በኦሮሚያ ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞን ቀስቅሶ የነበረው አዲስ አበባን በዙሪያዋ ካሉ የኦሮሚያ ከተሞች ጋር ያስተሳስራል የተባለው ማስተር ፕላን ተራማጅና አንድ ቀን ተመልሶ ይመጣል ብለው እንደሚያስቡ ኦህዴድ ሊቀ መንበር እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ኩማ ደመቅሳ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ባለፈው ሳምንት ኦዴፓ (የቀድሞው ኦህዴድ) በጅማ ከተማ ድርጅታዊ ጉባኤውን ባደረገበት ወቅት ተሳታፊ የነበሩት አቶ ኩማ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ አወዛጋቢ ስለነበሩና እርሳቸው በከፍተኛ የስልጣን ሃላፊነት ላይ በነበሩበት ጊዜ ስለታቀዱና ተግባራዊ ስለተደረጉ ጉዳዮች ምላሽ ሰጥተዋል።
«ኦሮሞ እና አማራን የሚነጣጥሉ አይሳካላቸውም»
በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ ተቀስቅሶ ለረጅም ጊዜ ለዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ መነሻ ምክንያት እንደሆነ የሚነገርለትና ከ2006 ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የነበረው የአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከት እንዳለ ተናግረዋል።
ጉዳዩ ከመፈናቀል ጋር አብሮ ስለመጣ እንጂ «ተራማጅ አስተሳሰብ ነው ብዬ አስባለሁ» በማለት የሚናገሩት አቶ ኩማ፤ ጊዜ ሊወስድ ይችላል እንጂ ማስተር ፕላኑ አንድ ቀን ተመልሶ ይመጣል ብለው እንደሚያስቡ ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በተመሳሳይ ኦሮሚያ ውስጥ ለጠንካራ ጥያቄና ተቃውሞ ምክያት የነበረው የአዳማ ከተማን የኦሮሚያ ክልል መዲና እንድትሆንና የክልሉ መስሪያ ቤቶች ወደዚያው እንዲዘዋወሩ መደረጋቸው ይጠቀሳል።
ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት አቶ ኩማ ውሳኔው ስህተት እነደሌለበት ያምናሉ። አሁንም ወደኋላ መለስ ብለው ሲመለከቱ «አሁንም ያኔ የነበረኝ አቋም ስህተት ነው ብዬ አላምንም» ካሉ በኋላ፤ «አዳማ የክልሉ ዋና ከተማ ሆና እንደተቀየረች ብትዘልቅ ኖሮ ከተማዋ ታድግ እንደነበር» ሲሉ ገልጸዋል።
ማንበብዎን ይቀጥሉ፦ «ማስተር ፕላኑ ተመልሶ ይመጣል» አቶ ኩማ ደመቅሳ