Home › Forums › Semonegna Stories › ሚዛናዊነት ከራስ ቢጀምር ― ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)
Tagged: በቀለ ገርባ, አብይ አህመድ, እስክንድር ነጋ, ጃዋር, ጠቅላይ ሚኒስትር
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 8 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
March 24, 2019 at 4:19 pm #10401AnonymousInactive
“ገና በጠዋቱ ሀገሪቱ መሪ እያላት ስርዓት አልበኝነት ነገሰ፣ ሕግ ረከሰ፣ የንፁሃን ደም በከንቱ ፈሰሰ የሚል ጩኸት ብዙዎች ቢያሰሙም የሽግግር ባኅሪው ነው በሚል ሚዛናዊ ምላሽ መስጠት አልተቻለም።”
———–ሚዛናዊነት ከራስ ቢጀምር ― ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)
አለማየሁ ገበየሁ
ፍርድ ቤት የቆመችው የፍትህ ምስል /Lady Justice/ ተጠሪነቷና ምሳሌነቷ ለፍርድ ቤት ሥራ ብቻ አይመስለኝም። አይኗን ሸፍና ያላጋደለ ሚዛን የያዘችው አስተዳዳሪዎች በሞራል ሕግ ተመርተው ለዜጎች ሁሉ ሚዛናዊ አገልግሎትና ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ነው።
ዶ/ር አብይ አህመድ ደጋግመው ስለሚዛናዊነት ይሰብካሉ። ጋዜጠኞች የተመጣጠነ ዜና እንዲያቀርቡ፣ አክቲቪስቶች ከዋልታ-ረገጥ ሀሳብ ወደ መሃል እንዲመጡ፣ ፖለቲከኞች እኔ ብቻ ነኝ አዳኝህ ወይም የማውቅልህ ከሚለው አባዜ ተላቀው ለሌላውም ሥራ እውቅና እንዲሰጡ ወዘተ…
የሚዛን መንሻፈፍ ግለሰብን፣ ማኅበረሰብንና ሀገርን እየቆየ እንደሚጎዳና ለማይጠገን ቀውስ እንደሚዳርግ የሚገነዘብ ሁሉ በዚህ ሀሳብ ይስማማል። ችግሩ ዶ/ር አብይ እንዳሉት ሁሉም ቀድሞ ጣቱን የሚቀስረው ሌሎች ላይ የመሆኑ አባዜ ነው። ይህ የጣት ቅሰራ ራሳቸው ዶ/ር አብይንም ይመለከታል። አንዱን ትልቅ ጥፋት ሸፋፍነህ ሌላው ላይ ጣትህን ስትቀስር ሚዛናዊነት ይንጋደዳል። አንዱን ትልቅ ጥፋት አላየሁም ብለህ አይንህን ከሸፈንክ ሌላኛው ጥፋት ላይ የአይንህን መጋረጃ ቀደህ ለመጣል ሞራል ታጣለህ።
ከብዙ ምሳሌዎች የተወሰኑትን ብቻ እናንሳ። ገና በጠዋቱ ሀገሪቱ መሪ እያላት ስርዓት አልበኝነት ነገሰ፣ ሕግ ረከሰ፣ የንፁሃን ደም በከንቱ ፈሰሰ የሚል ጩኸት ብዙዎች ቢያሰሙም የሽግግር ባኅሪው ነው በሚል ሚዛናዊ ምላሽ መስጠት አልተቻለም። ከዚህ ይልቅ በቅድሚያ ለውጡ ያመጣቸውን ትሩፋቶች ሳትደባብቁ አሞግሱ ማለት መጣ። ትክክል ነው ሚዛናዊ ለመሆን የበርካታ ባኅሪያት/ ጥሩ ተናጋሪ፣ ትዕግስተኛ፣ ይቅር ባይ፣ ትሁትና የሰላም አጋር/ መሆናቸውን መመስከር ይቻላል። በዚህ ጥሩ ባኅሪ በመታገዝም መንግስታቸው አስደሳች ፖለቲካዊ ድሎች አስመዝግቧል። ይህ ማለት ግን ለውጡ መሳ ለመሳ እየተጓዘ ያለው ከነውጥ ጋር ነው ነው ማለት ስህተት አይደለም። ሕገ-ወጥነት ሀገሪቷን የወረረው ይቅርባይነት ስለበዛ ነው የሚል የቄለ ግምገማ የለኝም – በዚህ ረገድ መንግስታቸው ስትራተጂካዊ ብቃት የለውም የሚለው ሀሳብ የበለጠ ቅርብ ነው። አሁን በቅርቡ እንኳን የሀገራችን ስርዓት አልበኝነት ተግባር ከ8 እስከ 10 ወራት ይቀጥላል በማለት እንደ ዓመታዊ ዕቅድ ነግረውናል። ሕገ-ወጥነትን አምርሮ ከመታገል ይልቅ ከሕገ-ወጥነት ጋር ተቻቻሎ ለመኖር ማሰብ ገራሚ አቋም ነው። በተሸፋፈነች ፍትሃዊ አይን ሚዛናዊነትን እንይ ከተባለ ከዚህም በላይ ነው።
መንግስት ባለበት ሀገር አሥራ ምናምን ባንኮች በጠራራ ፀሐይ ሲዘረፉ የሽግግር ሂደት ባኅሪው ነው የምትል ከሆነ ሌላውን ሌባ ወይም ሙሰኛ ለመገሰጥም ሆነ ፍርድቤት ለማቆም ይከብዳል። ምክንያቱም ፍ/ቤት የቆመችው የፍትህ ምስል ስለምትታዘብ። ለተቃውሞ ዱላና ገጀራ አደባባይ ይዞ የወጣ ማኅበረሰብ በቸልታ አልፈህ ያለዱላ ስብሰባ የከተመውን ወጣት በማያሳምን ምክንያት አስረህ የምታሸማቅቅ ከሆነ የሚዛናዊነት መሠረትህ ተናደ ማለት ነው። ይከበር እየተባለ የሚለፈፈው ሕግ ባለመከበሩ ዱላና ገጀራው አድጎ እነሆ ዛሬ የጦር መሣሪያ ይዞ አደባባይ መውጣት ተጀምሯል። በገዛ ፍቃድህ ሚዛናዊ ካልሆንክ ብሎም ቸልተኝነት እንደ ኩይሳ ካሳደግክ ሌሎች አደባባይ የተገተረውን የፍትህ ሚዛን በሌላ ጡንቻ ይሰብሩብሃል። ትርፉና ውጤቱም ይሄው ነው።
የቸገረው የከተማ ህዝብ ከሰውነት ተራ ወጥቶ በሠራው ኮንዶሚኒየም አትገባም ተብሎ ገጀራ ሲወደርበት “የባለገጀራዎች ሀሳብ ይለምልም” ብሎ መግለጫ ማውጣት እንዴት ሚዛናዊ ሊሆን ይችላል? በቡራዩና ለገጣፎ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰው መፈናቀል፣ እንግልትና አግላይ ርምጃዋች ከልብ ሳታወግዝ ሌላ ታፔላ ለጥፎ አደባብሶ ማለፍ የሚዛናዊነትን ጥያቄ ያስነሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር የሚበትኑ ሀሳቦች ይወገዙ ይላሉ። በሀገሪቱ ያለው ሁለት መንግስት የአብይና የቄሮ ይባላል የሚል ትንታኔ የሚሰጠው ጃዋር የበርካታ በታኝ ሀሳቦች ባለቤት ቢሆንም ውግዘት አይመለከተውም። ኦሮሞ ከቋንቋው ውጭ ሌሎችን ማነጋገር የለበትም፤ ከሌሎች ጋር መጋባትም ማቆም አለበት የሚለው የ“ምሁሩ” በቀለ ገርባ አፓርታይዳዊ አስተያየት ለመመርመርም ሆነ ለመተቸት አልተፈለገም። በተቃራኒው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚንቀሳቀሰው እስክንድር ነጋ ላይ ግልጽ ጦርነት እናውጃለን ተብሏል። ሲጠቃለል ዶ/ር አብይ በበቀለ፣ በኦነግ፣ በጃዋር፣ በሕገወጥ ፖለቲከኞችም ሆነ በእስክንድር ሀሳብ ላይ ሚዛናዊ መሆን አልቻሉም።
ለዚህም ነው ማንኛውም ሚዛናዊ ለመሆን የሚጥር ሰው ለምን የሚል ቀጥተኛ ጥያቄና እንዴት የሚል የጀርባ ምፀት ለማንሳት የሚገደደው። ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ እንዲሰብር ብሂሉ ስለሚያስገድድ? ምንም ቢሆን ዘር ከልጓም ስለሚስብ?… ኢትዮጵያዊነትን መርህ አድርጌያለሁ የሚል መሪ ለጃዋርም ሆነ ለእስክንድር ሀሳቦች እኩል የድጋፍም ሆነ የተግሳጽ መስፈርት ማበጀት ካልቻለ መርሁ ሁሉ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ ለራሱ ችግር ይፈጥሩበታል (backfire ያደርግበታል)። ዶ/ር አብይ ከጊዜ ወደጊዜ እየገረጣ የመጣባቸውን ሕዝባዊ እምነት ስር ሳይሰድ ለማከም ከፈለጉ ሚዛናዊነት ከራሳቸው መጀመር ያለባቸው ይመስለኛል። ጥሩ መሪ ደግሞ እንደዛ ነው። መንገዱን የሚያውቅ፣ በመንገዱ የሚሄድ እና መንገዱን የሚያሳይ ስለሚሆን። ባለጊዜ ነን በሚሉ ቡድኖች የሚጊሩ አስከፊና አቀያያሚ ጉዳዮችን አደብ ማስገዛት፣ አቅም ቢያጥር እንኳን በግልጽ ‘አካፋን አካፋ’ በማለት ማውገዝ መጀመር አለባቸው። ከዚህ ከጀመሩ ሌላኛውን ብልሹ ሀሳብና ተግባር ለማረቅ ምቹ መደላድል ይፈጥራል። ይህ አካሄድ ልበ ሙሉነትን በቀላሉ ማትረፍ የሚያስችል ሲሆን፥ ከሁሉም አቅጣጫ በቂ ድጋፍ ያስገኛል። አክባቢዎን በሚያውቋቸው ሰዎች መሙላት ብቻ ሳይሆን ገለልተኛና ሚዛናዊ ሀሳብ የሚሰጡትንም አማካሪዋች ቢያበዙ ጭልጥ ብሎ ከመሳሳትም ያድናል።
አለማየሁ ገበየሁ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.