Home › Forums › Semonegna Stories › ‹‹ምን አለሽ?›› የአምለሰት ሙጬ ፊልም ምን ነገር ይኖረው ይሆን?
Tagged: Amleset Muchie, Min Alesh, ቴዲ አፍሮ, አምለሰት ሙጬ, ዋለልኝ አየለ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 4 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
July 23, 2019 at 7:12 am #11474AnonymousInactive
አዲሱ የአምለሰት ሙጬ ፊልም ‹‹ ምን አለሽ? ›› የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል። ይህ ቃል ላልቶ እና ጠብቆ ሲነበብ የተለያየ ትርጉም ይሰጣል። ደግነቱ ላልቶም ጠብቆም ቢነበብ የፊልሙ ርዕስ ነው። ሁለቱም ትርጉም የፊልሙ ጭብጥ ነው። ይሄ ቃል ሌላም ማብራሪያ እንድንሰጥ ያስገድደናል።
ዋለልኝ አየለ (አዲስ ዘመን ዕለታዊ ጋዜጣ)
ከብዙ መገናኛ ብዙኃን እና ድረ-ገጾች አንድ ያስተዋልኩት ነገር “የፊልሙን ኢንዱስትሪ አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ” የሚል አገላለጽ ነበር። ይህ ፊልም ሦስት ዓመታት እና አምስት ሚሊዮን ብር ወስዷል። የፊልሙ ባለቤት ራሷ ታዋቂ ብትሆንም የታዋቂው ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ሚስት መሆኗ ይመስላል ፊልሙን ገና ሳይታይ ዝነኛ አድርጎታል። ምክንያቱም ሌሎች ፊልሞች ከመታየታቸው በፊት እንዲህ ስማቸው ሲጠራ ስላልሰማን ነው። ማን ያውቃል ሲታይ ደግሞ እንደተባለውም የፊልሙን ኢንዱስትሪ ከፍ የሚያደርግ ቢሆንስ? ለመሆኑ በፊልሙ ውስጥ ምን አለ ይሆን?
ስለ ‹‹ ምን አለሽ? ›› ፊልም ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። የፊልሙ ደራሲ፣ ዳይሬክተር እና ፕሮዲዩሰር አርቲስት አምለሰት ሙጬ ማብራሪያ ሰጥታለች።
ፊልሙ ‹‹ ምን አለሽ? ›› የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል። ይህ ቃል ላልቶ እና ጠብቆ ሲነበብ የተለያየ ትርጉም ይሰጣል። ደግነቱ ላልቶም ጠብቆም ቢነበብ የፊልሙ ርዕስ ነው። ሁለቱም ትርጉም የፊልሙ ጭብጥ ነው። ይሄ ቃል ሌላም ማብራሪያ እንድንሰጥ ያስገድደናል።
መርካቶ አካባቢ ‹‹ምን አለሽ ተራ›› የሚባል ሰፈር እንዳለ እናውቃለን። የዚህ ፊልም መቼት ደግሞ መርካቶ ነው። የሆነው በአጋጣሚ ሳይሆን ታስቦበት ነው። ‹‹ምን አለሽ ተራ›› ይህን ስያሜ ያገኘው ቦታው የገበያ ቦታ ስለሆነና እዚያ የሄደ ሰው ምንም እንደማያጣ ስለሚታወቅ ነው። ለመሆኑ የፊልሙ መቼት ለምን መርካቶ ሆነ?
መርካቶ ማለት ትንሿ ኢትዮጵያ ማለት ነው። ከየትም የመጣ ሰው የሚገናኝበት ነው፤ የታታሪ ሰዎች መገኛ ነው፤ የሥራ ቦታ ነው። የፊልሙ ባለቤቶች የተጠቀሙትን ገለጻ ስንጠቀም ደግሞ መርካቶ እንዲህ ነው።
‹‹ሙስሊም ሲሰግድ የክርስቲያኑ በር ላይ አንጥፎ ነው፤ ክርስቲያን ታቦት ሲያወጣ ሙስሊሙ መንገድ እየጠረገለት ነው›› የፊልሙ ባለቤት የሆነችው የአምለሰት ሙጬ ባለቤት ደግሞ ‹‹ራጉኤል አይደል ወይ የአንዋር ጎረቤት›› የሚለው ዘፈኑ የበለጠ ግልጽ አድርጎታል። መርካቶ በእነዚህ ምክንያቶች ለፊልሙ መቼት ተመረጠ። የአፍሪካ ትልቁ የገበያ ማዕከል ነው፤ የአገሪቱ ታታሪ ሠራተኞች መዳረሻ ነው።
የፊልሙ ጭብጥ ደግሞ ከዚህ ጋር ይሄድልናል። ዋና ገጸ ባህሪዋ ሯጭ ናት፤ ድህነትን በሩጫ ማሸነፍ እንዳለብን ታምናለች፡ ፡ ጠንክሮ በመሥራት ከድህነት ለመላቀቅ ሩጫ እንደሚያስፈልግ ታምናለች። በሯጯ እምነት ድህነት ያለው ጭንቅላት ውስጥ ነው፤ የመሥራት ወኔ ካለ የትኛውም ነገር ይሠራል። ሩጫ ያለው ደግሞ መርካቶ ነው። መርካቶ ውስጥ ያለ ነጋዴ ልብ ብለን ብናይ ቁጭ ብሎ የሚዝናናበትና የሚተኛበት ጊዜ የለውም፤ ሁሌም ሥራ ላይ ነው።
ሩጫ የተመረጠበት ሌላም ምክንያት አለው። የፊልሙ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ነው። ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ደግሞ ሩጫ ጥሩ ሽፋን ሆኖ ተገኝቷል፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በሩጫ ስለምትታወቅ። በፊልሙ ውስጥ ሦስት ነገሮች መታወቅ እንዳለባቸው አምለሰት ተናግራለች፤ ድህነት፣ አኩሪ ታሪክ እና ሩጫ። ከአኩሪ ታሪካችን እና የሩጫ ዝናችን ጋር ድህነት እየተፎካከረ ይገኛል፤ ‹‹ይህን ድህነት በሩጫ ማሸነፍ አለብን!›› የደራሲዋ እምነት ነው።
የ‹‹ ምን አለሽ? ›› ቃል መንታ ትርጉሞች
ቃሉ ጠብቆ ሲነበብ፤ ‹‹ምንድን ነው ያለሽ? ምን ይዘሻል? ምን ይኖርሻል…?›› (“What do you have?”) የሚሉ ትርጉሞች ይሰጠናል። እንደተባለው ፊልሙ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ዝና ማስተዋወቅ ነው፤ ይህን ታሪክና ዝና ሲያስተዋወቅ ኢትዮጵያ ‹‹ምን አላት? በውስጧ ምን ይገኛል? እነማን አሉባት?›› የሚለውን ይመልሳል። በፊልሙ ውስጥ ከ400 በላይ ተዋናዮች መሳተፋቸው ደግሞ ይሄን እንደሚያሳይ ይነግረናል።
ቃሉ ላልቶ ሲነበብ ‹‹ምን ጠየቀሽ?›› (“What did he ask you?”) የሚል ትርጉም ይሰጠናል። ይሄ ጥያቄ ለኢትዮጵያ ይሆናል። ዓለም ምን አለሽ(ምን ጠየቀሽ) ተብላ ትጠየቃለች። ዓለም ስለኢትዮጵያ ምን እንደሚል ይነገርበታል ማለት ነው። ስለድህነቷም ይሁን ስለአኩሪ ታሪክ፣ ወግ እና ባህሏ አገራት ምን እንደሚሉ እናይበታለን።
ድምፃዊ አብነት አጎናፍር በአንድ ወቅት ከሸገር ኤፍ ኤም ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ሲናገር፤ ‹‹ለካ አያውቁንም›› የሚለውን ዘፈኑን የሠራው ውጭ አገር ሄዶ ስለኢትዮጵያ ምንም የማያውቁ አጋጥሞት ነው። አብነትና ጓደኞቹ በሆነ አጋጣሚ ታሰሩ፤የታሰሩበትም ከየት እንደመጡ ተጠየቁ፤ ‹‹ከኢትዮጵያ›› ቢሉም ይችን አገር ሊያውቁላቸው አልቻሉም። የተራራ ስም ቢጠሩ፣ የዓድዋን ታሪክ ቢጠቅሱ፣የአትሌት ስም ቢደረድሩ ምንም ሊያውቁላቸው አልቻሉም፤ ‹‹እኛ ግን የእነርሱን የልደት ቀን ሳይቀር እናውቃለን›› ያለው አብነት በዚህ ቁጭት ተነሳስቶ ‹‹ለካ አያውቁንም›› የሚለውን ዘፈን ሠርቷል። ምናልባት አምለሰትም ይሄ አጋጥሟት ይሆን?
‹‹ ምን አለሽ? ›› ፊልም ከውጭ ባለሙያዎች ጋር ነው የተሠራው። ይህም የይዘትና የቴክኒክ ዘመናዊነት እንዲኖረው አድርጓል። በይዘት በኩል ደራሲዋ እንደተናገረችው፤ የሥራ ትጋትን ለማሳየት ከውጭዎቹ የተወሰደው ነገር የጊዜ አጠቃቀም ነው። እነርሱ ጋ እያንዳንዷ ደቂቃ ዋጋ አላት፤ ይሄን ከእነርሱ ተሞክሮ ተወስዶ ተሠርቷል።
በቴክኒካል ጉዳይ ሆሊውድ የሚጠቀማቸው ዘመናዊ መሳሪያዎችን ተጠቅሟል፤ መጠቀም ብቻ አይደለም፤ አዳዲስ ተዋንያን የእንዲህ ዓይነት ዘመናዊ መሳሪያዎችን አጠቃቀም እንዲለምዱ ተደርጓል።
በሌላ በኩል በሚያስፈልግበት ጉዳይ ሁሉ የባለሙያ ድጋፍ ተደርጎበት ነው። ዋና ገጸ ባህሪዋ ሯጭ እንደመሆኗ የአትሌቲክስ ባለሙያ ያስፈልገዋል፤ ይሄንንም ተጠቅሟል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ሚና እንደነበረው በመግለጫው ላይ ተነግሯል። ከአልባሳት ድጋፍ ጀምሮ፣ ምን ዓይነት ልብስ በምን ሁኔታ እንደሚያስፈልግ የሙያ ድጋፍ አድርጓል። ፊልሞች እንዲህ በሚመለከተው ባለሙያ ድጋፍ ሲሠሩ ስነ ምግባሩንና ሙያውን የጠበቀ ይሆናሉና ቢለመድ እንላለን!
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.