ግን አስቂኝ ነው። ስጠረጥር ግን ባለሙያውን ንዴት ውስጥ በመክተት ይበልጥ እንዲገፉበት የፈለገም ይመስለላል። ከሳምንታት በፊት ሰምተን ያለቀውን ጉዳይ ዛሬ በሰበር ዜና ባገኘው ሚዲያ ሁሉ ማስተጋባት የቅንነት ልቡን የሚታመን አያደርገውም። ጊዜያዊ ስሜቱን ማብረድም ሆነ ዘላቂ መፍትሄውን በሰከነ መንገድ መመለስ ይጠበቅበታል እንጂ የብልጣብልጥነት ጨዋታ በመገናኛ ብዙሃን (ሚዲያ) በኩል መጫወት አይጠቅምም።
ሌላው ከዶ/ር አቢይ ጋር ተያይዞ፡- እንደሚታወቀው ባለፈ ከሕክምና ማኅበረሰብ ጋር ያደረገው ውይይት ብዙዎችን አስከፍቷል። በዚህም የተነሳ የብዙ ሐኪሞች የሥራ ሞራል ወርዷል፣ የብዙዎች ስሜት ቀዝቅዟል። በዚህ ብቻም የተነሳ ብዙ ህመምተኞች ይጎዳሉ፤ ተጎድተዋል። ይህ እንግዲህ ከጥያቄዎቻቸው ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ የሌለው ተጨማሪ ችግር ነው። የአንድ አገር መሪ በተናገረው ነገር የሚበላሸው ብዙ ነገር እንደሆነ ግልጽ ነው። የዚህንም ፍሬ አይተነዋል። ለዚህ ትክክለኛው መድኃኒት እርምት ነው። ስለ ባለሙያው ክብርም ባይሆን ስለሚበደሉቱ ህመምተኞች ሲባል፣ የተነገረውም በአደባባይ ስለሆነ፣ የዶ/ር አቢይ መንግሥት በአደባባይ ይቅርታ ቢጠይቅ አገር ትጠቀማለች።
ሌላው ከሕክምና ስነምግባርና ሀገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር የተለያየ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች አሉ። እርግጥ ነው ሀገሪቷ ገና አልተረጋጋችም፤ እርግጥ ነው የሐኪሞቹን ጥያቄ ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ሊያውሉ የሚፈልጉ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ። ይህን ለማስቀረት ኃላፊነት ያለበት ደግሞ ጠያቂው ሐኪም ብቻ ሳይሆን ተጠያቂው መንግሥትና ተመልካቹ ማኅበረሰብም ጭምር ነው። መመለስ ባለበት መንገድ ካልተመለሰ ባልተፈለገ መንገድም ሊወድቅ ይችላል፤ ስጋቱ የሁሉም ነው። ይህን ተፈጥሯዊ ዕጣውን በመዘንጋት ከየአቅጣጫ ጠያቂውን ብቻ መውቀስ ተገቢ አይደለም፤ ጥያቄውንም ማራከስ ይሆናል። እርግጥ ነው ሕክምና በተቻለው መጠን ሁሉ ህመምተኛን ማስቀደምን ይጠይቃል። ይህን ጠያቂዎቹም ያውቃሉ። ይሁንና የሕክምና ሥራ የሚሠራው ሰው ሆኖ መኖር ከተቻለ ብቻ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። በብዙ ቦታዎች ያለው እውነታ ደግሞ የደኅንነት ስጋት ጉዳይ ስለሆነ ከሁሉም ይቀድማል– ከሕክምናም። ይህን ችግር ግን ብዙ ሰው የተረዳው አይመስለኝም። ብዙዎቹ ጥያቄዎች ደግሞ ቀጥታ ለህሙማኑ ጥቅም የሚውሉ ናቸው። በአሠራር ብልሹነት መሥራት አልቻልንም ማለት እንደ አገር ቢታሰብ ትልቅ ችግር ነው እንጂ የሕክምና ባለሙያ ጥያቄ ብቻ ተደርጎ ባልተወሰደ ነበር።
ከማኅበራዊ ድረ-ገጾች ጩኸት እስከ ሥራ ማቆም ተደርሷል። ነገሮች በዚሁ የሚሄዱ ከሆነ ደግሞ ሥራ ማቆሙ እየተስፋፋ ሄዶ የብዙዎቹ ሕይወት እስከ መቅጠፍ ሊደርስ ይችላል። ማኅበራዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ጉዳይም ሊሆን ይችላል እና ሁሉም ቆሞ ቢያስብበት ሸጋ ነው። “መንግሥትስ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ላይ ሆኖ የሕክምና ባለሙያን ጥያቄ መመለስ ይችላል ወይ?” ከተባለ “አዎ ይችላል።” ምናልባትም ጊዜ የሚፈልጉ አንዳንድ ከባድ ጥያቄ የሆኑበትም ካሉ አመላለሱን ያማረ በማድረግ መተማመንን መፍጠር ይችላል። አሁን እየሄደ ባለበት መንገድ ግን አይደለም። ለዚህም ነው “መንግሥት ሆይ፥ የጤና ባለሙያውን ጥያቄ ከልብህ አድምጥና መፍትሄ ስጥ!” የምንለው።
አክሊሉ ደበላ (የሕክምና ዶ/ር)
——
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.